ሉዓላዊነት በዲጂታል ዘመን

ዘመኑ የዲጂታል ነው፡፡ የሠው ልጅ በትውልድ ቅብብሎሽ ከዘመን ጋር እየዘመነ እዚህ ደርሷል፡፡ የማሰብ፣ የማሰላሰል፣ የመመራመር እና አዳዲስ ነገሮችን የመፍጠር ድንቅ ጸጋውን ተጠቅሞ የማይቻል የሚመስለውን ችሎ አሳይቷል፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ በዕውቀት የመራቀቁ እና የማደጉ ሂደት በውጤት እየታጀበ፣ የመሬትን ውስጠ ገመና እየፈተሸ፣ ከጠፈር እልፍኝ እየተምነሸነሸ፣ ለአዲስ ነገር ያለው ጉጉት እያየለ፣ ፍላጎቱ በሥራ ፍሬ እያፈራ… ዓለምን እየሾፈረ ከዲጂታል ዘመን ላይ አድርሷታል፡፡

ከኮምፒዩተር መፈብረክ ጋር ተያይዞ፣ በፈጣን ዕድገት ታጅቦ፣ አዳዲስ ግኝቶችን አዋልዶ ግስጋሴውን የቀጠለው የ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን፤ “የዲጂታል ወይም የመረጃ ዘመን” በመባል ይታወቃል፡፡ እንደ በይነ መረብ (ኢንተርኔት)፣ የሞባይል ስልክ፣ የማህበራዊ ሚዲያ መድረኮች፣ የመረጃ እና የመገናኛ ቴክኖሎጂዎች ያሉት አዳዲስ ግኝቶች ፈጣን ዕድገት ለዲጂታል ዘመን እውን መሆን ወሳኝ ሚና መጫወታቸውን በዘርፉ የተፃፉ ሰነዶች ያስረዳሉ፡፡ አሁን ላይ የሚታየው ቀልጣፋ ግንኙነት፣ እጅግ ፈጣንና የተሳለጠ የመረጃ ተደራሽነት እና ዓለምን ወደ አንድ መድረክ የማምጣት ብቃት የዲጂታል ዘመን ልዩ ባህርይ ነው ብሎ መናገር ይቻላል፡፡

አገራት ሉዓላዊነታቸውን ለማስጠበቅ ተወዳዳሪ አቅምን መፍጠር የሚጠይቀው የዲጂታሉ ዓለም

በዘመነ ዲጂታል ዓለም ብዙ ትሩፋት አግኝታለች፡፡ በአንፃሩ በርካታ ፈተናዎችንም ተጋፍጣለች፡፡ ከትሩፋቱም ሆነ ተፅዕኖው የሚያመልጥ እንደሌለ በግለሰብ፣ በቤተሰብ፣ በማህበረሰብ፣ በአገር ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዕለቱ የምናሳልፋቸው ሁነቶች ምስክር ናቸው፡፡ በዚህ ፅሁፍም ጳጉሜን 3  ቀን  2016  ዓ/ም  የሉዓላዊነት ቀን  በሚል መሰየሙን  መነሻ  በማድረግ የዲጂታል ዘመንን ከሃገራት ሉዓላዊነት ፅንሰ ሃሳብ ጋር ያለውን ቁርኝት፤ በተለይም ተግዳሮቶቹን እና የመፍትሄ አማራጮችን በተወሰነ መልኩ ለመዳሰስ እንሞክራለን፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በ2024 ካወጣው መረጃ በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ ቁጥራቸው 193 የሚሆኑ ሉዓላዊነታቸው በሕግ የተረጋገጠላቸው አገራት አሉ፡፡ እነዚህ አገራት ሉዓላዊ የሚለውን ማዕረግ ለመያዝ ቢያንስ የራሳቸው የመንግስት ግዛት ያላቸው፣ በህጎቻቸውና በአስተዳደራቸው ላይ ያለ የውጭ ጣልቃ ገብነት ሙሉ ቁጥጥር እና ስልጣን ያላቸው መሆን አለባቸው፡፡ ይህን ነባራዊ ወይም ተለምዷዊ ብያኔ በመገዳደር ጥያቄ ውስጥ እንዲወድቅ የዲጂታል ቴክኖሎጂ አብዮት አሉታዊ ተጽዕኖ አድርጎበታል፡፡ የበይነ መረብ (ኢንተርኔት) ተደራሽነት መጨመር፣ በአለም አቀፍ ደረጃ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች መስፋፋት፣ የድንበር ተሻጋሪ የመረጃ ፍሰቶች መበራከት መንግስታት የአገራቸውን ሉዓላዊነት ላለማስደፈር ድንበሮቻቸው ላይ የሚያቆሟቸው ወታደሮች፣ የፀጥታ እና የደህንነት ባለሙያዎች፣ ወንዝና ጠንካራ የብረት አጥሮች በቂ ሆነው አልተገኙም፡፡

