
AMN – ህዳር 8/2017 ዓ.ም
መንግስት ወጣቶች የፈጠራ ሀሳባቸውን የሚያሳድጉበት እና ቴክኖሎጂን የማላመድና የመፍጠር አቅማቸውን የሚያጎለብቱበት አማራጮችን እየፈጠረ እንደሚገኝ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ(ዶ/ር) ገለጹ።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጂንሲ (ጃይካ ) ውስጥ በሚገኘው ኒንጃ ዩኒቨርስቲ ስታርትአፕ ልማት ፕሮግራም እና አር ኤንድ ዲ ግሩፕ ጋር በመተባበር በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች የሚገኙ ጀማሪ የስታርትአፕ ሀሳብ ያላቸው ተማሪዎች የንግድ ሀሳባቸውን ለማሳደግ እና የፈጠራ ስራዎቻቸውን ወደ ቢዝነስ እንዲቀይሩ ድጋፍ የሚያደርግ የስልጠናና ውድድር መርሀ ግብር አካሄዷል።
ውድድሩ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እና አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ የተውጣጡ 23 ጅምር የስታርትአፕ ሀሳብ ያላቸው ተማሪዎች የተሳተፉበት ሲሆን፤ ከእያንዳንዱ ዩኒቨርስቲ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ የወጡ ተወዳዳሪዎች የእውቅናና ለስራቸው የሚያገለግላቸው ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ (ዶ/ር) መንግስት የጀመረውን በእውቀት የሚመራ እና በቴክኖሎጂ የተደገፈ የኢኮኖሚ ጉዞ ውጤታማ ለማድረግ የስታርትአፕ እና የፈጠራ ስራዎች ትልቅ አበርክቶ እንዳላቸው ገልጸዋል።
መንግስት ወጣቶች የፈጠራ ሀሳባቸውን የሚያሳድጉበት እና ቴክኖሎጂን የማላመድና የመፍጠር አቅማቸው የሚያጎለብቱበት እድል እያመቻቸ ይገኛልም ብለዋል።
የጃፓን ዓለም አቀፍ የትብብር ኤጀንሲ(ጃይካ) ተወካይ ሳኪኮ ኮሮሳካ የኢትዮጵያ መንግስት በዩኒቨርሲቲዎች የሚደረገው የፈጠራ ሀሳብን የማጎልበት ሥልጠና እና ውድድር ወደ ሌሎች ዩኒቨርስቲዎች ለማስፋፋት የያዘውን እቅድ ለማሳካት የጃፓን መንግስት ድጋፍ ያደርጋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ውድድሩ በመቀሌ፣በጅማ፣ በአዲስ አበባ እና በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲዎች እየተተገበረ ይገኛል።