መጽሐፍት ለትውልድ!

May be an image of text

በዚህ ርዕስ በሳምንት አንድ ቀን ሰኞ ከቀኑ 10:00 ሰዓት ላይ ጠቃሚ ናቸው ያልናቸውን መጽሐፍት ለአንባቢ የምንጋብዝበት ነው።

የመጽሐፍቱ ምርጫ የእናንተ የውድ ተከታዮቻችንም ጭምር ነው፤ አንብባችሁ የወደዳችሁትን መጽሐፍ ብትጠቁሙን እኛም አንብበን ያላነበቡ እንዲያነብቡት መልሰን እንጋብዛለን።

ለዛሬ “25 የስኬት ቁልፎች”ን በጨረፍታ ዳስሰን ሙሉውን እንዲያነቡት ግብዣችን ነው። እነሆ!! 25 የስኬት ቁልፎች

ርዕስ-25 የስኬት ቁልፎች

ደራሲ-ኢየብ ማሞ (ዶ/ር)

የገጽ ብዛት-160

ስኬትን የማይመኝ ሰው የለም፡፡ የስኬት ትርጉም ግን አወዛጋቢ የሆነበት ወቅት ላይ ነን ያለነው፡፡ ስኬት ለሚለው ቃል ሰዎች እንደ መነሻ ሃሳባቸውና እንደምኞታቸው ትርጉሙን ይለዋውጡታል፡፡ የስኬትን ትክክለኛ ትርጉምና 25 መሰረታዊ የስኬት ጎዳናዎችን ለመገንዘብ ይህ መጽሐፍ የግድ ነው፡፡

ደራሲው በ“25 የስኬት ቁልፎች” ሲሉ በሰየሙት መጽሐፋቸው ለስኬት ወሳኝ ናቸው ያሉዋቸውን ነጥቦች በሀያ አምስት ምዕራፎች ከፍሎ አቅርቧል ፡፡

“የነፋሱ ግፊያ ወደ ከፍታዬ ያወጣልኛል” በሚለው ምዕራፍ ለስኬት የተግዳሮት አስፈላጊነት ምን ያህል እንደሆነ ጽፈዋል ፡፡ ተግዳሮትና ስኬትን በንስርና ንፋስ ንፅፅር አቅርቦልናል ፡፡

ንስር የሚጋፋው አንድ ብቸኛ ተግዳሮት ነፋስ ነው ፡፡ የሚያስገርመው ነገር ግን ንስር ወደ ከፍታው እንዲወጣ የሚደግፈውም ያው የሚጋፋው ነፋስ ነው ፡፡ የንስር አቋም “የሚጋፋኝን ይህንን ነፋስ ተጠቅሜ ወደ ከፍታዬ እበራለሁ ፤ የነፋሱ ግፊያ ወደ ከፍታዬ ያወጣኛል ፡፡” የሚል ነው፡፡ ንስር ከሚጋፋው ብቸኛ ጠላቱ ከነፋስ ተግዳሮት ውጪ ለመኖር ቢወሰንና ያንን ጥያቄውን ተግባራዊ የሚያደርግለት ኃይል ተገኝቶ ነፋስ ከፍጥረት ክስተት ውስጥ ቢወጣለት የሚጋፋው ብቸኛ ነገር ስለተወገደለት “እፎይ” ይላል ፡፡ ታሪኩ ግን እዚያ ላይ ብቻ አያበቃም ፡፡ የከፍታ ህይወቱንም እዚያው ያስረክባል ፡፡ ከሚጋፋው ከብቸኛ ጠላቱ ከነፋስ ውጪ ንስር ከዶሮ ተለይቶ አይታይም ፡፡” ይለናል መጽሐፉ፡፡

ተግዳሮት በሌለበት ስኬት አይኖርም ነው አዝማሚያው ፡፡ ስኬታማ ሰዎች ከፈተና ርቀው የኖሩ ሳይሆኑ ወርቅ በእሳት እንደሚፈተው ፤ በፈተና ተፈትነው ነጥረው የወጡ ወርቆች ናቸው ፡፡ ወርቅ እነሱ ዘንድ የሚገኘውና ብርቅና ድንቅ የሚሆኑብንም ለዚህ ነው ፡፡

ስኬታማ ሰዎች ችግሮችን እንደ ዕድሎች እንጂ እንደ ችግሮች አያዩዋቸውም ፡፡ የተከፈተ በር የተከፈተ ስለሆነ ሌላ እምቅ ዕድል በውስጡ አላዘለ ይሆናል ፡፡ የተዘጋ በር ግን የመከፈት ዕድልን የያዘ በረከት ነው ። በተከፈተው በር መግባት ስኬት ሊሆን አይችልም ፡፡ የተዘጋውን በር በብልሀት ከፍቶ መግባት ግን ስኬት ነው ፡፡ ስለዚህ ስኬት ያለው ተግዳሮት ባለበት ነው ፡፡ የንስሩ ከፍታ በሚፈታተነው ነፋስ መኖር እንደተሳካ ስኬታማነት ከችግሮት ማህፀን ይወለዳል ፡፡

“የሰውን ዘር የአምፑልን ብርሃን እንዲፈለስፍ ያነሳሳው የጨለማው ተግዳሮት መሆኑን አትዘንጋ ። የበሽታው ግፊያና የስቃያችን ጥልቀት በህክምና ዛሬ የደረስንበት ደረጃ እንድንደርስ አበረታን ፡፡ መራራቃችንና ለመገናኘት ያለን ናፍቆት የጫነብን የመገለል ጫና የበረራን ፈጠራና የስልክን መስመር የመሳሰሉትን ብልሃቶች ከውስጣችን ፈልቅቆ አወጣው ፡፡” ይላል መጽሐፉ ፡፡

