AMN – ጥር 2/2017 ዓ.ም
መንግስት የወጪ በጀትን በዋንኛነት በሀገር ውስጥ ገቢ በመሸፈንና የበጀት ጉድለት ዝቅተኛ እንዲሆን በማድረግ ምቹ የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታን ለማስፈን እየሰራ ነው ሲሉ የገንዘብ ሚንስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ ገለጹ፡፡
የፌዴራልና የክልሎች የፋይናንስ፣ የገቢዎች፣ የፕላንና ልማት 29ኛው የምክክር መድረክ በጅማ ከተማ ተጀምሯል።
የምክክር መድረኩ በዋናነት ተግባራዊ እየተደገ ባልው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም፣ በመንግስት ፋይናንስ አሰተዳደር ስርዓት፣ በሀገራዊ የልማት እቅድ እና በገቢ ዘርፍ በተሰሩ ስራዎች ላይ ያተኩራል ተብሏል፡፡
በምክክር መድረኩ ላይ የገንዘብ ሚንስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ እንደገለጹት ኢትዮጵያ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራዊ በማድረግ ላይ ናት፡፡
መንግስት የወጪ በጀትን በዋንኛነት በሀገር ውስጥ ገቢ በመሸፈንና የበጀት ጉድለት ዝቅተኛ እንዲሆን በማድረግ ምቹ የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታን ለማስፈን እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
የተሟላ ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ውጤታማነት በማረጋገጥ ረገድ ከፌዴራል እስከ ታችኛው የመንግስት መዋቅር ድርስ ርብርብ ማደረግ ይጠበቃል ሲሉም አመልክተዋል፡፡
በምክክር መድረኩ የመንግስት ፋይናንስ አስተዳደር ማሻሻያ ስራዎች ያመጡት ለውጦች የተገመገመ ሲሆን የተገኙት ውጤቶች አበረታች ቢሆኑም ለውጡን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ መገለጹን ከአዲስ አበባ ፋይናንስ ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