በኪነ ጥበባዊ ስራዎች ውስጥ ጎልተው ከሚንጸበራቁ ነገረ- ጭብጦች መካከል አንዱ ነው፤ተፈጥሮ፡፡ ውበትና የሰው ባህሪያትን ለመወከል ተፈጥሮ በኪነ ጥበብ ውስጥ ትልቅ ቦታ አላት፡፡ በሃገራችን የኪነ ጥበብ ሥራዎች ውስጥ ትልቅ ስፍራ እንዳላትም ሙዚቃዎቻችን፣ የዕይታዊ ሥነ ጥበቦቻችንና የሥነ ጽሑፍ ስራዎቻችን ጥሩ አብነት ናቸው፡፡
ከሀገራችን አውራ ከያኒያን መካከል ስለ ተፈጥሮ ያልተቃኘ፤ ስለተፈጥሮ ውበት ያላዜመና ስለተፈጥሮ ሃያልነት በብሩሹ ያልመሰከረ የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም። ለአብነትም ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድህን፣ ገብረክርስቶስ ደስታ፣ በዓሉ ግርማ፣ ጥላሁን ገሰሰ፣ ቴዎድሮስ ታደሰ፣ መዝገቡ ተሰማና ሌሎች ከያኒያን በፈጠራ ሥራዎቻቸው ተፈጥሮን አጉልተው በማሳየት ይታወቃሉ። በተለይ ደግሞ በውበት ላይ ውበትን አክላ ክሱት በምትሆንበት ወርሃ- መስከረም ከተፈጥሮ ጋር አያይዘው ተጠብበውባታል። በዚህ አጭር ጽሑፍም ወርሃ መስከረምን ለኪነ ጥበባዊ የፈጠራ ስራዎች ማበብ ትልቅ ተነሳሽነት እንደምትፈጥርና አበርክቶዋም ትልቅ መሆኑን በጨረፍታ እናስቃኛችኋለን፡፡
“የኢትዮጵያ ታሪክ ጥያቄዎችና ባሕሎች” በተሰኘው በ1986 ዓ.ም. በታተመው መጽሐፋቸው፤ ሀብተማርያም አሰፋ (ዶ/ር) ወርሃ-መስከረምን እንዲህ ገልጸዋታል። “መስከረም ‘ምስ-ከረም’ ከከረመ በኋላ ወይም ክረምት ካለፈ በኋላ ማለት ነው። የመስከረም ወር ዝናብ የሚቆምበት ፀሐይ የምትወጣበት ከወንዞች ንጹሕ ውሃ፣…የሚጎርፍበት፣ አዝርዕት አድገው ማሸት የሚጀምሩበት፣ ሜዳዎች፣ ተራራዎችና ሸለቆዎችም በአበባ የሚያሸበርቁበት እና የሚያቆጠቁጡበት ነው” በማለት ወርሃ መስከረምን ይገልጿታል። የምሁሩን አገላለጽ ተከትለን መስከረምን ስንቃኛት ለኪነ ጥበባዊ የፈጠራ ሥራዎች እጅግ ምቹ ሆና እናገኛታለን፡፡ ለምን? ከተባለ ደግሞ ከውበት ጋር ጥብቅ ትስስር አላትና ነው መልሱ፡፡
ሥዕል
እንደ ሥዕል ላለ የዕይታዊ ሥነ ጥበብ ተፈጥሮና ውበት እጅግ አስፈላጊ ነገሮች ናቸው። ተፈጥሮና ውበት ህብረት ፈጥረው በሰው ላይ ከፍተኛ መደመም የሚፈጥሩት ደግሞ በወርሃ-መስከረም ነው፡፡ ሰዓሊው እንደ ማንኛውም ሰው የክረምቱ ጭጋግ አልፎ የመጀመሪያው ብርሃናማ ወር (መስከረም) እንዲመጣ መሻቱ ተጠባቂ ነው፡፡ ታዲያ ሰዓሊው ይህቺን የውበት እመቤት የሆነችውን መስከረምን እንደሌላው ሰው ተገርሞ ብቻ አያሳልፋትም፡፡ የፈጠራ ሥራው እንብርት ያደርጋታል እንጂ፡፡ ምክንያቱም የፈጠራ ስራ የሚጀምረው ከንሸጣ (inspiration) ስለሆነ፡፡
መስከረምና ተፈጥሮ ውበት ለብሰው፤ መሬት ደግሞ አደይ ተጎናጽፋ ስትመጣ፤ ሰዓሊው ብሩሹን ይዞ በሸራው ላይ ውበትን ያስሳል፡፡ በተፈጥሮ በህብረ- ቀለማት ውበት ተነሽጦ አዲስ ተስፋን ይሰንቃል፡፡ አዲስ መሻትና ጉጉት በተደራስያን ላይ እንዲጋባም ያደርጋል። መስከረምና ተፈጥሮም የፈጠራ ሥራዎቹ እምብርት የመሆን አቅም አላቸው፡፡
ለአብነትም ከሃገራችን ሰዓሊያን መካከል የተፈጥሮን ጸዓዳ ውበት፤ የመልክዓ-ምድር ግርማ ሞገስና ከሰዎች ጋር ያላቸው መስተጋብርን አጉልቶ በማሳየት ረገድ መዝገቡ ተሰማ ቀዳሚ ተጠቃሽ ነው፡፡ መዝገቡ በሥዕል ሥራዎቹ የተፈጥሮን ትንግርት ገልጦ ያሳያል። የተፈጥሮ ህብረ- ቀለማትን በስራዎቹ ላይ አጉልቶ በማሳየት የሰዎችን ቀልብ ይገዛል። ቀለሞቹን በቡርሹ አጥቅሶ ሸራዎቹ ላይ ያፋቅራል። የመዝገቡ የሥዕል ሥራዎች በሆነ ወር ስም ይሰየሙ ቢባል ያለማጋነን በመስከረም ነው መሰየም ያለባቸው። ከዚህ በመነሳት ወርሃ- መስከረም ለፈጠራ ስራዎች ማበብ ትልቅ ተነሳሽነት እንደምትፈጥር መመስከር ይቻላል፡፡