“በ30 ዓመቱ ሞተ ፣ በ60 ዓመቱ ተቀበረ” በሚል ርዕስ ስር በቀረበው ክፍል ባለ ራዕይ የመሆንና በዓላማ የመፅናት አስፈላጊነት ቀርቧል ፡፡ ከዓላማ ውጪ የሚኖር ህይወት ከህይወት አይቆጠርም ፡፡ ዓላማ ቢስ ወይም ከባለራዕይነት ወደ ዓላማ የለሽነት የመጣ ሰው ኖሯል ለማለት ከባድ እንደሆነ ያትታል – ይህ የመጽሐፉ ክፍል ፡፡

“አንድ ሰው በትርፍ ጊዜው ብዙ ሙታን ወደተቀበሩበት የመቃብር ስፍራ ሄዶ በሰዎች መቃብር ላይ የተጻፉትን ጽሑፎች በማንበብ ሳይ ሳለ ፣ በአንድ ሰው መቃብር ላይ አንድ ግር የሚል ጽሑፍ አነበበ ። ጽሑፉ በ”30 ዓመቱ ሞተ ፣ በ60 ዓመቱ ተቀበረ” ይላል፡ ጽሑፉ ግር ብሎት ቆሞ ማሰላሰል ጀመረ ፡፡ “አንድ ሰው በ30 ዓመቱ ሞቶ እንዴት ለ30 ዓመታት ሳይቀበር ሊቆይ ቻለ ?” ይህንን እያሰበ የጽሑፉን ትርጉም የሚያውቅ አንድ ሰው ደረሰ ፡፡ “ምን እንደምታስብ ገብቶኛል” አለው ሃሳቡን አንብቦ ፡፡

ጥያቄውን በግምት ደርሶበት ኖሮ በቀጥታ መልሱን ነገረው ፡፡ “ይህ ሰው እጅግ በጣም የሚያስገርም ራእይና ዓላማ የነበረው ሰው ነበር ፡፡ ብዙ ነገሮችን የመስራት እቅድ የነበረውና በዚህም ትጋቱ በሕብረተሰቡ ዘንድ እጅግ የታወቀና ለትልቅ ነገር የሚጠበቅ ሰው ነበር ፡፡ ልክ 30 ዓመት ሲሞላው በተለያዩ ውጣ ውረዶች በማለፉ ምክንያት ተስፋ በመቁረጥ ዓላማውን ሁሉ ትቶ ከርታታ ሰው ለመሆን በቃ ፡፡ የሚቀጥሉትን 30 ዓመታት እንዲሁ በየቦታው ሲንቀዋለል ነው ያሳለፈው ፤ ካለምንም ዓላማ ፡፡ የጽሑፉ ትርጉም ይህ ነው ፡፡ ሰውዬው ሞተ ብለው የሚያምኑት ራእዩን በጣለበትና ጊዜውን በተራ ነገር ማሳለፍ በጀመረበት በ30 ዓመቱ ነው – በአካል ቢኖርም ሞቷል ነው አባባላቸው ፡፡ ልክ በ60 ዓመቱ ታምሞ አካላዊ ሞትን ሲሞት ያን ጊዜ ተቀበረ ማለታቸው ነው”

በአካል መኖር ብቻውን ኖሯል አያስብልም ነው ነገሩ ፡፡ ህያው የሚያደርገን ራእይና የመኖር ዓላማ እንጂ ቆሞ መሄድ አይደለም ፡፡ ቆሞ ለመሄድ በአራት እግር ሆነ እንጂ እንስሳም ይሄዳል ፡፡ እንስሳ ግን የሰውን ስራ ከማቅለሉ ውጪ የራሱ ራዕይ የለውም ፡፡ ስለሌለውም የሌሎች ባሪያ ሆኖ ይኖራል ፡፡ በሰው ራእይና ዓላማ የለሽ ህይወት ህይወት ሳይሆን ሞት ነው ፡፡ ዓላማ አልባው ሰውም ለመቀበር ነፍሱ ከስጋው እስክትነጠል ይጠበቃል እንጂ ሙትማ ሙት ነው ፡፡ ሰውን ህያው የሚያደርገው ህልሙ ነው የሚል ይመስላል ፀሐፊው፡፡

ልክ ነው ዓላማ ያለው ሰው መሆንና በዓላማው የሚፀና ሰው መሆን ሁለት የስኬት ቁልፎች ናቸው ፡፡

ስኬታማ ሰዎች ባለራዕይ ናቸው ፡፡ ለራዕያቸውም ታማኝና ፅኑ ናቸው ፡፡ ለፈተናም ሆነ ለየትኛውም ነገር በቀላሉ እጅ አይሰጡም ፡፡ እጅ አለመስጠታቸው የህያውነታቸው ምልክት ፣ የስኬታቸው ጠቋሚ ነው ፡፡

በሌላው ስለ ትኩረት ወሳኝነት በሚያወራው “እንዲያይ ሳይሆን እንዲያተኩር” በሚለው ምዕራፍ ለስኬት የትኩረትን አስፈላጊነት ያትታል ደራሲው፡፡

“25 የስኬት ቁልፎች” የተሰኘው መጽሐፍ በዚህ መልኩ የተለያዩ 25 ለስኬት አስፈላጊ ያላቸውን ነጥቦች እየዳሰሰ በ160ኛው ገፅ ላይ ያበቃል ፡፡ መጽሐፉ በየጽሑፉ መሀል የሀሳቡ መደገፊያና ማጠናከሪያ የሆኑ አባባሎችን በወሽመጥነት እያስገባ ለአንባቢያን ቀርቧል ፡፡

በሰለሞን በቀለ

All reactions:

1717

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review