መስከረም በባለቅኔዎች ብዕር

You are currently viewing መስከረም በባለቅኔዎች ብዕር

እንቁጣጣሽ እንኳን መጣሽ

በአበቦች መሃል እንምነሽነሽ

ዳመናው ይግፈፍ ይውረድ ዥረቱ

ፀሐይዋ ትውጣ ትሙቅ ምድሪቱ

በፀሐይ ሙቀት ትድመቅ አበባ

ጸደይ አማረች መስከረም ጠባ ትላለች አንጋፋዋ አርቲስት ዘሪቱ ጌታሁን በዘመን አይሽሬውና በአዲስ ዓመት ማድመቂያ ዘፈኗ። በእርግጥም መስከረም ልዩ ነው፤ ለአይን ማራኪ እይታን ይፈጥራል፤ ውብ ነው፤ ጋራና ተራራው አይንን የሚስብ መንፈስን የሚያድስ አረንጓዴ ሸማ ይለብሳል፡፡ መስከረም አዲስ ስሜት ነው። ሁሉም ሰው በአዲስ ወኔና እቅድ ለአዲስ ለውጥ ይነሳሳል። ህይወትና ተፈጥሮ እንደ አዲስ ይነቃቃል፡፡ መስከረም ተናፋቂ ነው፤ ምክንያቱም በዚህ ወር ጠፍተው የከረሙ አበቦችና ወፎች ይከሰታሉ፡፡ መስከረም ጥበብ ነው፤ ምክንያቱም ባለቅኔዎች ብእራቸውን፣ ሰዓሊዎች ብሩሽና ሸራቸውን እንዲያነሱ ድምጻውያን እንዲያቀነቅኑ አድርጓቸዋል፡፡ ወዳጅ ዘመድ “እንዴት ከረማችሁ” ተባብሎ የሚጠያየቅበት፣ እንቁጣጣሽን አብሮ የሚያሳልፍበት፣ ምግብና መጠጥ የሚገባበዝበት፣ መልካም ምኞትና ተስፋ የሚገላለጽበት ወር ነው፡፡ የአዲስ ልሳን ዝግጅት ክፍልም ተናፋቂ፣ ውብ፣ ባለትዝታ፣ የብርሃን፣ የብራ፣ የተስፋ እና የልምላሜ እንዲሁም የተፈጥሮ መለወጥ መልክ መገላጫ የሆነው መስከረም በባለቅኔዎች እዴት ተገለጸ የሚለውን ለመዳሰስ ሞክሯል፡፡

በመስከረም የሚታየው የተፈጥሮ ውበት ለቅኔ መነሻ ሃሳብ ሆኗል

መቼም መስከረምና ግጥም ሲነሳ ወደ ሁሉም ሰው አእምሮ ቀድሞ የሚመጣው የሰዓሊና ገጣሚ ገብረክርስቶስ ደስታ “አንተነህ መስከረም” የሚለው ግጥም ነው፡፡ ባለቅኔው፡-

ማለቂያ በሌለው ደማቅ ሰማያዊ፤

ከሩቅ ያለው ጋራ ተነክሮ ሐምራዊ

በዚያ ላይ ደመናው እንደ ጥጥ ተነድፎ፤

እየተራራቀ ሲያንጃብብ ተቃቅፎ።

አንተ ነህ መስከረምመስከረምን በቃላት የስእል ውብና ምስል ከሳች በሆነ አገላለጽ ገልጾታል፡፡ መስረከም ሰማዩ እንዲያምር፣ ጎርፉና ብርዱ የክረምቱ ዝናብና ጉም መሻር፣ የአዲስ ተስፋና አዲስ ገጽ ምልክት መሆኑን ይገልጻል፡፡

