ለፖሊስ አመራርና አባላት ሲሰጥ የነበረው ስልጠና ተጠናቀቀ

AMN ህዳር 20/2017 ዓ .ም

ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ፣ ከአዲስ አበባ ፖሊስና ከድሬዳዋ ፖሊስ ለተውጣጡ የወንጀል ምርመራ ባለሙያዎች በዱባይ ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ባለሙያዎች ሲሰጥ የነበረው ስልጠና ተጠናቋል።

የወንጀል ምርመራ ተግባር በየጊዜው አዳዲስ ዕውቀትንና ክህሎትን የሚጠይቅ ሙያ በመሆኑ የወንጀል መርማሪዎች አቅምም ዘመኑን የዋጀና እየረቀቀ የመጣውን ወንጀል አፈፃፀም በምርመራ አጣርቶ ተጠርጣሪዎችን በሕግ አግባብ ተጠያቂ ለማድረግ የሚያስችል መሆን እንዳለበት ተገልጿል።

ስልጠናውን የወሰዱት የወንጀል ምርመራ አመራርና አባላት ዘመኑ የቴክኖሎጂ ዘመን እንደመሆኑ መጠን በዲጂታል ቴክኖሎጂ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን በብቃት ለመመርመር የወንጀል ምርመራ ተግባሩ በቴክኖሎጂና በስልጠና የታገዘ በመሆኑ ለሥራችን መሳካት ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል ብለዋል።

በሌላም በኩል በአድቫንስድ ዲጂታል ፎረንሲክ እና በሳይበር ወንጀል ምርመራ ለፖሊስ አመራርና አባላት ስልጠና ተሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ከኮሪያ ናሽናል ፖሊስ ኤጀንሲ ጋር በመተባበር ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ፣ ከአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ፖሊስ እንዲሁም ከዩኒቨርሲቲው ለተውጣጡ የፖሊስ አመራርና አባላት በአድቫንስድ ዲጂታል ፎረንሲክ እና በሳይበር ወንጀል ምርመራ ሲሰጥ የቆየው ስልጠና የምርመራ አቅምን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያሳድግ ተገልጿል።

በስልጠናው ማጠቃለያ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ የምርምር፣ ማማከርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ምክትል ኮሚሽነር ዳንኤል ብርሃኑ የኮሪያ ናሽናል ፖሊስ ኤጀንሲ ከኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ዩኒቨርሲቲው በፎረንሲክ ቴክኖሎጂ በሳይበር ወንጀል ምርመራ ስልጠና በመስጠቱ ላቅ ያለ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ከስልጠናው አዳዲስ ዕውቀቶችን ያገኙበትና የውጭ ሀገር መልካም ተሞክሮዎችንም መቅሰማቸውን አመራርና አባላቱ ጨምረው መናገራቸውን የፊደራል ፖሊስ መረጃ ያመለክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review