ልጆች፤ እንዴት ናችሁ? ትምህርትስ ጥሩ ነው? ጤናችሁ ደህና፤ ትምህርታችሁ ጥሩ እንደሆነ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ በዛሬው ቆይታችን እንደተለመደው አንድ ጉዳይ ይዘን ወደ እናንተ መጥተናል። ይኸውም ልጆች በትምህርታቸው ጎበዝ እንዲሆኑ ምን ማድረግ አለባቸው? የሚል ነው፡፡ ጉዳዩ ሰፊ ቢሆንም በጥቂቱ ለማየት ወድደናል፡፡ ለዚህ ደግሞ በ“አለንላችሁ በጎ አድራጎት ድርጅት” የስነ-አዕምሮ ባለሙያ ሱዛን ሳላ ሙያዊ ማብራሪያቸውን እንዲያጋሩን አድርገናል።
ልጆች በትምህርታችሁ ስኬታማ በመሆን ስታድጉ መሆን ለምትፈልጉት ዶክተርነት፣ ኢንጂኒዬርነት፣ መምህርነት… ጥናታችሁ ላይ መበርታት ይጠበቅባችኋል፡፡ ለዚህ ደግሞ አዕምሯችሁ ሳይከፋፈል የምታጠኑበት አመቺ የጥናት ቦታ ሊኖራችሁ ይገባል፤ ወላጆቻችሁም ይህን እንዲያመቻቹላችሁ ማድረግ አለባችሁ፡፡ ይህም ሲባል እንደ ቴሌቪዢን ከመሳሰሉ አላስፈላጊ ድምፆች የተጠበቀ አካባቢ ሊኖር ይገባል። ለጥናታችሁ የሚረዷችሁን የተለያዩ ቀለማት ያላቸውን ቁሳቁሶች እንደ እርሳስ፣ ማርከር፣ ስቲከር የመሳሰሉትን ከጥናት ጊዜ በፊት ማስተካከል ተገቢ ነው፡፡ መደበኛ የጥናት ጊዜ እንዲኖራችሁ የጊዜ ሰሌዳ ማዘጋጀት ይጠበቅባችኋል። ከዚህ በተጨማሪ በፈተና ወቅት እንዳስፈላጊነቱ መቅደም ያለበትን ማስቀደም ይኖርባችኋል፡፡
ልጆች ለትምህርታችሁ ስኬታማነት ልታደርጉት የሚገባ ሌላው ነገር ተገቢ ካልሆነ ጭንቀት ራስን ማራቅ ነው፡፡ ተገቢ ያልሆነ ጭንቀት ለጤናችሁም ሆነ ለውጤታችሁ ጥሩ አይደለም፡፡ ʻነገ ፈተና አለኝ እንዴት ልሆን ነው፣ እወድቅ ይሆን? የአምና ፈተና ውጤቴ እንዲህ ነበር፤ ለወደፊቱ ችግር ይፈጥርብኝ ይሆን?’ በሚል መጨናነቅ፤ ዛሬ ላይ ውጤታማ እንዳትሆኑ እንቅፋት ስለሚሆናችሁ ከእዲህ አይነት አስተሳሰብ መውጣት ይጠበቅባችኋል፡፡
ልጆች፤ ሌላው ትኩረት ልትሰጡት የሚገባው ጉዳይ በራስ መተማመንን ማሳደግ ነው፡፡ ሀሳባችሁን በራሳችሁ መግለጽ ይጠበቅባችኋል፡፡ ትምህርት ቤት ውስጥ የሚሰጧችሁን የቤት ስራዎች፣ ፕሮጀክቶች… በራሳችሁ መስራት መቻል አለባችሁ፡፡ ይህ የ“እችላለሁ” ስሜት እንዲኖራችሁ አጋዥ አቅም ይሆናችኋል።
ሌላው ልጆች በቴክኖሎጂ የምታጠፉትን የጊዜ አጠቃቀም መመጠን ይጠበቅባችኋል፡፡ ልጆችዬ፤ ረጅም ሰዓታትን ስልክና የመሳሰሉ ነገሮች ላይ ስታሳልፉ የትኩረት መጠናችሁ ይቀንሳል፡፡ እየበዛ ሲሄድ የአዕምሮ ጤና እክል ያመጣል፡፡ ስለሆነም ስልክ፣ ቴሌቪዢን… የምታዩበትን ግዜ በልኩ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ እያንዳንዷን እንቅስቃሴያችሁን በፕሮግራም በመደልደልና የማከናወኛ ግዜ በማስቀመጥ ይሁን የሚባለው አንደኛውና ቁልፉ ጉዳይ ይኸንኑ በአግባቡ ለማስኬድ ነው፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ልጆች ስልክ ስትጠቀሙ አስተማሪ የሆኑ ጌሞችን አውርዳችሁ ማየት ላይ ብታተኩሩ እናንተም በእጅጉ ትጠቀማላችሁ፡፡
የቤተሰብ የጋራ ግዜ ላይ በንቃት መሳተፍ፣ በጽሞናም መከታተል ሌላኛው ተገቢ እና አስፈላጊ ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በቤት ውስጥ እናትና አባት የሚሰሩትን ስራ እያዩ ማደግ፣ ትምህርትም መውሰድ ይጠበቅባችኋል። ከወላጆቻች የህይወት መንገድ ለእናንተ የሚሆን አስተማሪ ነገር እንደሚገኘው መዘንጋት የለባችሁም፡፡ በፊልም የምታዩዋቸውን በተሳሳተ እና ልክ ባልሆነ መንገድ አርአያ አድርጋችሁ እንዳትሄዱ መጠንቀቅ አለባችሁ፡፡ በጥቅሉ በትምህርታችሁ ስኬታማ እንድትሆኑ ከላይ የተጠቀሱትን ጨምሮ ጠቃሚ የሆኑ ነገሮችን ማድረግ ይጠበቅባችኋል እንላለን፡፡ እናንተስ ምን ትላላችሁ? ከቤተሰቦቻችሁ፣ ከመምህሮቻችሁ፣ ከጓደኞቻችሁ ጋር ሀሳብ ተለዋወጡ፤ በጋዜጣችን የዌብ ሳይት ገጽ መልዕክት ከላካችሁ ደግሞ ይደርሰናል፡፡ መልካም ሳምንት ይሁንላችሁ!
በለይላ መሀመድ