ማህበራቱ ሸማቹን ከኑሮ ውድነት ምን ያህል ታድገዋል?

You are currently viewing ማህበራቱ ሸማቹን ከኑሮ ውድነት ምን ያህል ታድገዋል?

አቶ ፍስሀ ነጋ በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ቁጥር 3 አንድነት የሸማች ህብረት ስራ ማህበር ሸማች ሱቅ ሩዝ እና መኮረኒ ሲሸምቱ ነበር ያገኘናቸው፡፡ በማብራሪያቸውም፣ በሸማች ሱቆች የሚገዛው የፋብሪካም ሆነ የግብርና ውጤቶች ከነጋዴው ጋር ሲነጻጸር በዋጋም ሆነ በጥራት የተሻለ ነው፡፡ በብዛት ጠብቄም ቢሆን ግብይት የምፈጽመው በሸማች ሱቆች ነው፡፡ አሰራራቸው ወጥነት ቢኖረው የተሻለ ነው፡፡ የሚፈለጉ የፍጆታ ቁሳቁሶችን ሳይቆራረጡ ቢይዙና ማህበረሰቡን ከሚስተዋለው የኑሮ ውድነት ቢታደጉት መልካም ነው፡፡የአብዛኛው ነዋሪ ፍላጎት የሆነው ዘይት እንኳን አሁን ላይ የለም፡፡ የነጋዴው ሱቅ  ግን ሁልጊዜም ሙሉ ነው፡፡ ነጋዴው ህብረተሰቡ የሚፈልገውን ከየትም ተሯሩጦ ያመጣል። የሸማች ህብረት ስራ ማህበራትም በዚህ ልክ ማቅረብ ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡

በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ቁጥር 3 አንድነት የሸማች ህብረት ስራ ማህበር ገንዘብ ተቀባይ ወይዘሮ ሰላማዊት ይስሀቅ

በጉዳዩ ዙሪያ በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ቁጥር 3 አንድነት የሸማች ህብረት ስራ ማህበር ገንዘብ ተቀባይ ወይዘሮ ሰላማዊት ይስሀቅን አነጋግረናቸዋል። እንደሳቸው ገለጻ፤ በግል ንግድ ላይ ከተሰማሩ እና በሸማች ሱቆች ላይ ባለው የሸቀጥ  ዋጋ ልዩነት  በብዛት ነዋሪው ወደ ሸማች ሱቅ ይመጣል፡፡ የፍርኖ ዱቄት ሱቅ 100 ብር ሲሆን ሸማች ሱቅ ውስጥ 87 ብር ነው፡፡ የበቆሎ ዱቄት ዋጋ ደግሞ 50 ብር ነው፡፡ ሱቅ ግን 70 ብር ይሸጣል፡፡ ቡና ውጪ ላይ እስከ 450 ብር ሲሆን በሸማች ሱቅ ውስጥ ግን 300 ብር ነው፡፡ ቀደም ሲል ነዋሪው የሚመጣው የድጎማ ምርት እንደ ስኳርና ዘይት ለመግዛት ብቻ ነበር፡፡ አሁን ላይ ግን ልዩነቱን እያዩ ብዙ ምርቶች ለመግዛት ይመጣሉ፡፡ ነገር ግን የሚፈልገውን ሁሉ እያገኘ አይደለም፡፡ የሸማች ሱቁ አስፋልት ዳር ከመሆኑም የተነሳ የሚገቡ ምርቶች ቶሎ ቶሎ ያልቃሉ፡፡ አላፊ አግዳሚው ሁሉ ይገዛል። ምርቶቹን ቀጥታ ከገበሬው ገዝተው መሸጥ የሚችሉበት ሁኔታ ቢመቻች ደግሞ ከዚህም በላይ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል፡፡

