AMN-የካቲት 23/2017 ዓ.ም
በጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ የተመራ የጤና ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች ልዑካን ቡድን በጉራጌና በሀድያ ዞኖች በጤናው ዘርፍ እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎችን ተዟዙረው ጎብኝተዋል።
በጉብኝታቸው ወቅት መንግስት ለመጀመሪያ ደረጃ ጤና አገልግሎት ትኩረት ሠጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ተናግረዋል።
በወልቂጤ ከተማ በተለይም የመጀመሪያ ደረጃ ጤና እንክብካቤ የሚሰጥባቸውን ተቋማት በጥሩ ሂደት ላይ እንደሚገኙም ሚንስትሯ ጠቁመዋል።
በከተማው ግንባታው ያልተጠናቀቀውን ሆስፒታል መመልከታቸውንም አንስተው፤ ሆስፒታሉ ተጠናቆ አገልግሎት እንዲሰጥ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
እንዲሁም ለበርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘውን በሀድያ ዞን የንግስት እሌኒ መሀመድ መታሰቢያ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል መመልከታቸውን ገልፀዋል።
ሆስፒታሉ የመድኃኒት አቅርቦትን ጨምሮ ያሉበትን ችግሮች ለመፍታት ከተቋሙ አመራር አባላት ጋር የተሰራው ሥራ ውጤታማ መሆኑን ማረጋገጣቸውን ጠቁመዋል።
በሆስፒታሉ የፅኑ ህሙማን የህክምና አገልግሎት መስጫን ፅዱ ከማድረግ ጀምሮ በርካታ መሻሻሎች እንደታዩም አስረድተዋል፡፡
ሚኒስቴሩ ከህክምና አገልግሎት ጋር ተያይዞ ከማህበረሰቡና ከጤና ባለሙያዎች የሚነሱ ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ በመመለስ ጤናማና አምራች ዜጋን ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በዚሁ ወቅት የጤና ሚንስቴር ለንግስት እሌኒ መሀመድ መታሰቢያ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላዝድ ሆስፒታል ያደረገው የአንድ አምቡላንስ ድጋፍ ርክክብ መደረጉንም ኢዜአ ዘግቧል።