አዲስ አበባ ታይተው የማይጠገቡ በርካታ ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ እምቅ የቱሪዝም ሀብቶች አሏት። ሙዚየሞችን፣ ሐውልቶችን፣ አብያተ- መንግስታትን፣ የተለያየ የኪነ- ህንፃ ውበትና አሻራ ያረፈባቸው ታሪካዊ ቤቶችን፣ ቤተ- እምነቶችን፣ ፓርኮችን እና ዋሻዎችን በጉያዋ አቅፋ ይዛለች፡፡ በቅርብ ዓመታት ደግሞ ተጨማሪ የመዲናዋን ገጽታ የቀየሩ፣ የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎች አማራጮችን ያሳደጉ ትላልቅ የቱሪዝም ፀጋዎች ለምተው ወደ ስራ ገብተዋል።
አቶ አብዱልከሪም ኡመር በትርፍ ጊዜያቸው አልፎ አልፎ በከተማዋ የሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻዎችን የመጎብኘት ልምድ አላቸው፡፡ ያገኘናቸውም ከቤተሰባቸው ጋር ሆነው በዓድዋ ድል መታሰቢያ ጉብኝት ሲያደርጉ ነው፡፡ “በቅርቡ ተሰርተው ለህዝብ ክፍት የሆኑ እንደ እንጦጦ፣ አንድነት፣ ወዳጅነት አደባባይ ፓርክ ያሉ የመስህብ ቦታዎችን የማየት ዕድል አጋጥሞኝ አይቻቸዋለሁ። ቦታዎቹን ሳናለማ መቆየታችን ያስቆጫል።” የሚሉት አቶ አብዱልከሪም፣ ብዙ ጓዳ ውስጥ ተደብቀው የቆዩ ሀብቶቻችንን አሁን ማውጣትና መጠቀም ጀምረናል፡፡ ይህን ጅምር ነባር የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎችንም ለጉብኝት ምቹና ሳቢ እንዲሆኑ በማድረግ ማጠናከር እንደሚገባ ያነሳሉ፡፡
ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ አቶ መሰለ ዘውዱ የቱሪዝም ስፍራዎችን የመጎብኘት የዳበረ ባህል ባይኖራቸውም፣ የእረፍት ጊዜ ሲኖራቸው ከልጆቻቸው ጋር በመሆን ከሚኖሩበት ጎጃም በረንዳ አካባቢ እንደ ብሔረ- ፅጌና ጉለሌ የዕፅዋት ማዕከል ወዳሉ መናፈሻዎች ጎራ እያሉ ያሳልፋሉ፡፡ የዓድዋ ድል መታሰቢያ መሰራቱ ደግሞ የሀገራቸውን ታሪክ እያወቁና እየተዝናኑ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉበት አማራጭ አግኝተዋል፡፡ ሰዎች የእረፍት ጊዜያቸውን የሚያሳልፉባቸው እንደነዚህ ዓይነት ቦታዎችን ለማስፋት የሚሰራው ስራ በጣም ትልቅና የሚያስደስት በመሆኑ መጠናከር እንዳለበትም ገልጸዋል፡፡
አሁን አሁን የቱሪዝም እንቅስቃሴውና አካሄዱ እየተቀየረ መጥቷል፡፡ ቱሪስቶች መስህቦችን ማየት ብቻ ሳይሆን በሚሄዱበት አካባቢ ባለ እንቅስቃሴ ላይ ተሳትፎ ማድረግ ይፈልጋሉ፡፡ ለምሳሌ፡- ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ ያለምንም አስጎብኚ በእግራቸው እየተንቀሳቀሱ ከተማዋን ማየት፣ ሬስቶራንት ጎራ ብለው ምሳ መብላት፣ ቡና ሲፈላ ወይም እንጀራ ሲጋገር ማየት ብቻ ሳይሆን በሚሳተፉበት ዓይነት መልክ የተቃኘ ሆኗል ይላሉ የኢትዮጵያ ቱሪስት ጋይድ ባለሙያዎች ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንት እና በአስጎብኝነትም ከ16 ዓመታት በላይ በመስራት ላይ የሚገኙት አቶ ክብሮም ተስፋዬ፡፡