ወይዘሮ አስናቀች ሲሳይን ደግሞ ያገኘናቸው የአንድነት የሸማች ህብረት ስራ ማህበር ባቋቋመው ወፍጮ ቤት ጤፍ ለመግዛት ሲመርጡ ነው፡፡ “በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለምንገኝ የህብረተሰብ ክፍሎች ሸማች ሱቆች እየሰጡት ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው። የወፍጮ ቤቱ ቋሚ ደንበኛ ነኝ፤ዋጋውም ከሌሎች የግለሰብ ወፍጮ ቤቶች ዋጋ ጋር ሲነጻጸር አቅምን ያገናዘበ ነው፡፡ ጥራቱም የተሻለ ነው፡፡ እንዲህ አይነት ለሸማቹ የተሟላ የሸማች ማህበራት ሱቆች በሁሉም አካባቢዎች ቢስፋፉና ህብረተሰቡን ተደራሽ ቢያደረጉ መልካም ነው፡፡ በሌሎች ወፍጮ ቤቶች በኪሎ 150 እና 160 ብር የሚሸጥ ጤፍ በሸማች ሱቁ አማካኝነት በተቋቋመው ወፍጮ ቤት ግን 121 ብር ከ50 ሣንቲም ነው፡፡” ብለዋል። አክለውም ሳሙና፣ ፓስታ፣ መኮረኒ፣ ፍርኖ ዱቄት በሸማች ሱቅ እንደሚገዙና ዘይት ግን ስለሚዘገይ በብዛት ከነጋዴ ሱቅ እንደሚሸምቱ አክለዋል፡፡

የወፍጮ ቤቱ ሂሳብ ተቆጣጣሪ ሆነው እያገለገሉ የሚገኙት ወይዘሮ ቆንጂት ታደሰ የጤፍ አቅርቦት በተመለከተ ሲገልጹ፤ በአሁኑ ወቅት በወፍጮ ቤቱ የቀረበው ጤፍ ብቻ እንደሆነ እና ጤፍ በበቂ ሁኔታ መኖሩንና የአካባቢው ነዋሪም ደስ ብሎት ገዝቶ እንደሚሄድ ተናግረዋል። እንደ ጤፉ ሁሉ የሽሮ እህልን ጨምሮ የተለያዩ ጥራጥሬዎች እንዲቀርብለት በየጊዜው እንደሚጠይቋቸውም ነግረውናል፡፡ በሸማች ማህበሩ እየቀረበ ያለው ጤፍ ከአካባቢው ነዋሪም ባለፈ ወይዘሮ ቆንጂትን ጨምሮ በሸማች ሱቁ ለሚያገለግሉ እንዲሁም ለወረዳው የመንግስት ሰራተኞችም በወፍጮ ቤቱ እየቀረበ ኑሯቸውን እየደገፈው ነው፡፡ የሚገዙትን ጤፍ በአንድ ጊዜ ለመክፈል ሳይገደዱ ከደሞዛቸው እየተቆረጠ የሚከፍሉበትም ምቹ ሁኔታ እንደተፈጠረላቸው ወይዘሮ ቆንጂት ገልጸዋል፡፡

በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 የአንድነት ሸማች ህብረት ስራ ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ምናየሁ አባቴ፤ማህበሩ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ከማድረግ አንጻር እየሰራ ያለውን ስራ በተመለከተ የጋዜጣው ዝግጅት ክፍል  አነጋግሯቸው ምላሽ ሰጥተውናል፡፡ ሥራ አስኪያጁ በሰጡት ምላሽም፤ ለምግብ ፍጆታ የሚውሉ የኢንዱስትሪና የግብርና ምርቶችን ያቀርባል፡፡ በመንግስት ድጎማ የሚቀርቡ ስኳር፣ የግብርና ምርቶችን እንደ ጤፍ፣ በቆሎ የጥራጥሬ እህሎችን እንዲሁም የፋብሪካ ምርቶችን እንደ ፍርኖና የበቆሎ ዱቄት፣ ሩዝ፣ ፓስታ፣ መኮረኒ፣ የተለያዩ የጽዳት ቁሳቁሶችን ከዩኒየን ጋር ትስስር በመፍጠር በየሸማች ሱቆቹ ለተጠቃሚው ህብረተሰብ ያቀርባል፡፡ በዋጋ ረገድም ውጪ ካለው ገበያ ጋር ሲነጻጸር ቅናሽ ነው፡፡ ለምሳሌ፡- ፍርኖዱቄት ገበያ ላይ በኪሎ በ100 ብር ሲሆን በሸማች ሱቁ ግን 87 ብር ነው፡፡ ፓስታ ሱቅ ላይ 90 እና 95 ብር ሲሆን በሸማች ሱቁ ግን ከ73 እስከ 75 ብር ድረስ ነው፡፡ የዋጋ ተመኑም አይለዋወጥም፡፡ ገበያን ለማረጋጋት በወረዳው ከሚገኙት 7 ሱቆቹ በተጨማሪ በባዛርና እሁድ ገበያዎች ላይ በመውጣት ነዋሪውን ተጠቃሚ የማድረግ ስራ እየተሰራ ነው በማለት አብራርተዋል፡፡