የዲጂታል ዘመን በሃገራት ላይ  ካመጣቸው ግንባር ቀደም ፈተናዎች መካከል ሉዓላዊነትን ለማስጠበቅ አስቸጋሪ እና ውስብስብ ማድረጉ አንዱ ነው፡፡ አገራት ሉዓላዊነታቸውን ለማስጠበቅ ዳር ድንበራቸውን በእግር፣ በፈረስ፣ በተሽከርካሪ ወይም በመርከብ ከሚመጣ ጠላት መከላከል በቂ ተደርጎ የሚቆጠርበት ዘመን አብቅቷል፡፡ በትጥቅ የተደራጀ ሠራዊትን ሳያዘምቱ፤ በግለሰብ ወይም በቡድን ደረጃ በተደራጀ፣ በአነስተኛ ክፍል ውስጥ ተቀምጦ የዲጂታል ጦሩን በሚያስወነጭፍ አካል አገራት ጥቃት ሊደርስባቸው እና ሉዓላዊነታቸው ሊደፈር ይችላል፡፡ በዚህ መሰል ጥቃት፤ መንግስት እና ሕዝብ ጥሪታቸውን አሟጥጠው የገነቧቸው ግዙፍ መሠረተ ልማቶች ከአገልግሎት ውጪ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ያከማቿቸው ወሳኝ መረጃዎች ተመንትፈው ባዷቸውን ሊቀሩ፣ ሕዝብና መንግስትን የሚለያዩ የሃሰት መረጃዎች ሊሰራጩ ይችላሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋነኛ ምክንያቶቹ የበይነ መረብ (ኢንተርኔት) ዓለም አቀፋዊ ተፈጥሮ (Global Nature of the Internet)፣ በዘርፉ የተሰማሩ ግዙፍ ኩባንያዎች አይነኬነት (Dominance of Tech Giants)፣ የሳይበር ደህንነት ስጋቶች (Cyber security Threats)፣ የመረጃዎች ጥበቃ ክፍተት (Data Sovereignty) እና የዲጂታል ቅኝ ገዢነት (Digital Colonialism) በዋናነት እንደሚጠቀሱ በዘርፉ ጥናት በመሥራት የሚታወቁት አሜሪካዊ ሊቅ ጎንዛሌዝ.አር.ጄ (González, R. J.) በጎርጎሮሳዊያን የዘመን ቀመር 2020 “War Virtually: The Quest to Automate Conflict, Militarize Data, and Predict the Future” በሚል ርዕስ ፅፈው በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ አማካኝነት ባሳተሙት መጣጥፍ ላይ አስፍረዋል፡፡

የዓለም የኃይል ሚዛን በጥቂት አገራት የተያዘ ነው፡፡ ተደጋግሞ እንደሚባለው ጥቂቶቹ ልዕለ ሃያል አገራት ብዙሃኑን “እንዳሻቸው” እያደረጓቸው ሕይወት ቀጥሏል፡፡ በዘመነ ዲጂታልም፤ የተሻለ ተጠቃሚ፣ በተፅዕኖው የከፋ ተጠባቂ፣ በአንፃሩ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በብዙሃኑ ላይ ተፅዕኖ የማሳደር አቅምን የያዙት እነዚሁ ልዕለ ሃያላን ስለመሆናቸው የአደባባይ ሐቅ ነው፡፡ ለዚህ ማሳያው ዓለምን በዲጂታል ቴክኖሎጂው መስክ ያራቆቷት፣ ምርትና አገልግሎታቸውን ያስፋፉባት፣ ባሻቸው ጊዜና ሁኔታ ማብራት ማጥፋት የሚችሉ፣ ከእያንዳንዱ ጫፍ የተሰራጨን መረጃ የሚሰበስቡ… ትላልቅ ግን ደግሞ ጥቂት የዲጂታል ቴክኖሎጂ ባለቤቶች እነዚሁ ልዕለ ሃያል አገራት የመሆናቸው እውነት ነው፡፡ በአንፃሩ ኢትዮጵያንና የመሳሰሉ በኢኮኖሚም፣ በዲጂታል ቴክኖሎጂውም ከኋላ ረድፍ የሚከተሉ አዳጊ እና በማደግ ላይ ያሉ አገራት ሊተውት በማይችሉት የዲጂታል ቴክኖሎጂ ምህዳር ውስጥ ዳፋውን እየተጎነጩ ይገኛሉ፡፡

ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ አገራት በዲጅታሉ ዓለም ላይ የሚያደርጉት ተሳትፎ በፈተና የመታጀቡ ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያየለ ስለመምጣቱ የቅርብ ጊዜ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በኢትዮጵያ ለዓመታት የቆየና አሁንም የሚታየው በሕዝቦች መካከል ልዩነትን የሚፈጥሩ እና ለግጭት የሚዳርጉ ሃሰተኛ መረጃዎች ስርጭት፣ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እና በሌሎች ወሳኝ ተቋማት ላይ እየተቃጣ የከሸፈ የሳይበር ጥቃት፣ በባንኮች እና የፋይናንስ ተቋማት ላይ የሚቃጣው የማስተጓጎል ተግባርን ለአብነት መጥቀስ እንችላለን፡፡

በጎርጎሮሳዊያን የዘመን ቀመር በ2020፤ “ትራንስኔት” በተሰኘው የደቡብ አፍሪካ መንግስታዊ የሎጂስቲክስ ኩባንያ ላይ የደረሰው ከፍተኛ የሆነ የራንሰምዌር ጥቃት የሚታወስ ነው፡፡ በወቅቱ የደረሰው የሳይበር ጥቃት የወደብ ሥራን እስከማቋረጥ መድረሱን “Cybersecurity in Africa: Threats, Challenges and Solutions”. በሚል ርዕስ በአፍሪካ የኢንፎርሜሽንና ኮሙዩኒኬሽን ጆርናል ላይ የታተመው ፅሁፍ ያመለክታል፡፡

ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ያነጋገርናቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ እና የስማርት ሲቲ ዘርፍ ኃላፊ ቱሉ ጥላሁን (ዶ/ር) ሃሳባቸውን አጋርተውናል፡፡ እንደሳቸው ገለፃ፤ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ለሠው ልጅ ዕድገት እና ብልፅግና እጅግ ወሳኝ መሣሪያ ሆኗል፡፡ ምርታማነትን በመጠንና በጥራት በማሳደግ፣ የሠውን ልጅ የሥራ ጫና በመቀነስ፣ ግንኙነትን በማሳለጥ፣ ቀልጣፋና ፈጣን የመረጃ ልውውጥ እንዲኖር በማድረግ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ለተገልጋዮቻቸው ያላቸውን ተደራሽነት በአስደናቂ ሁኔታ አሻሽሎታል፡፡ የጉልበት፣ የግብዓት፣ የጊዜ ብክነትን አስቀርቷል፡፡ ሠዎች ባሉበት ሆነው ከዓለም መገናኘት እና ያሻቸውን መሸመት የሚችሉበት ደረጃ ደርሰዋል፡፡

የዲጂታል ዘመን ሁኔታን ከመዲናችን አዲስ አበባ እና ከአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማስተሳሰር ሃሳባቸውን ያጋሩት ቱሉ(ዶ/ር)፤ “የዲጂታል ዘመኑ የፈጠራቸውን የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ረገድ እንደ አገር ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻሎች እየታዩ ይገኛሉ፡፡ በተለይ ባለፉት አምስት ዓመታት እየታየ ያለው ለውጥ አበረታች ነው። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እንቅስቃሴም ይህንኑ የሚያሳይ ነው፡፡ ከተማዋን ስማርት ሲቲ የማድረግ መርሃ ግብርን ሊያሳኩ የሚችሉ በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውና እየተሠሩ መሆናቸው ዘመኑን በሚመጥን ደረጃ ለመጓዝ ያለውን ተነሳሽነት የሚያሳይ ነው፡፡ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ተቋማት አገልግሎታቸውን በኦንላይን እያደረጉ ነው፡፡ የኮሪደር ልማቱ አካል ተደርገው የተሻሻሉ ነባር እንዲሁም በአዲስ የተዘረጉ መሰረተ ልማቶች የዲጂታል ቴክኖሎጂን በግብዓትነት በስፋት ተጠቅመዋል፡፡ ለአብነት አዳዲስ የተተከሉ የመብራት ምሰሶዎችን ብንመለከት አገልግሎታቸው ከመብራትነት ባለፈ፤ የደህንነት ካሜራ የተገጠመላቸው፣ ለማስታወቂያ አገልግሎት የሚውል ስክሪን ያላቸው ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ በአገር ደረጃም ሰፋፊ ሥራዎች እየተሠሩ ስለመሆናቸው በ2025 ዲጂታል ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ ታቅዶ እየተተገበረ ያለው አገር አቀፍ ዕቅድ ምስክር ነው” ብለዋል፡፡