እንደሳቸው ገለፃ፣ ከዚህ ቀደም አዲስ አበባ ላይ እንግዶች በራሳቸው ከሆቴል ወጥተው የእግር እንቅስቃሴ የሚያደርጉበት ምቹ ሁኔታ ብዙም አልነበረም፡፡ ምክንያቱም በእግር ጉዞ ለማድረግ መንገዶች ምቹ፣ መዳረሻ ቦታዎች ያሉባቸው አካባቢዎችም በደንብ የለሙ አይደሉም፡፡ የዓድዋ ድል መታሰቢያን ጨምሮ በቅርብ የተሰሩ የህዝብ መናፈሻዎች እንግዶች እያረፉ፣ እየተዝናኑ በእግራቸው ጉዞ እያደረጉ የሚጎበኙበትን አጋጣሚ የሚፈጥሩ ናቸው፡፡ እንደ አስጎብኚ የሚያስጎበኟቸው እንግዶች “አንድ ቀን በራሳችን አዲስ አበባን እንያት” ብለው እንደነገሯቸው ያነሱት አቶ ክብሮም፣ ከዚህ በፊት ግን አንድ ቀን ከተማዋንና የተመረጡ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ከተመለከቱ በኋላ፣ ለሁለተኛ ቀን አይቆዩም ነበር፤ ቀጥታ የተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢ የሚገኙ መስህቦችን ለማየት ነበር የሚወጡት ይላሉ፡፡
አዲስ አበባ አፍሪካ ህብረትን ጨምሮ የተለያዩ አህጉርና አለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ መሆኗ የሚያስገኘውን ዕድል በአግባቡ ሳንጠቀምበት ቆይተናል፡፡ የዓድዋ ድል መታሰቢያ መገንባቱ የተለያዩ ኹነቶችን በማዘጋጀት አፍሪካውያንንና በመላው አለም ያሉ ጥቁር ህዝቦችን በመሳብ በኮንፈረንስ ቱሪዝም ለመጠቀም የምንችልበትን ዕድል ይፈጥርልናል። በሀገር ውስጥም ሰዎች ጊዜያቸውን እየተዝናኑ ታሪካቸውን የሚያውቁበት አጋጣሚ እንደሚፈጥር አቶ ክብሮም ያነሳሉ፡፡
በአዲስ አበባ አዳዲስ መስህቦች መልማታቸው የቱሪስቶች ቆይታ እንዲራዘም ከማድረጉ ባሻገር ሌሎች ክልሎችም ትምህርት በመውሰድ የቱሪዝም መስህብ ቦታዎችንና መንገዶችን ውብና ፅዱ አድርገው እንዲሰሩ መነቃቃት ፈጥሯል፡፡ እንደ ሀገርም ሰፊ የስራ ዕድልና መልካም ገፅታ እየፈጠረ ነው። በግላቸውም ተጨማሪ ቀናት በማስጎብኘት የተሻለ ገቢ እንዲያገኙ እንዳገዛቸው ይናገራሉ፡፡
አቶ ክብሮም በማብራሪያቸው፣ አዲስ አበባ ባላት አቅም ልክ ከቱሪዝሙ የምታገኘውን ገቢ ለማሳደግ፣ የከተማንም ሆነ የሀገር መልካም ገፅታ ለመገንባት ብዙ ስራዎች ሊሰሩ ይገባል። አንደኛ ቱሪስቶች ወደ ከተማዋ ከገቡ በኋላ ከአየር መንገድ ወጥተው ታክሲ ይዘው ሆቴል እስኪደርሱ ያለው ሂደትን ቀላል ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ከሌላ ሀገር የሚመጡ፣ አዲስ እንደመሆናቸው ከአየር መንገድ ወጥተው ወዴት መሄድ እንዳለባቸው መረጃ የሚሰጣቸው አካል የለም፡፡
ከዚህ አንፃር የከተማዋ አስተዳደር ወይም የሚመለከተው ተቋም የቱሪስቶችን እንቅስቃሴ የሚከታተልና ደህንነታቸውን የሚያስጠብቅ በዘርፉ ግንዛቤ ያለው የቱሪስት ፖሊስ አይነት ማቋቋም እንደሚያስፈልግ ያነሳሉ፡፡
