ልጆች፤ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የመሥራት ልምዳችሁ ምን ይመስላል?

You are currently viewing ልጆች፤ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የመሥራት ልምዳችሁ ምን ይመስላል?

በለይላ መሀመድ

ሰላም ልጆችዬ፤ እንዴት ናችሁ? ሰላም ናችሁልኝ? “በጣም ደህና ነን” እንደምትሉኝ ተስፋ አደርጋለሁ። ልጆችዬ፤ የመጀመሪያ መንፈቅ ዓመት ወይንም የአንደኛ ሴሚስተር ትምህርታችሁን አጠናቃችሁ የሁለተኛ መንፈቅ ዓመት ትምህርት ከጀመራችሁ ትንሽ ቆየት ብላችኋል፡፡ እረፍታችሁን እንዴት ነበር ያሳለፋችሁት? ልጆችዬ፤ የእረፍት ጊዜያችሁን ጠቃሚ በሆኑ ነገሮች ላይ እንዳሳለፋችሁ አልጠራጠርም። ቤተሰብን በማገዝ፣ በጨዋታና በአንዳንድ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ፡፡

ለመሆኑ ልጆችዬ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ለጤናማ ህይወት ከሚመከሩ ተግባራት መካከል አንዱ መሆኑን ታውቃላችሁ? የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ምን ያህል ጠቀሜታ እንዳለው የስፖርት ባለሙያና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አሰልጣኝ ሲስተር ሜላት ዘውዱ ለእናንተ መልእክት እንዲያስተላልፉ የዝግጅት ክፍላችን ጋብዟቸዋል፡፡ ከባለሙያዋ መልእክት በፊት ግን ህጻን ኤልዳና ሀይሌ እና ህጻን ኻሊድ አደም ምን አይነት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንደሚያደርጉ የነገሩንን እነግራቸዋለሁ፡፡

የ9 ዓመት ህጻን የሆነችው ኤልዳና ሀይሌ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የምታደርገው አልፎ አልፎ በሚዘጋጀው የማስ ስፖርት መርሃ ግብር ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ዝግጅቱ የሚካሄደው መሀል ከተማ አካባቢ ስለሆነ፤ ወደ ስፖርቱ የምትሄደውና የምትሠራው ከእናቷና ከሌሎች ቤተሰቦቿ ጋር በመሆን ነው፡፡ በእንዲህ አይነት ስፖርታዊ እንቀስቃሴዎች መሳተፏ ደስታ እንደሚፈጥርላት የገለጸችው ህጻን ኤልዳና፣ በተለይም ከሌሎች አቻ ጓደኞቿ ጋር ስላስተዋወቃት ተመሳሳይ ዝግጅቶችን በጉጉት ትጠብቃቸዋለች፡፡ ከዚህ ውጪ ትምህርት ቤት በስፖርት የትምህርት ክፍለ ጊዜ እና በእረፍት ጊዜዋ ከጓደኞቿ ጋር እየተሯሯጠች እንደምትዝናና ገልጻልናለች።

የ13 ዓመቱ ኻሊድ አደምም ከስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ጋር ፍቅርና ጥብቅ ቁርኝት እንዳለው ነው የሚገልጸው። በአሁኑ ወቅት በማርሻል አርት ቴኳንዶ ስፖርት በሳምንት ሦስት ቀናት በቋሚነት እየሰለጠነ ሲሆን፤ በዚህም ሰማያዊ ቀበቶ ላይ ደርሷል፡፡ እሁድ እሁድ ጠዋት ከ12 ሰዓት ጀምሮ ከሌላ አካባቢ ከሚመጡ ተመሳሳይ ሰልጣኞች ጋር በመሆን በተመረጡ አካባቢዎች የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያደርጋል፡፡ የቴኳንዶ ስፖርት ከመጀመሩ በፊትም ሆነ አሁን ላይ  ከትምህርት ቤት መልስ የሚኖረውን ትርፍ ጊዜ ከሰፈር ጓደኞቹ ጋር እግር ኳስ ይጫወታል። የማርሻል አርት ቴኳንዶ ስፖርት መስራቱም ሆነ ከጓደኞቹ ጋር መጫወት መቻሉ እንደሚያስደስተውና ልዩ ስሜት እንደሚፈጥርለት ተናግሯል፡፡ 

የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለጤናማ ህይወት ከሚመከሩ ተግባራት መካከል አንዱ እንደመሆኑ መጠን ህጻናት ይህን በመደበኛነት ከማከናወን አንጻር ምን ማድረግ እንዳለባቸው የስፖርት ባለሙያና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አሰልጣኝ ሲስተር ሜላት ዘውዱ ለዝግጅት ክፍላችን ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ እንደ ሲስተር ሜላት ማብራሪያ፤ ህጻናት አምስት ዓመት እድሜ ከሞላቸው በኋላ ሁሉንም አይነት ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ማድረግ ይችላሉ፡፡ ፍላጎታቸውን መሰረት ያደረጉ የስፖርት አይነቶችን ደግሞ በባለሙያ ታግዘው በመደበኛነት እንዲሰሩ ማድረግ ይመከራል፡፡

ህጻናት አሁን ላይ በመደበኛነት እየሰሯቸው ያሉት የስፖርት አይነቶች ማርሻል አርት፣ ቴኳንዶ፣ ካራቴና ውሹ  ስፖርት ናቸው፡፡ ይህንንም ወላጆች ከትምህርት ጋር ይጋጫል በሚል ክረምት ላይ ብቻ ውስን ለሆኑ ጊዜያት ነው እንዲሰሩ የሚያደርጓቸው፡፡ ይሁን እንጂ ህጻናት ዓመቱን ሙሉ ጊዜን በመከፋፈልና በአግባቡ እንዲጠቀሙ በማድረግ በሳምንት ሁለትና ሶስት ቀናት እንዲሰሩ ቢደረግ ጠቀሜታ አለው። ከትምህርት ቤት መልስ በመረጡት የስፖርት አይነት ሲጫወቱ አእምሯቸው ይዝናናል፤ ውስጣቸው ይደሰታል፡፡ አካላዊና ሥነ-ልቦናዊ ጥንካሬ ይኖራቸዋል፡፡ በሥነ-ምግባር የታነጹ ይሆናሉ፡፡ አዕምሯቸው ፈጣንና ነገሮችን የመረዳት ብቃታቸውን በማሳደግ በራስ የመተማመን ክህሎት እንዲያዳብሩም ያደርጋቸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ትኩረት እያገኘና እየተነቃቃ መጥቷል፡፡ ይህ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። በተለይ ህጻናት ለአካላዊና አእምሯዊ እድገት የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ባህል ሊያደርጉ ይገባል ሲሉ የስፖርት ባለሙያዋ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review