AMN – ታኅሣሥ 29/2017 ዓ.ም
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በአፋር ክልል በርዕደ መሬት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አደጋው በደረሰበት የገቢ ረሱ ዞን የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት አባል ሙሳ አደም (ዶ/ር) ገልፀዋል።
ሠራዊቱ በአዋሽ ፈንታሌና በዱለሳ ወረዳዎች በርዕደ መሬት ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች ከአደጋ ቀጠና በማውጣት ሕይወት አድን ስራ እየሰራ ነው ብለዋል።
በክልሉ ገቢ ረሱ ዞን የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት አባልና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ሙሳ አደም (ዶ/ር) የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በችግር ቀን ደራሽ መሆኑን ያሳየበትን ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
የሰላም ዘብ የሆነው ሠራዊቱ ለርዕደ መሬቱ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የሚኖሩ ወገኖችን በ14 ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች በማጓጓዝ ህይወት የመታደግ ተግባር እየፈጸመ መሆኑን ተናግረዋል።
ሠራዊቱ ተጋላጭ የሆኑ ወገኖችን ከአደጋ ቀጠና ከማንቀሳቀስ ባሻገር የመጠጥ ውሃ እና ሌሎች ድጋፎችን በማቅረብ አጋርነቱን አሳይቷል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅትም ሠራዊቱ የአካባቢው ነዋሪዎችን የአደጋ ስጋት ካለባቸው ቦታዎች የማንሳት ተግባሩን እየተወጣ እንደሚገኝም ገልፀዋል።
ሠራዊቱ ስፍራው የከሰም ስኳር ፋብሪካ የሚገኝበት በመሆኑ የፋብሪካውን ደህንነትና የአካባቢውን ሰላም በማረጋገጥ ረገድም ግዳጁን እየተወጣ ነውም ብለዋል።
የመከላከያ ሰራዊት ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመው የህዝብ አጋርነቱን በተለያዩ ተግባራት ማስመስከር መቀጠሉን ማስታወቃቸውን ከመከላከያ ሰራዊት የማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።