የመስህብ ቦታዎች ንጹህ፣ አስፈላጊው ግብአት የተሟሉላቸው እንዲሆኑ ማድረግ ሌላኛው በደንብ ሊሰራበት የሚገባው ጉዳይ እንደሆነ አቶ ክብሮም ጠቁመዋል። ለምሳሌ፡- “የሀገርን መልካም ገፅታ ሊገነቡና ሀገርን ሊያስተዋውቁ የሚችሉ ትልቅ ስም ያላቸው የውጭ ሀገር እንግዶችን የማስጎብኘት ፕሮግራም ይዘን በድንገት መብራት ጠፍቶ ለማስጎብኘት የተቸገርንበትና ያዘንንበት አጋጣሚ አለ፡፡ አንዳንዴ ደግሞ የመፀዳጃ ቤት ሲፈለግ ደረጃውን ያልጠበቀ፣ የተሰባበረ፣ ውሃ የሌለው ይሆናል፡፡ እነዚህ ጉዳዮች ጥቃቅን ሊመስሉ ይችላሉ፤ ነገር ግን በቱሪዝም ዘርፍ ትልቅ ዋጋ አላቸው፡፡ እንዲህ ዓይነት ጉዳዮችን ትኩረት በመስጠት፣ ከቱሪዝም ማህበረሰቡ ጋር በቅርበት እየተነጋገሩ፣ ባለድርሻ አካላትን እያሳተፉ በመስራት ከቱሪዝም ዘርፍ የሚገኘውን ጥቅም አሟጥጦ ለመጠቀም መስራት ይገባል።”ይላሉ፡፡
የቱሪዝም መምህርና ተመራማሪ አያሌው ሲሳይ (ዶ/ር) ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለፁት፣ በአዲስ አበባ ከነባር የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎች በተጨማሪ በቅርብ ዓመታት እየለሙ ያሉ፣ በኮሪደር ልማት ከተማዋን ፅዱና ውብ ለማድረግ እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎች በቱሪዝም መስህቦች ላይ እሴት የሚጨምሩ ናቸው፡፡ ቱሪስቶች ቆሻሻ ነገር ማየት አይወዱም፡፡ ወንዞች ቆሻሻ የሚጣልባቸውና መጥፎ ሽታ ያላቸው ከሆኑ ከተማዋን ማየት አያስደስታቸውም፡፡ ንፅህና በራሱ አንዱ የአገልግሎት አይነት ነው፡፡
የአዳዲስ የቱሪዝም መስህቦች ልማት፣ ከተማዋን በእግር ለመንሸራሸር ምቹ፣ አዲስ አበባን የኮንፈንስ ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ የሚያግዙ ናቸው፡፡ በተለይ የውጭ ቱሪስቶች ከተማዋን እረግጠው የሚያልፉ ከሆነ ቢያንስ ከተማዋንና የተመረጡ የቱሪዝም መዳረሻዎችን (በሲቲ ቱር) እንዲጐበኙ ማመቻቸት ያስፈልጋል፡፡ “በአዲስ አበባ በእግራችሁ እየሄዳችሁ አእምሯችሁን ዘና አድርጋችሁ የምትመጡበት ቦታ አለ” በማለት በአስጎብኚዎችና በኤምባሲዎች በኩል ማስተዋወቅ ይገባል፡፡ በሀገሪቱ የሚገኙ መስህቦች በሚተዋወቁባቸው መድረኮች ሁሉ በከተማዋ የሚገኙ ሀብቶችን አብሮ ማስገባትና እንዲተዋወቁ መረጃ ማድረስ እንደሚገባ የቱሪዝም መምህሩ አያሌው (ዶ/ር) ያነሳሉ፡፡
ከቱሪዝሙ ዘርፍ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ በቱሪዝም መዳረሻዎች አካባቢ የሚሰጠውን አገልግሎት ማሻሻል ላይ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል፡፡ መስህቡን በጥሬው ብቻ ማቅረብ ሳይሆን የሚበላበት፣ ከመስህቡ ጋር አብሮ ቱሪስቶችን የሚያስደስት ገንዘብ ሊያወጡ የሚችሉበት ምን መንገድ አለ? ብሎ በተጠና መንገድ መስራትን ይጠይቃል። ለምሳሌ፡- በየካ ክፍለ ከተማ የሚገኘው ከአለት ተፈልፍሎ የተሰራውን