በዲጅታል ዘመን አገራት ራሳቸውን ለማደራጀት እና ከተፅዕኖ ለመውጣት በዘርፉ ከፍተኛ ሥራ መሥራት እንዳለባቸው የጠቆሙት የስማርት ሲቲ ዘርፍ ኃላፊ ቱሉ ጥላሁን (ዶ/ር) ኢትዮጵያዊያን በጦርነት አውድማ ሞተው ጠላትን ድል በማድረግ እንደሚታወቁት የቀድሞ አባቶቻችን ራሳቸውን ዘመኑን በሚመጥን አግባብ ማዘጋጀት እንደሚገባቸው አሳስበዋል። እንደ እሳቸው አገላለጽ፤ ጊዜው ራስን በዕውቀት፣ በክህሎት እና በስነምግባር ማብቃትን ይጠይቃል። ስለዚህ ትውልዱ የተፈጠረለትን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ መሆን የሚያስችል የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዕውቀትና ክህሎትን መታጠቅ ይኖርበታል፡፡ ኢትዮጵያዊያን በዚህ ዘርፍ ዕምቅ አቅም እንዳላቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ በሆኑ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ውስጥ ተቀጥረው የሚሠሩ ኢትዮጵያዊያንን መመልከት ይበቃል፡፡ በአገር ውስጥም ያሉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች እና በተለያየ ደረጃ በሙያው ተሠማርተው የሚገኙ ወጣቶች እየሠሯቸው ያሉ ተግባራት በተስፋ ሰጪነታቸው የሚጠቀሱ ናቸው። መንግስትም ዘርፉን ለማሳደግ የሠጠው ትኩረት ትልቅ ነው፡፡ በቅርቡ በጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ(ዶ/ር) ይፋ የተደረገው እና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መንግስት ድጋፍ የሚተገበረው የ5 ሚሊዮን ኮደሮች ንቅናቄ በቀጣይ ዘርፉን የበለጠ ለማሻሻል ትልቅ አቅም ይፈጥራል፡፡

በዲጂታል ዘመን እንደ አገር ሊደርስ የሚችለውን ዓለም አቀፍ ተፅዕኖ ለመከላከል ከዜጎች እና ከመንግስት የሚጠበቅ ቁልፍ ተግባር መኖሩንም ቱሉ ጥላሁን (ዶ/ር) አንስተዋል፡፡ በእሳቸው ገለፃ መሰረት ዜጎች ራሳቸውን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ዕውቀት እና ክህሎት ማብቃት ይኖርባቸዋል፡፡ ዘመኑ የፈጠራቸውን የዲጂታል ቴክኖሎጂ መሣሪያዎች በዕውቀት፣ በአግባቡና በኃላፊነት መንፈስ መጠቀም ይገባል፡፡ በዚህ ዘመን በማህበራዊ ሚዲያዎችም ሆነ በሌሎች አግባቦች የምናሰራጫቸው እያንዳንዳቸው መረጃዎች ከግለሰብ ጀምሮ በማህበረሰብ እና በአገር ደረጃ ሊፈጥር የሚችለውን አዎንታዊ እና አሉታዊ ተፅዕኖ ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት መሆን ይኖርበታል። መንግስት ዜጎች የዲጂታል ቴክኖሎጂ ግንዛቤያቸው እንዲያድግ፣ መሠረተ ልማቶች እንዲሟሉ፣ አገር በቀል የዲጂታል ቴክኖሎጂ ፈጠራዎች እንዲበራከቱ፣ የአገርን እና የሕዝብን አንድነት እና ደህንነት አደጋ ሊጥሉ የሚችሉ ጉዳዮችን ማስቀረት ወይም ማረም የሚያስችሉ የሕግ ማዕቀፎችን በማውጣት ላይ እየሠራ ያለውን ጅምር ተግባር አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል። ትውልድን በዕውቀትና በክህሎት አብቅተው የሚያወጡ የትምህርት ተቋማት ጉዳዩን በትኩረት ይዘው በየደረጃው ሊፈፅሙት ያስፈልጋል። ያ ካልሆነ ግን “በቅኝ ግዛት ሳትገዛ የኖረች አገር” የሚለውን አኩሪ ገድል በዚህ ዘመን አስጠብቆ መጓዝ ከባድ ይሆናል፡፡

