መጽሐፍት ለትውልድ፣ በየሳምንቱ ሰኞ ዕለት ጠቃሚ ናቸው ያልናቸውን መጽሐፍት ለአንባቢ የምንጋብዝበት አምዳችን ነው።
የመጽሐፍቱ ምርጫ የእናንተ የውድ ተከታዮቻችንም ጭምር ነው፤ አንብባችሁ የወደዳችሁትን መጽሐፍ ብትጠቁሙን እኛም አንብበን ያላነበቡ እንዲያነብቡት መልሰን እንጋብዛለን።
ለዛሬ “አመራር A to Z”ን በጨረፍታ ዳስሰን ሙሉውን እንዲያነብቡት ግብዣችን ነው።
ርዕስ – አመራር A to Z
ደራሲ – ኢዮብ ማሞ (ዶ/ር)
የታተመበት ጊዜ – 2011 ዓ.ም
የገጽ ብዛት – 155
በሕይወታችን የአመራርን ጥበብ ካላዳበርን በስተቀር የትም መድረስ አንችልም፤ ራሳችንን፣ ቤተሰባችንን፣ ሥራችንን እና ንግዳችንን (ቢዝነሳችንን) ለመምራትም ሆነ ሕይወትህን በጣፈጠ እና በአግባቡ ወደፊት ለማራመድ መሠረታዊ የአመራር ግንዛቤ ያስፈልገናል።
ይህ መጽሐፍ ከአመራር መሠረታዊ ትርጉም በመነሳት የተለያዩ የአመራር ጥበቦችን ማንም ሊገነዘበው በሚችለው መንገድ ግንዛቤ ያስጨብጣል።
ለመቀየር እና ለመሻሻል መጣር እና ቀድሞ ለመገኘት መታገል ወሳኝነት አለው፤ መጽሐፉም የሚነግረን ይህንኑ ነው።
በተለይም አመራርነት ሲባል በተቋም ወይም በመሥሪያ ቤት ደረጃ ብቻ የሚያስፈልግ እና የሚተገበር ጉዳይ አድርገን የምንወስድ ብዙዎች ነን።
መምራት ራስን እና ከራስ ይጀምራል። ራስን በአግባቡ እና በጥበብ መምራት ቀዳሚው ነገር ነው። በመቀጠል ቤተሰብን፣ ማኅበረሰብን፣ ተቋምን፣ አገርን እያለ ይቀጥላል።
“አመራር A to Z” የተሰኘው ይህ መጽሐፍ ታዲያ አመራር እና መሪነት ምን ማለት እንደሆነ፣ እንዴት መምራት እንዳለብን ወዘተ… ይነግረናል።
መሪ ሁሉን ነገር ያውቃል ወይም ማወቅ አለበት ብሎ ማመን በፍጹም ትክክል አይሆንም። ሆኖም፣ መሪ በሚመራው ተቋም ዙሪያ በቂ እውቀት ቢያዳብር ተጽእኖውን የሰፋ ያደርገዋል።
መሠረታዊ እውቀት የጎደለው መሪ ዘወትር በሌሎች ሰዎች እውቀት ተደግፎ ከመኖሩም በላይ በሚሠራው ሥራ ዙሪያ ውጤታማነትን ለመገምገም እንኳ መሠረታዊ ብቃት አይኖረውም።
ስለእውቀት ካነሳን አይቀር ከጥንታዊ አባባል የሚከተሉትን አራት ዓይነት ሰዎች እንመልከት።
1. የማያውቅ እና እንደማያውቅ የማያውቅ ሰው ሞኝ ነውና አትከተለው ይባላል።
2. የማያውቅ እና እንደማያውቅ የሚያውቅ ደግሞ ያልበሰለ ነውና አስተምረው።
3. የሚያውቅ እና እንደሚያውቅ የማያውቅ ሰው ያንቀላፋ ኃያል ነውና ቀስቅሰው።
4. የሚያውቅ እና እንደሚያውቅ የሚያውቅ ደግሞ መሪ ነውና ተከተለው ይባላል።
ከመጽሐፉ የተወሰደ
“በዚህ ዓለም ውስጥ ልታሻሽለው እንደምትችል እርግጠኛ የሆንክለት አንድ ነገር አለ፤ እሱም ራስህን ነው።
ታላላቅ ሰዎች ካለማቋረጥ በመማር እና ራሳቸው በማሻሻል የታወቁ ናቸው። ለመሻሻል ደግሞ የተማሪነትን መንፈስ እንደያዙ መቆየት ግድ ነው።
እንደዚህ ዓይነት ሰዎች በደረሱበት ደረጃ እና እውቀት በፍጹም አይኩራሩም፤ በምትኩ፣ ‘ከዚህ በኋላ መድረስ ያለብኝ ደረጃ ምንድን ነው? ምንስ ነገር ማወቅ አለብኝ?’ በሚሉት ጥያቄዎች የተሞሉ ናቸው።
መማር እና መሻሻል ማቆም አንድ ሰው በራሱ ላይ ሊያደርስ ከሚችላቸው ከባድ በደሎች መካከል ዋነኛው ነው።
ራስን በድሎ ሌሎችንም በእርሱ ተፅዕኖ ሥር ያሉትን ሁሉ ይበድላል። የእውቀት እና የመረጃ ለውጦች እረፍት በማይሰጡበት በዚህ ዘመን ወደ ፊት አለመራመድ ማለት ወደ ኋላ መቅረት ማለት ነው።
አንድ ሰው ራሱን ካላሻሻለ ፈጠነም ዘገየ ከእርሱ በልጦ የተገኘ ሰው እንደሚተካው ሊያስታውስ ይገባል። ከዚህ ለውጥ ጋር ያልተራመደ ሰው ደግሞ የሚጠብቀው በነገሮች ሁሉ ወደ ኋላ መቅረት ነውና ላለመበለጥ እና ላለመቀደም ቀድሞ መገኘት አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው።” መልካም ንባብ!
በሰለሞን በቀለ