የሐምሌን ጨለማ የነሐሴን ዝናም፤

የሻርከው አንተ ነህ፤

በብርሃን አውዝተህ

በክረምቱ ወራት ሰማዩን ያስጌጠው፤

የማርያም መቀነት በቀለም ያበደው።

ጤዛው አርሶታል መሬቱ ላይ ለቆ፤

በቀይና ቢጫ መስኩ ተለቅልቆ።

ወንዝና ጅረቱ ድንጋይና ዐፈሩ፤

አገሩ ውብ ሆኗል ሜዳው ሸንተረሩ።

ይህ ግጥም ፈረንጆቹ “Topographical poetry” የሚሉት የግጥም አይነት ነው ሊባል ይችላል፡፡ ይህ የግጥም አይነት ዋናው አላማው መልክዓ ምድር ወይም አንድን አካባቢን አካላዊ ገፅታዎች በቃላት በመግለጽ ሌሎች ሰዎች ላይ ስሜቱን ማጋባትና ስእላዊ  እይታ መፍጠር ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ግጥም ብዙውን ጊዜ ተራሮችን፣ ሸለቆዎችን፣ ወንዞችን፣ ደኖችን እና ሌሎች የተፈጥሮ አካላትን ጨምሮ ስለ ቦታው አቀማመጥ ቁልጭ ያለ እና በአጭር ቅኔ በማቅረብ ልዩ የሆነውን ምንነት እና ባህሪ ለመግለጽና ስሜቱን ለማጋባት ያለመ ነው ይላሉ ጃዲፕ ሳራንጅ የተባሉ የዘርፉ ምሁር፡፡ እ.ኤ.አ. በ2018 ለንባብ በበቃውና “Topography and Poetry” በተሰኘው ስራቸው ላይ እንደገለጹት የመሬት ገጽታና ውበትን ልምላሜን በቅኔ መግለጽ አንባቢዎች እይታውን፣ ድምፁን እና ስሜቱን በገጣሚው ቃል አማካኝነት እንዲረዱ ያስችላቸዋል። ይህም በቅኔ አንባቢው እና በመሬት ገጽታ መካከል ልዩ የግንኙነት ስሜት እንዲኖር ያደርጋል፡፡ ከላይ የተገለጹት የሰዓሊና ገጣሚ ገብረክርስቶስ ደስታ ስንኞችም በዚህ አውድ የሚቃኙና የሚገለጹ ናቸው፡፡

ዕንቁጣጣሽ አንተ ስጦታህ የበዛ፤

ለሰው መታሰቢያ ውበት የምትገዛ።

በሽቱ መዓዛህ ለውጠው ዓመቱን፤

ይታደስ ያረጀው ፍጥረት ሌላ ይሁን።

ከምረው ዘመኑን ካበው ባመት ባመት፤

በወሩ ደረጃ ፍጥረት ይጓዝበት።

ፍየሎች ይዝለሉ ቅጠል ይበጥሱ፤

ከተሰደዱበት ወፎች ይመለሱ።

ይልቀሙት እህሉን፤ ይሥሩ ቤታቸውን፤

ይስፈሩበት ዛፉን...በማለትም ሁሉንም ሰው ትዝታ ያለበትን የሌለበትንም ጋራውና ዛፉን የሚያውቀውም የማያውቀውም በትዝታ ስሜት እንዲነጉድና ህይወትና ኑረት በኢትዮጵያ በወርሃ መስከረም ምን እንደሚመስል በምናብ ያስቃኘናል።

የደስደስ ያሰሙ ንቦች ይራኮቱ፤

ይንጠራሩ አበቦች ይንቁ ይከፈቱ።

እንቦሳና ግልገል በመስኩ ይፈንጩ፤

ከብቶች ሣሩን ይንጩ፤

ሕጻናት ይሩጡ ይሳቁ ይንጫጩ።

ዛፎች ይተንፍሱ፤

የነፋሱ ጠረን፤

ይሰራጭ በቦታው ያውደው አገሩን።

ዐደይ አበባ ነህ የመስቀል ደመራ፤

ጠረንህ አልባብ ነው ዐየርህ የጠራ።

ያገር ልብስ አንተ ነህ ነጭ እንደ በረዶ፤

ሰው የሚያጌጥብህ ጥበብህን ወስዶ እያለ መስከረምን የበለጠ እንድናውቀው፣ እንድንረዳው እና ከሌላ ማእዘን እንድናየው ይቀሰቅሰናል። የግጥሙ አንባቢዎች ከተፈጥሮ እና አካባቢ ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዲያስቡት፣ እንዲያሰላስሉት እና በትዝታ እንዲያስታውሱት ይገፋፋል። በዚህም ገጣሚው መስከረም የወራቶቹ ሁሉ አውራ ነው ሲል ይገልጸዋል።

ቡቃያ ነህ እሸት ጓሚ የበሰለ፤

አረንጓዴ ልብስህ በጌጥ የተሳለ።

ጥቁር አረንጓዴ፤ ቢጫማ አረንጓዴ፤

ያተር አረንጓዴ፤ ንጹህ አረንጓዴ።

ቀለም! ቀለም! ቀለም!

የሚስተካከልህ የሚያስንቅህ የለም፤

ሐዘን የምታርቅ የገነት ምሳሌ፤

ይታደል ወለላህ ጠጁ በብርሌ።

ይስከር በደስታ ሕዝቡ ይሳሳቅ፤

ድምጹ እየተማታ ሙዚቃው ይፍለቅ።

ዕንቁጣጣሽ ብለን እንስጥህ ሰላምታ፤

የዘመኑ መሪ የወሮቹ ጌታ።

ሰዓሊና ገጣሚ ገብረክርስቶስ ደስታ ቅኔውን ሲያጠቃልል

ይጨብጨብ ለዝናህ!

