የመንግስት ኮሙኑኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ(ዶ/ር) ለሹዋሊድ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ሚኒስትሩ ያስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ ሙሉ መልዕክት እንደሚከተለው ይቀርባል፦
ባለፉት የለውጥ ዓመታት ጉዞ ውስጥ በበርካታ የአገራችን አካባቢዎች የሚገኙ የህዝባችንን መልካም እሴቶች የሚያጠናክሩ ለመጪው ትውልድ የተሻለች ሀገር መገንባት የሚያስችሉ ባህሎቻችን እና እሴቶቻችንን ከማጎልበት ረገድ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ።
በዚህ ረገድ ባለፉት ዓመታት በማይዳሰስ ቅርስነት በተባበሩት መንግታት የትምህርት የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ያስመዘገብነው የሹዋሊድ ባህላዊ ክብረ በዓል አንዱ ነው። ይህም ሐረርን በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስ የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ሁለት ቅርሶችን ያስመዘገበች ብቸኛዋ የሀገሪቱ ከተማ አድርጓታል።
ሹዋሊድ የረመዳን ፆም ተጠናቆ ኢድ አልፈጥር ከተከበረ በኋላ ስድስት ተከታታይ ቀናት ተፁሞ የሚከበር በዓል ነው።
የሹዋሊድ በዓል ከጥንት ጀምሮ በትውልድ ቅብብሎሽ ዛሬ ላይ የደረሰ ደማቅና እንደ ሌሎች በዓላት ሁሉ የኢትዮጵያዊያን የኩራት ምንጭ ከሆኑ ባህላዊ ዕሴታችን ውስጥ አንዱ ነው።
ይህ ባህላዊ በዓል በክልሉ የመቻቻል፣ የአብሮነት እና የመረዳዳት እሴትን እንዲሁም በተለይም የቱሪዝም ዘርፉን ከማጎልበት አንፃር ጠቀሜታው የጎላ ነው።
የሹዋሊድ ምሽት ሀረር የምትታወቅበት የአብሮነት እሴትም ጎልቶ የሚታይበት፤ የከተማዋ ነዋሪ የሆኑ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችም በጋራ የሚሳተፉበት ባህላዊ ክብረ በአልም ነው።
እንኳን ለሹዋሊድ በዓል አደረሳችሁ!!