በዘመነ ዲጂታል በአገራት ሉዓላዊነት ላይ የተጋረጡትን ፈተናዎች ለመቋቋም መንግስታት በተናጥል እና በጋራ መሥራታቸው አልቀረም። በሥራቸው ውጤታማ ከሆኑት መካከል፡- የአውሮፓ ህብረት አገራት፣ ቻይና፣ አሜሪካ እና ህንድ ይጠቀሳሉ። በርካታ አገራትን አቅፎ የያዘው የአውሮፓ ህብረት የአጠቃላይ መረጃ ጥበቃ ደንብ (General Data Protection Regulation-GDPR) በጎርጎሮሳዊያን የዘመን ቀመር ከ2018 ጀምሮ በመተግበሩ ለአባል አገራቱ የዲጂታል ሉዓላዊነት መጠበቅ ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል፡፡ ይህ ሕግ የአውሮፓ ህብረት ዜጎችን በግል የመረጃ ማሰራጫ ማዕከላቸውን እንዲቆጣጠሩ ያደርጋል፡፡ በአንፃሩ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ኩባንያዎች መረጃን እንዴት እንደሚሰበስቡ፣ እንደሚያከማቹ እና እንደሚጠቀሙ ጥብቅ መስፈርቶችን ይጥላል።

በአገረ ቻይና ተግባራዊ እየተደረገ ያለው ከዲጂታል ቴክኖሎጂ ጋር የተያያዘው ሕግ የአገሪቷን ሉዓላዊነት በመጠበቅ ረገድ በውጤታማነቱ ይጠቀሳል። ይህ ሕግ ታላቁ የፋየርዎል እና የመረጃ ህግ (China’s Great Firewall and Data Localization Law) ይሰኛል፡፡ ሕጉ አገሪቷ የኢንተርኔት አገልግሎትን ለመቆጣጠር እና በመንግስት የማይፈለጉትን ይዘቶችን ሳንሱር ለማድረግ እና ተገቢ እርምጃ በተገቢው ወቅት ለመስጠት ያግዛታል። በተጨማሪም የቻይና ኩባንያዎች በሀገሪቱ ውስጥ ውሂብ (Data)  እንዲያከማቹ የሚያስገድድ የውሂብ አካባቢ ህጎችን አውጥታለች፣ ይህም የቻይና ባለስልጣናት በድንበራቸው ውስጥ የሚፈጠረውን መረጃ ለመቆጣጠር አስችሏቸዋል፡፡

በተመሳሳይ ዩናይትድ ስቴትስ የዲጂታል ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ እንደ ክላውድ አክት (CLOUD Act) ያሉ ህጎችን አውጥታ በሥራ ላይ አውላለች፡፡  የህንዱ ፑሽ ፎር ዳታ ሉዓላዊነት  (India’s Push for Data Sovereignty) የግላዊ መረጃ አሰባሰብን፣ ማከማቻን እና ሂደትን ለመቆጣጠር ያለመ የግል መረጃ ጥበቃ ሕግና ደንብ ይጠቀሳል፡፡

በአጠቃላይ የአገራትን ሉዓላዊነት ፈተና ውስጥ የጣለውን የዲጂታል ዘመን እንቅስቃሴ ተግዳሮቱን እየተቋቋሙ ከውጤቱ ለመቋደስ አገራት በግልም ሆነ በጋራ ጠንካራ ሥራ መሥራት እንደሚገባቸው የዘርፉ ምሁራን ይመክራሉ። ባለሁለት ሰይፍ የሆነውን ዲጂታል ቴክኖሎጂ ሚዛኑን በጠበቀ አግባብ ለመጠቀም  መንግስታት ግልጽነትን እና ትብብርን በማጎልበት ሉዓላዊነትን በሚያከብሩ ዓለም አቀፍ ደንቦች እና አሠራሮች ላይ መተባበር አለባቸው።

በደረጀ ታደሰ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review