ልጆች በትምህርት እንዴት ጎበዝ መሆን እንደሚቻል ታውቃላችሁ?

ሰላም ልጆችዬ እንዴት ናችሁ? ሰላም ናችሁ? ትምህርታችሁን በትኩረት እንደምትከታተሉ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ የሁለተኛ መንፈቅ ዓመት (ሴሚስተር) ትምህርታችሁን መማር ከጀመራችሁ ቆያችሁ አይደል? ጎበዞች፡፡ ልጆችዬ የደረጃ ተማሪ ለመሆን ክፍል ውስጥ በጥሞና ከማዳመጥ በተጨማሪ በቂ ጥናትና ዝግጅት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ታውቃላችሁ? ለዛሬ የሴቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ ለትምህርታቸው ትኩረት በመስጠት ውጤታማ የሆኑ ሴት ተማሪዎችን ተሞክሮ አቅርበንላችኋል፡፡ በአግባቡ አንብባችሁ ቁም  ነገር እንደምትጨብጡ ተስፋ እያደረግን የአስተያየት ሰጪዎችን ሀሳብ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡     

“ወደፊት አትሌት በመሆን ሀገሬን የማስጠራት ህልም አለኝ፡፡”

የ5ኛ ክፍል ተማሪ ሮማን ዳዊት

90 ነጥብ 5 አማካኝ ውጤት በማምጣት ከክፍሌ አንደኛ መውጣት ችያለሁ፡፡ 5ኛ ክፍል ስገባ 1ኛ ልወጣ የቻልኩት አክስቴ የተለየ ትኩረት እና ክትትል ስላደረገችልኝ ነው። እንዳጠና ታበረታታኛለች፤ ምቹ ሁኔታ ትፈጥርልኛለች፡፡ የማጠናበትን የተለየ ቦታ አዘጋጅታልኛለች፡፡ አስፈላጊ ነገሮችን አሟልታልኛለች፡፡ በየቀኑ የቤት ሥራዬን ስሠራ ክትትል ታደርግልኛለች፡፡ የሚከብደኝንም ታስረዳኛለች፡፡

የ4ኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ 5ኛ ነበር የወጣሁት፡፡ አሁን 1ኛ ወጥቻለሁ። ይህንን ውጤት ለማምጣት በየቀኑ የማደርገውን ሥራ በጊዜ ከፋፍዬ መጠቀሜ አግዞኛል። ከትምህርት ቤት ወደ ቤቴ እንደገባሁ የደንብ ልብሴን እቀይራለሁ፡፡ ተጣጥቤ መክሰሴን ከበላሁ በኋላ የተማርኩትን አጠናለሁ፡፡

አትሌት የመሆን ህልም አለኝ። እንደነ ደራርቱ አገሬን ማስጠራት እፈልጋለሁ። አትሌቶች አሸንፈው የሀገራችንን ሰንደቅ ዓላማ ሲያውለበልቡ አይቼ ውስጤን ደስታ ተሰማውና እንደነሱ የመሆን ፍላጎት አደረብኝ። ከትምህርቴ ጎን ለጎን ቤት ውስጥ ብዙ ጊዜ ገመድ እዘላለሁ፣ እሮጣለሁ፣ የተለያዩ ስፖርታዊ እንቅቃሴዎችን አደርጋለሁ፡፡ ጎበዝ በመሆኔ መምህሮቼ በተለይም የሂሳብ አስተማሪዬ አጋዥ መጽሐፍ ሸልሞኛል፡፡

“ጥሩ ውጤት በማምጣት ከክፍሌ አንደኛ ወጥቻለሁ”

የ7ኛ ክፍል ተማሪ መስከረም አቅነዳ

ጥሩ ውጤት (98 ነጥን 9 አማካኝ ውጤት) በማምጣት ከክፍሌ አንደኛ ነው የወጣሁት፡፡ አንደኛ ልወጣ የቻልኩትም ክፍል ውስጥ መምህር ሲያስተምር በንቃት በመከታተልና በማጥናት ነው። የማጠናው ከትምህርት ቤት መልስ በቂ እረፍት ካደረግኩ በኋላ ነው፡፡ ሳጠና የማይገባኝን ቤተሰቦቼን በመጠየቅ እንዲያስረዱኝ አደርጋለሁ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በቴሌቪዥን ትምህርታዊ ፕሮግራሞች ይከፍቱልኛል፡፡ ለምሳሌ ለ6ኛ እና 8ኛ ክፍል ትምህርት የሚሰጥ የልጆች ዓለም የሚል ፕሮግራም ከፍተው እንድከታተል ያደርጉኛል፡፡ መምህሮቼም እንዳጠና ያበረታቱኛል፡፡

1ኛ ክፍል 4ኛ እንዲሁም 2ኛ ክፍል 2ኛ የወጣሁ ሲሆን ከ3ኛ ክፍል ጀምሮ ግን 1ኛ ነው የምወጣው። ወላጆቼ በትምህርቴ ጎበዝ በመሆኔ አጋዥ መጻሕፍትን ሸልመውኛል። ወደፊት ተምሬ አርክቴክት መሆን እፈልጋለሁ። ይህንን ሙያ ልመርጥ የቻልኩትም የማይ ቾይዝ ሪል ስቴትን በቴሌቪዢን በማየቴ ነው፡፡ ከጥናቴ ውጪ ራሴን ለማዝናናት ስፈልግ የተለያዩ ዲዛይኖችን እሞክራለሁ። ተማሪዎች ጎበዝ ተማሪ ለመሆን በስነ ምግባር መታነጽ ይኖርባቸዋል፡፡ መምህራንን ማክበር ያስፈልጋል፡፡ መምህራን ሲከበሩ የምንማረውን ትምህርት ማክበርና መውደድ እንችላለን። ሌላው መከታተልና ያልገባንን ያለምንም ፍርሀት በመጠየቅ ለመረዳት መጣር ያስፈልጋል፡፡

“አንደኛ ልወጣ የቻልኩት ትምህርት ላይ ትኩረት በማድረጌ ነው”

የ6ኛ ክፍል ተማሪ ዮርዳኖስ ሰይፉ

ከክፍሌ 98 ነጥብ 1 አማካኝ ውጤት በማምጣት አንደኛ ነው የወጣሁት። ከ2ኛ ክፍል ጀምሬ አንደኛ ነው የምወጣው፡፡ አንደኛ ልወጣ የቻልኩት ደግሞ ከጨዋታ ይልቅ ትምህርት ላይ ትኩረት በማድረጌ ነው፡፡ ቤተሰቦቼም እንዳጠና ይገፋፉኛል። የአጠናን ዘዴየ ጠዋት ወደ ትምህርት ቤት ከመሄዴ በፊት የምማረውን ቀድሜ አጠናለሁ። ከትምህርት ቤት ስመለስም በየቀኑ የተማርኩትን አጠናለሁ፡፡ ሁልጊዜ ወላጆቼ ጥሩ ውጤት ካመጣሽ ትሸለሚያለሽ እያሉ ሽልማት በመስጠት ጭምር ያበረታቱኛል፡፡ በተመሳሳይ መምህሮቼም ያበረታቱኛል፡፡ ወደፊት ትምህርቴን ተምሬ ፓይለት መሆን እፈልጋለሁ፡፡

በለይላ መሀመድ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review