ይጨብጨብ ለሥራህ!

ይጨብጨብ ለመልክህ!

አንተ ነህ መስከረም፤

ዘመን የምታድስ አስጊጠህ በቀለም በማለት ነው።

ስለመስከረም የተቀኙ የሀገራችን ባለቅኔዎች እና ገጣሚዎች እጅግ በርካታ ናቸው። ብዙዎች በቅኔ አማካኝነት የተፈጥሮን ዓለም በምእናብ የሚቀርጹ ድንቅ ስራዎችን ፈጥረው፣ አድናቆት እና ማሰላሰልን ለማነሳሳት ያለውን አቅም ለመፍጠር ሞክረው ተሳክቶላቸዋል። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ባለቅኔው ሙሉጌታ ተስፋዬ ነው፡፡ የባለቅኔው ሙሉጌታ ተስፋዬ (አያ ሙሌ) “ደስ ይላል መስከረም” ይሰኛል፡፡ ይህ ግጥምም መስከረም በመጣ ቁጥር በብዙዎች ዘንድ የሚታወስና በሬዲዮ የሚሰማ እንዲሁም በጋዜጣ የሚነበብ ነው፡፡ ባለቅኔው ግጥሙን የሚጀምረው፡-

በግርሻጣይ ሰርዶ ነቅሎ በሚያዚያሽ ተርበጥብጦ

በግንቦት ሐሩር ተቀቅሎ በፀሐይ አብስሎ በዝናብ አብቅሎ

ከወዳጅ ከዘመድ ተቀላቅሎ

ባዝራን ከአህያ አዳቅሎ

በባለበርሸት ሽልም በቅሎ

ተፈናጦ አብሮ ገስግሶ

ጅራፍ ግርፊያ ሆያ ሆዬቡሄ በሉ ተጫውቶ

ኪዳነ ምሕረትን አንግሶደግሞ በወሩ አስተርዮ

ግሼን ማሪያም እማአርአያም ደጀሰላም ደርሶ

ለመሳለም

እዮሃ አበባዬ መስከረም ጠባዬ

ዐደይ ለምለም ለኔ እንዳንቺ የለም

እያሉ ንጥቂያ ..

ከጀንበር መፍለቂያ እሥከ ጀንበር መጥለቂያ

አለላ ነቅሎ ባሕር እንጉዳይ

ጀግና ሰው ገዳይ

አካል እንጉዳይ

እያሉ ሲያንጎራጉሩ

ደስ ይላል መስከረምበሚሉ ስንኞች ነው። ይህ ግጥም  እንደ ሰዓሊና ገጣሚ ገብረክርቶስ ደስታ ሁሉ አላማው መስከረምን በቅኔ መግለጽ ነው። ነገር ግን የግጥሙ የመጀመሪያ አካባቢ ከሚታዩና ከሚዳሰሱ የተፈጥሮ መልኮች ይልቅ ስለ ባላገሩ ህይወትና ባህል ሰፊ ትኩረት ይሰጣል፡፡ የባህልና የህይወት መስተጋብሩን ያሞካሻል፡፡ ይቀጥልና እርሱም ወደ ተፈጥሮ ውበት ያቀናል፡፡

ቡቃያው ጣል ከንበል ሲል

ሽሩባዋ ወርዶ እንዲያ ሲዘናፈል

ልቤ እንደበቆሎ ያድራል ሲፈለፈል

በቀጭን ተሰርታ ሥትል ዘንከት ዘንከት

ጃሎ ሲል ሊያነጋ አገር በመለከት

 ለመስቀል ጠንስሶ በማድጋ ገንቦ ለእንግዳ   ቀንሶ

በሞቴ አፈር ስሆን እያለ ሲያጋፍር

ጥርስ እንጎቻ አስፍቶ አሞጭ በመሰለው እርጎ ፍርፍር

እንኳን ሳቅ ጨዋታው ድብድቡ ልፊያው

ድገሙኝ ያሰኛል ሰፈፍ የለሽ ሞገድ መደዶ ዘር ዜማ ሲቆረቆር ክትፊያው

ደስ ይላል መስከረም፡፡

ጋዜጠኛ እና የሥነ ጽሑፍ ሃያሲ ዋለልኝ አየለ በተለይ ሁለቱን ግጥሞች በተመለከተ ያለውን ሃሳብ ለዝግጅት ክፍላችን ሲያስረዳ ቅኔ ማለት የምታውቀውን ነገር በአዲስ አገላለጽና አተያይ መግለጽ ነው፡፡ መስከረምን ሁላንችም እናውቀዋለን። ኖረንበታል፤ እየኖርንበት ነው፤ ሁለቱ ባለቅኔዎች ግን ለየት ባለ አገላለጽ መስከረምን በሌላ መልክ እንድናየው ከማድረጋቸው ባለፈ በትዝታ ወደ ኋላ እንድንመለስና ከልጅነት እስከ አዋቂነት ያለውን ጊዜ እንድናሰላስል ያደርጉናል ብሏል፡፡