የሸማች ማህበራት ከሸቀጣሸቀጥ በተጨማሪ ለተጠቃሚዎች ያዘጋጁት ጤፍ፣ በቆሎና የፉርኖ
ዱቄት ተጠቃሽ ናቸው

ስራ አስኪያጁ አቶ ምናየሁ አክለውም፤ በቅርቡ መንግስት ያደረገውን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ተከትሎ ነጋዴዎች ለምግብ ፍጆታ የሚውሉ ምርቶችን በተለይም ዘይት በመደበቅ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏልና ከዚህ ጋር በተያያዘ ከሸማች ሱቆች ምን ይጠበቃል? ስንል ላነሳንላቸው ጥያቄ አቶ ምናየሁ በሰጡት ምላሽ፤ ማሻሻያው እንደተደረገ ዩኒየን ላይ ያለንን የተለያዩ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶችን አቅርበናል፡፡ 60 ኩንታል የፍርኖ ዱቄት በየሱቆቹ ለሸማቹ እንዲቀርብ ተደርጓል፡፡ ለቀጣይም ተጨማሪ 60 ኩንታል የፍርኖ ዱቄት ለመግዛት ታቅዷል፡፡ የበቆሎ ዱቄትና ጤፍ ቀርቧል፡፡ ጤፍ አሁንም አለ፡፡ እስከበዓል የሚገባ 200 ኩንታል ጤፍ ታዝዟል፡፡ ፓስታ፣  መኮረኒ እና ሩዝ የመሳሰሉ የምግብ ፍጆታዎች በበቂ ሁኔታ አቅርበናል፤ ስቶክ ውስጥም አስቀምጠናል። በወቅቱ የአካባቢው ነጋዴዎች በሸማች ሱቆች ያሉትን የተለያዩ ምርቶች ለመግዛት መጥተው ነበር፡፡ ሆኖም ከሁለትና ሶስት ፍሬ በላይ እንዳይሸጥ የማድረግ ስራ ተሰርቷል።ዘይትን በተመለከተ ለጊዜው በየሱቁ አልቋል፤ ከማሻሻያው ጋር ተያይዞ የተፈጠረውን እጥረት ለመቀነስ ግዢ ለማከናወን ክፍያ ተፈጽሟል፡፡ አገልግሎት አሰጣጡም ቢሆን ምሳ ሰአትን ጨምሮ ቅዳሜና እሁድ የሽያጭ ባለሙያዎቹ እየሸጡ ይገኛሉ። አሁን ላይ ሱቅ ዘግተው ባንክ የሚሄዱ ባለሙያዎችን ማስቀረት ተችሏል፡፡ ባንኮች ራሳቸው እየዞሩ ገንዘብ የሚሰበስቡበት አሰራር ተዘርግቷል፡፡ ከዚህ ቀደም የየእለቱን ሽያጭ ሂሳብ ለመዝጋት በሚል 10 ሰአት ላይ ካሸሮች ሱቅ ዘግተው ባንክ ይሄዱ ነበር፡፡ ይህን ክፍተትም መድፈን ተችሏል ሲሉ ነው አቶ ምናየሁ የገለጹት። 

