
AMN ኅዳር -29/2017 ዓ.ም
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልእክት
እንኳን ለ19ኛው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን አደረሳችሁ! ብለዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አያይዘውም ኢትዮጵያ ማለት ኅብር ናት፡፡ አንድነት የሚገለጥባት ድንቅ ምድር ናት። የብሔር ብሔረሰቦች ኅብር አንድነቷን አይሸረሽረውም፤ ሀገራዊ አንድነቷ ኅብራዊነቷን አይጠቀልለውምም ብለዋል።
ሁለቱም ያስፈልጓታል። ኅብራዊነቷ ጌጧ፣ መልኳ፣ ጸጋዋ፣ ሀብቷ ነው። አንድነቷ ደግሞ ኃይሏ፣ ጉልበቷ፣ ዐቅሟ ነው።
የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀንን “ሀገራዊ መግባባት ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሀሳብ ስናከብር የኢትዮጵያን ቀለመ ብዙ ማንነት፣ እሴትና ፀጋ በማውሳት ነው። ምን ያህል የተሣሠርን፣ የተዛመድን፣ የተጋመድንና የተወራረስን እንደሆን እንማርበታለንም ነው ያሉት።
ይሄን ሁሉ ሀብት፣ ጸጋና ዕድል አውጥተን ለብልጽግና ከተጠቀምንበት የሚያደናቅፈን ዕንቅፋት ፣ የሚያሰናክለን ወልጋዳ እንደማይኖር እናረጋግጥበታለን። ሆኖም ዛሬም ድረስ ያልተሻገርናቸው ከትናንት የተሻገሩ ዕዳዎች፣ ነጠላ ትርክት የወለደው የፖለቲካ ስብራት እንዲሁም ድህነት የሀገራችንን የከፍታ ጉዞ ወደ ኋላ ጎትተዋል።
እነዚህን ሳንካዎች በማለፍ የበለፀገች፣ ጠንካራና የታፈረች ህብረ ብሔራዊት ሀገር ለመገንባት በጋራ ወሳኝ ጉዳዮች ላይ መግባባት ይገባናል።
በሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ውስጥ እምቅ ጥበብ፣ እውቀት፣ ሀገር አሻጋሪ ሀሳቦችና ባህሎች አሉ። እነዚህን እሴቶች በመደመር ለሀገር የከፍታ ጉዞ እና ለጠንካራ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት መጠቀም ያስፈልጋልም ብለዋል።
መግባባት ስንፈጥር የተደመረ አቅም ይኖረናል፤ ይህ ደግሞ ከልዩነት ፖለቲካ ወደ አንድነት ከድህነት ወደ ብልፅግና የምናደርገውን ጉዞ ያፋጥናልም ነው ያሉት በመልእክታቸው።