የዋሻ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ብናነሳ፣ ቱሪስቶች ለመጎብኘት ሲሄዱ በሰረገላ ብናደርገው ቦታው ምቹ ነው? የሚለውን ማየትና እንደየከባቢው ሁኔታ ቱሪስቶችን የሚስቡ፣ ቆይታቸውን አስደሳችና የማይረሳ የሚያደርጉ ነገሮችን ማየት ያስፈልጋል፡፡ አዳዲስ ሀሳቦችን ማፍለቅ ይጠይቃል፡፡ የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን እና የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ የሀገርን እወቅ ክበባትን በየትምህርት ተቋማትና መስሪያ ቤቶች በማቋቋምና በማጠናከር መስራት እንደሚጠይቅ አያሌው (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
ቢሮው ምን እየሰራ ነው?
አቶ ሳምሶን አይናቸው በአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ-ጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም መዳረሻ ልማትና የሀገር ውስጥ ቱሪዝም ማስፋፋት ዳይሬክተር ናቸው፡፡ አዲስ አበባ የዓድዋ ድል መታሰቢያን ጨምሮ 20 ሙዚየሞች፣ 22 ደረጃቸውን የጠበቁ ፓርኮች፣ ሀውልቶች፣ የገበያ ቦታዎች፣ ዋሻዎች፣ የተለያየ ኪነ ህንፃ አሻራ ያረፈባቸው ቤቶች እና ሌሎች የቱሪዝም መስህብ ፀጋዎች አላት ይላሉ፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መንግስት እንደ ሀገርና ከተማ ቱሪዝም የስራ ዕድል በመፍጠር፣ ገቢን በማሳደግ፣ መልካም ገፅታን በመገንባት የሚጫወተውን ሚና በመገንዘብ ለዘርፉ ያለውን እይታ በመቀየር በኢኮኖሚ ዘርፍ ስር እንዲሆን አድርጓል፡፡ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ከቆመባቸው ምሶሶዎች መካከልም አንዱ ሆኗል፡፡ ከአምስት ዓመታት ወዲህ በገበታ ለሸገር፣ በገበታ ለሀገር፣ ገበታ ለትውልድ የተሰሩና እየተሰሩ ያሉ የቱሪዝም መዳረሻዎች እንደ ከተማ እና እንደ ሀገር ለዘርፉ ለተሰጠው ትኩረት አንዱ ማሳያ እንደሆነ አቶ ሳምሶን ያነሳሉ፡፡
በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት የተገነቡት የአንድነት፣ እንጦጦ፣ የወዳጅነት አደባባይ ቁጥር አንድና ቁጥር ሁለት ፓርኮች፣ የሳይንስ ሙዚየም፣ የዓድዋ ድል መታሰቢያ በአዲስ አበባ ከተማ ዋነኛ የቱሪዝም መስህብ መዳረሻ ስፍራዎች በመሆን የከተማዋን ገፅታ እየቀየሩ ነው፡፡ የቱሪስት ፍሰቱን በከፍተኛ ደረጃ እንዲጨምርም አድርገዋል፡፡
በዘንድሮው ዓመትም ሰፋፊ፣ የተሽከርካሪ፣ የእግረኛና ሳይክል መንገዶችን፣ የህዝብ መናፈሻዎችንና የተለያዩ መገልገያዎችን በማካተት እየተሰራ የሚገኘው የኮሪደር ልማት የአዲስ አበባን ደረጃና ገፅታ ቀይሯል፡፡ “ልማቱ ቀጥታ ከቱሪዝም ጋርም የተገናኘ ነው” የሚሉት አቶ ሳምሶን፣ የኮሪደር ልማቱ የቱሪዝም አንድ አካል የሆነውን የእግር ጉዞ (ሀይኪንግ) ማድረግን ያበረታታል፡፡ ከዚህም ባለፈ የቱሪዝም መስህብ መዳረሻ ስፍራዎች ጎልተው እንዲታዩ፣ ማራኪና ሳቢነት እንዲኖራቸው እያገዘ ነው፡፡ አዲስ አበባ በቱሪዝም በአፍሪካ ቀዳሚ እና በዓለም ካሉ ከተሞች ጋር ተወዳዳሪ እንድትሆን ለማስቻል የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካትም ያግዛል፡፡
