AMN ህዳር 16/2017 ዓ .ም
የፌደራል፣ የክልል እና የከተማ አስተዳደሮች የገቢ ተቋማት የአራት ወራት የገቢ እና የዋና ዋና ስራዎች ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ በድሬዳዋ ከተማ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
በመድረኩን የገቢዎች ሚኒስትር ወ/ሮ ዓይናለም ንጉሴ ባለፉት አራት ወራት ብር 311.56 ቢሊዮን ጥቅል ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ 312.56 ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ የእቅዱን 100.3 በመቶ ማሳካት ተችሏል ብለዋል፡፡
አፈጻጸሙም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ118.58 ቢሊዮን ብር ብልጫ እና የ61 በመቶ እድገት ማሳየቱን ገልጸዋል።
የገቢዎች ሚኒስቴር የገቢ አሰባሰብ አፈጻጸምን በመሻሻል እና ህገ-ወጥ ንግድን በመቆጣጠር በህግ የተሰጡትን ስልጣንና ኃላፊነቶች በአግባቡ መወጣት የሚያስችሉ ስትራቴጂያዊ አቅጣጫዎችን በመከተል ተግባራዊ እያደረገ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡
ሚኒስትሯ አያይዘውም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በምስራቅ አፍሪካ ትልቅ ኢኮኖሚ እንደሆነ አመልክተው ሆኖም ግን የሀገራችን ኢኮኖሚ ከሚያመነጨው ገቢ አኳያ አሁንም እጅግ አነስተኛ የታክስ ገቢ እየተሰበሰበ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ይህንን ለማሻሻል እና በገቢ አስባሰቡ የላቀ ውጤት ለማምጣትም በተቀናጀ እና በተናበበ ሁኔታ መሰራት እንዳለበት ገልጸዋል፡፡
በቀጣይም የፌዴራልና የክልል ገቢ ተቀማት የየራሳቸው ግልጽ ተልእኮ ያላቸው ቢሆንም እንደ ሃገር ለላቀ ውጤት የሚያበቃ ሥራ ለመስራት የሚከለክላቸው ነገር እንደይማኖር ጠቁመዋል፡፡
የግብር ከፋዮቻችን የታክስ ህግ-ተገዥነት ከጊዜ ወደ ጊዜ ማሻሻል እንደሚገባ እና በተጨባጭ እየተስተዋለ ያለው የታክስ ስወራ እና ማጭበርበር ልምምድን ለመቅረፍ የሚያስችል ስራ ሊሰራ እንደሚገባ ማስገንዘባቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል፡፡
ኢትዮጵያ የትሪሊዮን የሃገር ውስጥ ገቢ ጉዞ በትጋት እና በቅንጅት እውን እንዲሆን የሁላችንንም ያልተቆጠበ ጥረት ትሻለች ያሉት ሚኒስትሯ በተጨማሪም መድረኩ ቁጥሮችን ለመገምገም ብቻ ሳይሆን ጠንካራ፣ ግልጽ እና ፍትሃዊ የገቢ ስርዓትን የማጎልበት እና ወደትሪሊየን የገቢ ጉዞ መሸጋገሪያ የጋራ ተልዕኮአችንን ለማረጋገጥ ቁርጠኝነታችንን በመግለጽ ቃል የምንገባበት ይሆናል ብለዋል፡፡
All reactions:
4747