የሶማሌ ክልል ርዕሠ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሀመድ የሀገራችን የምስራቁ ድንበር ደህንነትን በማረጋገጥና የክልላችን ሰላምና ፀጥታ ፀንቶ እንዲቀጥል በማድረግ ረገድ መከላከያ ሠራዊታችንና የክልሉ ፀጥታ ሀይሎች እንደ አገር እንድንኮራ አድርገውናል ብለዋል።
በምስራቁ የሃገሪቱ ክፍል ሰላምና ፀጥታ ዙሪያ ውይይት ተካሂዷል፡፡
በውይይቱም ርዕሠ መስተዳድሩ፣ ክልላችን ከለውጡ በኃላ ህብረተሰቡን በማሳተፍ በሰራቸው ስራዎችና የፀጥታ ሀይሎች የማጠናከር ተግባራት እንደ ክልል ተከስቶ የነበረውን ነውጥ በመቀልበስ አሁን የተገኘውን አስተማማኝ ሠላም ማምጣት ተችሏል ነው ያሉት።
አቶ ሙስጠፌ መሀመድ አገራችን የያዘችውን ፈጣን ዕድገት ለማደናቀፍ አልሸባብና የውስጥ ፀረ-ሰላም ሀይሎች ተናበው የምስራቁን ቦርደር አደጋ ላይ እንዳይጥሉ የፀጥታ ሀይሉ በንቃት መከታተል እንዳለበት አስገንዝበዋል።
በመከላከያ ዘመቻ ዋና መምሪያ የሃይል ክትትልና ስምሪት መምሪያ ሃላፊ ሜጄር ጄኔራል ተስፋዬ አያሌው ኢትዮጵያን በምስራቁ ቦርደር ለመተንኮስ ባለፉት ጊዜያት አልሸባብ በርካታ ሙከራዎችን ያደረገ መሆኑን ጠቁመው ህብረተሰቡን ጨምሮ የመከላከያ ሠራዊትና የክልሉ ፀጥታ ሀይሎች የአገሪቱን ቦርደርም ሆነ ክልሉን ሳያስደፍሩ መቆየታቸውን አንስተዋል።
የሶማሌ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀኔራል አብዲ አሊ በበኩላቸው ባለፉት ዘጠኝ ወራት 99 የአልሸባብ አባላትን በመደምሰስ ለጠላት ምስራቅ ኢትዮጵያ እንደማይቀመስ ያሳየና ከድምበር ባሻገር ከጀግናው መከላከያ ሠራዊት ጋር ግዳጆችን በመጋራት ድሎችን አስመዝግበናል ማለታቸዉን ከሃገር መከላከያ ሰራዊት ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል፡፡