አቶ ሳምሶን እንደገለፁት፣ የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪጥ- ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ነባር የቱሪዝም መስህብ መዳረሻ ስፍራዎች ከማልማት አኳያ በ2016 በጀት ዓመት የተለያዩ ስራዎችን አከናውኗል፡፡ ነባር የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎች ለጉብኝት ምቹ እንዲሆኑ የጎደሉ ነገሮች እንዲሟሉ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ ተሰርቷል፡፡ ለምሳሌ፡- ወደ ፓርኮች ሲገባ መቀመጥ ያለባቸው የደህንነት ምልክቶች አልነበረም፡፡ ፓርኩ ውስጥ አንበሳ ካለ አንበሳ መኖሩን፣ ጉድጓድ እና ሌላም ካለ መኖሩን የሚያመላክት የደህንነት ምልክት ማስቀመጥ ያስፈልጋል፡፡ የመዳረሻ ቦታዎች የት እንደሚገኙ የሚያመላክቱ አቅጣጫ መጠቆሚያዎች እንዲተክሉ፣ መረጃ መስጫዎች እንዲያዘጋጁ፣ ሀብቶቻቸውን በአግባቡ እንዲከታተሉ፣ የተሻለ የማስጎብኘት አገልግሎት እንዲሰጡ ለተቋማትና አስጎብኚዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና ተሰጥቷል፡፡
በ2016 በጀት ዓመት ደቡብ አፍሪካዊው የነፃነት ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ ስልጠና በወሰዱበት የኮልፌ ፖሊስ ማሰልጠኛ ማዕከል መታሰቢያ ሙዚየም ገንብቶ ወደ ስራ ለማስገባት ታቅዶ የነበረ ቢሆንም ማሳካት አልተቻለም።
ይህም የሆነው በዋናነት ስራውን ለማከናወን የሚጠይቀውን ከፍተኛ በጀት አለመገኘት ጋር ተያይዞ ነው፡፡ የማሰልጠኛ ማዕከሉ በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ባለቤትነት የሚተዳደር ሲሆን፣ የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ- ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ቦታው የቱሪዝም መስህብ እንደመሆኑ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ለምቶ በቀጣይ ዓመት ለቱሪስቶች ክፍት እንዲሆን እንደሚሰራ አቶ ሳምሶን ጠቁመዋል፡፡
በቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎች አካባቢ የመፀዳጃ ቤት ችግር እንደሚታይ ያልሸሸጉት አቶ ሳምሶን፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም ሳይቀር በቅርቡ ለቱሪስቶች የሚሆን መፀዳጃ ቤት መገንባቱንና ሌሎችም እንዲያሟሉ ክትትልና ድጋፍ እንደሚደረግ አንስተዋል። በኮሪደር ልማቱ የተገነቡና በመገንባት ላይ የሚገኙ ደረጃቸውን የጠበቁ 120 የህዝብ መፀዳጃ ቤቶች በቱሪዝም መዳረሻዎች እና በከተማዋ ያለውን የመፀዳጃ ቤት ችግርን በማቃለል ረገድ ትልቅ ሚና እንደሚኖራቸውም ጠቁመዋል፡፡