ዋለልኝ አየለ… የሽንብራ እሸት እየጠረጠሩ

የልጅነት ሚዜኧረ አይዋ ክንዴእያሉ እየጠሩ

አብሮ ወፍ ጥበቃ ማማ ላይ ተሰቅሎ

ካፊያውን በገሳ በአንድ ተጠልሎ

እሳት አቀጣጥሎ በቆሎ ጠባብሶ

አየሁ አላየሁምሰማሁ አልሰማሁም

በላልቶ አፍ አብሶ

ለስለሶ አስፈትሎ ናት ኩታ ለብሶ

ላዋቂ ተልኮ ለልጅ ተጎናብሶ

ደስ ይላል መስከረም የሚሉት የባለቅኔ ሙለጌታ ስንኞች በገጠራማው ክፍል የተወለደ እና ያደገ ሰው በትዝታ ወደ ቀየው ነጉዶ ልጅነቱን እንዲያስታውስ የሚደርግ ነው፡፡ የገብረክርስቶስ ስራም ቢሆን እንኳን የተወለዱበትን ቀዬ ይቅርና ሌላንም የሚያስናፍቅ ነው ሲልም አክሏል፡፡ የሚያመሳስላቸው ደግሞ ሁለቱም መስከረም የሌሎች ወራት ማእዘን መሆኑን መጋራታቸው ነው ይላል፡፡፡

ጥቅምትና ኅዳር ቢያዋውል ምንጭ ዳር

ታኅሳስና ጥር ዐውድማ አስለቅልቆ ጥሪት እሚያስቋጥር

የካቲት መጋቢት መኸር አስከትቶ ቢያበስል እንደ ዐቃቢት

ሚያዚያና ግንቦቱ ተርቲበኛው ቀርቦ ወርዶ ረከቦቱ

የላም ልጅ በዋንጫ ቢቀርብ ሥልባቦቱ

ሰኔ ሐምሌ ነሐሴ እንደ ቄስ ምናሴ

እያረበረበ ደግሞ እየወረበ

ሰማይ በበረቀ ታርሶ ርሶ ሲስረቀረቅ

ከራሱ እስኪታረቅ

ሁሉም እንደ ግብሩ

ሁሉም እንደ ሙያው!

አሥራ ሁለቱም ወር

እዮሃ አበባዬ መስከረም ሲጠባ

ያኔ ነው ገቢያ

ያኔ ነው መታያው

ያኔ ነው ማባያው

ደስ ይላል መስከረምባለቅኔ ሙሉጌታም መስከረምን ከሌሎች ወራት አንጻር እንደዚህ ነው የገለጸው፡፡ መስከረም በወጣት ገጣሚያን ዘንድም የተገለጸ እና የግጥም ርእስ መሆን የቻለ ልዩ ወር ነው፡፡ ከእነዚህ ገጣሚዎች ውስጥ በዕውቀቱ ስዩምን መጥቀስ ይቻላል፡፡

በአጠቃላይ መስረከም ወር ለኢትዮጵያውያን ልዩ እና ድንቅ ወር ነው። ዶቼቬሌ በኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር በ2005 ዓ.ም “ኢትዮጵያ እና መስከረም” የሚል አንድ ጽሑፍ ለንባብ አብቅቶ ነበር፡፡ ጽሑፉም እንዲህ ይላል፡፡ መቼስ ሀገሬው መስከረምን ሲናፍቅ ‘ለብቻ’ ነው። በባህሉ፣ በትውፊቱ፣ በስለ-ምኑ፣ … መስከረም በኪነ- ቃሉ እና ስነ- ቃሉ ልዩ ሥፍራ ይሰጠዋል። እንደ መስከረም ክብር፣ ሞገስ እና ፀጋ የተቸረው የትኛው ወር ይሆን? ማንም! ሀገሬው ለቆንጆ ልጁ ስም ሲያወጣ ‘መስከረም’ እንጂ በሌላ ወር ሰይሞ ያውቃል? አያውቅም። በኢትዮጵያ ምድር መስከረም ለሰው ልጅ ብቻ ሳይሆን ለእንስሳት እና አዕዋፋት ራሱ ልዩ ጊዜ ነው። “ኢትዮጵያ ነይ በመስከረም” እንዲሉ መስከረም ለኢትዮጵያ ውበቷ፣ ቀለሟ፣ ትዕምርቷ፣ የባህር ሃሳቧ መባቻ ነው። ተናፋቂው መስከረም ዝም ብሎ ወር ብቻ አይመስልም።

በአብርሃም ገብሬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review