መንግስት ችግሮች በድርድር እንዲፈቱ ጽኑ ፍላጎት አለዉ – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

You are currently viewing መንግስት ችግሮች በድርድር እንዲፈቱ ጽኑ ፍላጎት አለዉ – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

AMN-መጋቢት 11/2017 ዓ.ም

መንግስት ችግሮች በድርድር እንዲፈቱ ጽኑ ፍላጎት እንዳለው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ተናገሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሀገሪቱ የተለያዩ ክልሎች በተለይ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች እየተስተዋሉ ያሉ የጸጥታ ችግሮችን አስመልክቶ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በአንድ እጅ ሰላማዊ ትግል፣ በሌላ እጅ ደግሞ በጦርነት መንግስት ለመጣል የሚሞክሩ ኃይሎች አሉ ሲሉም ተናግረዋል።

መንግስት ችግሮች በድርድር እንዲፈቱ ነው የሚፈልገው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ባለፉት 7 ዓመታት ከየትኛውም የጎረቤት ሀገራት ጋር ጦርነት ያላካሄደ መንግስት አሁን ያለው መንግስት ብቻ እንደሆነም ገልጸዋል።

ይህም ከሀገር ባለፈ ለቀጣናው ሰላም ያለውን ቁርጠኛ አቋም የሚያሳይ እንደሆነ በምላሻቸው አብራርተዋል።

በኢትዮጵያ ሁለት መሰረታዊ ስብራቶች እንዳሉ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከዚህም ውስጥ አንደኛው የመጠፋፋት ባህል እንደሆነ ተናግረዋል።

ይህም መንግስታት ወደ ኃላፊነት ሲመጡ አልጋው አልጸናም በሚል ሳይደራጁ ለማጥፋት የሚደረግ ሙከራ መሆኑን ነው ያብራሩት።

ይህ የኢትዮጵያ ታሪክ በበርካታ መንግስታት የተሞከረ ስለመሆኑም ጠቁመዋል።

ሁለተኛው ከሶሻሊስት እሳቤ ጋር በስፋት ወደ ኢትዮጵያ የገባ በሽታ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህ እሳቤ በኢትዮጵያ ያመጣው ችግርም የጠላት እና የወዳጅ ፍረጃ ነው ብለዋል።

ይህም እሳቤ ለሰላማዊ ድርድር ቦታ የማይሰጥ እና በኃይል ስልጣን የመያዝ አባዜን አምጥቷል ሲሉ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ እየተስተዋለ ያለውም ችግር ይህ እንደሆነ በማንሳት፣ አሁንም በህዝብ የተመረጠን መንግስት በኃይል ለመጣል የሚሞክሩ ኃይሎች እንዳሉ አመላክተዋል።

ይሁን እንጂ የሚገርመው ነገር እነዚህ የነፃነት ታጋይ ነን የሚሉ ኃይሎች የሚያሰቃዩት እንታገልልሃለን የሚሉትን ህዝብ ነው ሲሉም አብራርተዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review