የቱሪስቶችን ደህንነት ለማረጋገጥ የቱሪስት ፖሊስ ለማቋቋም ስራዎች ከተጀመሩ መቆየቱን ያነሱት አቶ ሳምሶን፣ በአሁኑ ወቅት የቱሪስት ፖሊስ አደረጃጀቱን ለመፍጠር ከአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ቅድመ- ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል፡፡ የቱሪስት ፖሊስ ሲቋቋም ስምሪት የሚሰጣቸው የትኞቹ ተቋማት ይሁኑ? የክፍያቸው ሁኔታስ? የሚሉትን ጨምሮ ውሳኔ የሚፈልጉ ጉዳዮች እንዳሉም አንስተዋል፡፡
“ነባር የቱሪዝም መዳረሻዎች ለቱሪስቶች ምቹ እንዲሆኑ፣ አዳዲስ መዳረሻዎች እንዲገነቡ ሲደረግ ዋነኛ ዓላማው ቱሪስቶችን በመሳብ ገቢ ለማግኘት ነው” የሚሉት አቶ ሳምሶን፣ ባለፉት ዓመታት በተሰራው ስራ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከተማዋን የሚጎበኙ ቱሪስቶች ቁጥር እና የሚገኘው ገቢ በከፍተኛ ደረጃ እያደገ መጥቷል።
በ2016 በጀት ዓመትም ከ9 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ የሀገር ውስጥ እና 928 ሺህ የውጪ ሀገር ቱሪስቶች በከተማዋ ውስጥ የሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎችን ጎብኝተዋል፡፡ ከሀገር ውስጥ ቱሪስቶች 54 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር እና ከውጭ ቱሪስቶች 59 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ወደ ከተማዋ ኢኮኖሚ ፈሰስ ሆኗል፡፡ ይህም ቱሪስቶች መዳረሻ ቦታዎች ሲገቡ ከሚከፍሉት ገንዘብ በተጨማሪ በቆይታቸው የተለያዩ አገልግሎቶችን ሲጠቀሙ የሚያወጡትን ውጪ ያካተተ ነው፡፡
አቶ ሳምሶን እንደገለፁት፣ በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባ ከመሸጋገሪያነት ወደ መዳረሻነት ተቀይራለች፡፡ በከተማዋ የሚገኙ መዳረሻ ስፍራዎች ቱሪስቶችን የማቆየት አቅም ፈጥረዋል፡፡ አንድ ቀን ሳይሆን እስከ ሶስትና አራት ቀን የሚቆዩበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡
አዲስ አበባ በልማት ውስጥ ትገኛለች። በከተማዋ ጎልተው ከወጡ የልማት ስራዎች መካከል የቱሪዝም ዘርፍ ተጠቃሽ ነው።
ቱሪዝም የከተማዋን ኢኮኖሚ በመደገፍ፣ የስራ ዕድል በመፍጠር፣ ገጽታዋን በመቀየር ከፍተኛ አቅም ያለው እንደመሆኑ፣ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማልማትና የሚሰጡትን አገልግሎት የተሟላ በማድረግ ከዘርፉ ሊገኝ የሚችለውን ጥቅም ለማግኘት መረባረብ ይገባል እንላለን፡፡
በስንታየሁ ምትኩ