ሙዚቃ
ሙዚቃ ለስሜት እጅግ የቀረበች ኪነት ነች፡፡ የሙዚቃ እምብርት የሆነችው ዜማ ደግሞ የሰዎችን ቀልብ በቀላሉ ትገዛለች። ታዲያ ይህቺ ዜማ መልኳ ብዙ ነው፡፡ መገኛዋም አውታረ-ብዙ ነው፡፡ ሙዚቀኛው ዜማን ለመቀመር ተፈጥሮን አተኩሮ ማስተዋል ይጠበቅበታል፡፡ የአዕዋፋትን ዝማሬ በጽሞና ማድመጥ ይኖርበታል፡፡ ተፈጥሮ ደግሞ ዜማ አውጥታ የምታንጎራጉርበት ትልቁ ወቅት መስከረም ነች፡፡
ከዚህ አንጻር የውበት እመቤት የሆነችው ወርሃ- መስከረም ለሙዚቀኞች የምትመች ወር ነች፡፡ ከተፈጥሮ ውበትን ብቻ ሳይሆን ዜማን ለመቅዳት ማን እንደ መስከረም?! ለዚህ ጥሩ ማሳያ የቀደሙት የሃገራችን እውቅ ሙዚቀኞች ናቸው፡፡ ኮከቡ የሃገራችን ሙዚቀኛ ጥላሁን ገሰሰ የመስከረም መጥባትን ከውበት ጋር አሰናኝቶ አንጎራጉሮታል፡፡ ቴዎድሮስ ታደሰና አስቴር አወቀም በተስረቅራቂ ድምጻቸው ወርሃ መስከረምን ከውበትና ከተፈጥሮ ጋር አሰናኝተው ማቀንቀናቸው የሚታወስ ነው። ይህንን መነሻ በማድረግ ወርሃ- መስከረም እንደ ሙዚቃ ላሉ የፈጠራ ስራዎች ማበብ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳላት ጥርጥር የለውም፡፡
ሥነ ጽሑፍ
ሥነ ጽሑፍ በቃላት የሚከየን፤ በቃላት ውበትን ክሱት የሚያደርግ የፈጠራ ዘርፍ ነው። ለሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ተፈጥሮና ውበት እጅግ አስፈላጊ ጭብጦች መሆናቸው ከተለያዩ ከያኒያን ሥራዎች መረዳት አያዳግትም፡፡ ወርሃ-መስከረም ደግሞ በሥነ ጽሑፍ ውስጥ የጎላ ሥፍራ አላት፡፡ ለከያኒያኑ ትልቅ መነሳሳትን በመፍጠር ለኪነ ጥበባዊ የፈጠራ ሥራዎች ጉልህ አበርክቶም ሰጥታለች፡፡ በቀደመው ዘመን አበቦችና ተክሎች ተሰብስበው ቀለም ይሰራባቸው ነበር፡፡ የአበቦችና ተክሎች ቅጠል ደርቆ፣ ተቀይጦ ብራና ተፍቆ፣ ሥነ ጽሑፍ ተጽፎ ታሪክ ተሰንዷል፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ መስከረም ተመራጭና ትክክለኛ ወር ናት፡፡
ሀብተማርያም (ዶ/ር) ከላይ በተጠቀሰው መጽሃፋቸው፣ ወርሃ መስከረምን “የጨለማና የችግር ጊዜ የሚያበቃበት፤ የብርሃን፣ የደስታ፣ የእሸት፣ የፍሬና የጥጋብ ጊዜ የሚጀምርበትና የሚተካበት ነው፡፡ …በወርኃ መስከረም መሬቷ በአደይ አበባ አሸብርቃ ስለምትታይና በተለይም ዕንቁ የመሰለ አበባ ስለምታወጣ ዕንቁጣጣሽ፣ ዕንቁ የመሰለ አበባ አስገኘሽ ለማለት ‘ዕንቁጣጣሽ’ ተብላለች። አቧራ፣ ቡላ የነበረችው መሬት በዝናቡ ኃይል ለምልማ ተመልከቱኝ፣ ተመልከቱኝ የምትል ያሸበረቀች፣ በአበባ የተንቆጠቆጠች ሆነች…” ይላሉ፡፡ ከዚህ ከምሁሩ ብያኔ በመነሳት ወርሃ-መስከረም ጭጋጋማውን የክረምቱ ወራት ተገባድዶ በብርሃናማው የበጋው ወራት የመሸጋገሪያ ወር ነች፡፡ ይሄ ሽግግር ደግሞ በከያኒው ስሜት ላይ የሚፈጥረው ለውጥና ተነሳሽነት ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ለአብነትም ከቀደምት ባለቅኔዎች ከበደ ሚካኤል፣ ሙሉጌታ ተስፋዬ፣ ገብረ ክርስቶስ ደስታና ሌሎችም ገጣሚያን ለመስከረም የተቀኙበት ዋነኛ ምክንያት ይህንን ሽግግር በከያኒያኑ የሚፈጥረው የስሜት ለውጥና ተነሳሽነት ከፍተኛ በመሆኑ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ወርሃ-መስከረም ለኪነ ጥበባዊ የፈጠራ ስራዎች መወለድ ትልቅ አስተዋጽኦ የምታደርግ ወር ነች፡፡
በአብርሃም ገብሬ