የሸማች ሱቆች ምርት ገዝተው የሚያቀርቡት ከዩኒየኖች ብቻ ነው፡፡ ሸማች ሱቆች ከዩኒየኖች በተጨማሪ በቀጥታ ከአምራቾች ምርቶችን ገዝተው ለተጠቃሚ የሚያቀርቡበት ምቹ ሁኔታ ቢፈጠር ማህበረሰቡን በተሻለ ሁኔታ ተጠቃሚ ማድረግ ይችላሉ፡፡ እንደ ዘይት እና ጥራጥሬዎችን በበቂ ሁኔታ ከማቅረብ አንጻር ዩኒየኖች ክፍተት አለባቸው፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታትም ከከተማ እስከ ክፍለ ከተማ ህብረት ስራ ማህበራት ጋር በመነጋገር በቀጥታ ማምጣት የሚቻልበትን ሁኔታ የ90 ቀን እቅድ በማዘጋጀት ፍላጎታቸውን አሳውቀናል ሲሉም አክለዋል፡፡

ወይዘሮ ሂሩት ዘማሪያም የተለያዩ ምርቶችን ከሸማች ሱቆች እንደሚገዙ ይናገራሉ። ወይዘሮዋን ያገኘናቸው በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በእድገት ሁለገብ ሸማቾች ህብረት ስራ ማህበር ሸማች ሱቅ  ውስጥ ፈሳሽ ሳሙና እና ቡና ሲገዙ ነው፡፡ ወይዘሮዋ የእለታዊ የፍጆታ ቁሳቁሶችን ጨምሮ እንደ አቅማቸው ጤፍም የሚገዙት ከሸማች ህብረት ስራ ማህበር ነው። በሸማች ሱቁ የሚሸጡት ምርቶች ዋጋቸው ከሌላው ጋር ሲነጻጸር ቅናሽ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ዘይት ግን ቶሎ ቶሎ እንደማይመጣ ተናግረዋል፡፡

በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሁለት እድገት ሁለገብ ሸማቾች ህብረት ስራ ማህበር ሽያጭ ባለሙያ አቶ ዳግማዊ ንጉሴ ሁሉንም አይነት የፋብሪካና የግብርና ምርቶች በአንድ ላይ ማቅረብ በመቻላቸው በርካታ የህብረተሰብ ክፍል እንደሚገዛቸው ነው የሚናገሩት፡፡ እንደ ባለሙያው ገለጻ፣ አቅርቦታቸው የህብረተሰቡን ገቢ ያገናዘበ ነው፡፡ በዚህም ተመራጭ አድርጎቸዋል፡፡ ህብረተሰቡ በብዛት የሚፈልገውን እንደ ፍርኖ እና የበቆሎ ዱቄት፣ ቡና፣ ጤፍ የመሳሰሉትን እንደአቅሙ እንዲገዛ ይደረጋል፡፡ መንግስት በቅርቡ ካደረገው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ጋር ተያይዞ እንደ ከተማ በየአካባቢው ነጋዴው በተለይም የዘይት ምርት የመደበቅ ችግር ፈጥሮ በነበረበት ወቅት እንደአጋጣሚ ማህበሩም ሽጦ የጨረሰበት ወቅት ስለነበር ለህብረተሰቡ መድረስ አልተቻለም፡፡ በቀጣይ ግን ህብረተሰቡ ከመጪው በዓል ጋር ተያይዞ የመሰረታዊ ፍጆታ በዋናነት ዘይት፣ ፍርኖ ዱቄትና ጤፍ እጥረት እንዳያጋጥመው በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ህብረት ስራ ኮሚሽን ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ጥላሁን ጌታቸው፤ በከተማዋ 150 መሰረታዊ ሸማች የህብረት ስራ ማህበራት አሉ፡፡ ለእነዚህ ምርት የሚያቀርቡ በ11ዱም ከፍለ ከተሞች 11 ሸማች የህብረት ስራ ማህበራት ዩኒየኖች ይገኛሉ፡፡ ዩኒየኖቹ ክልል ከሚገኙ አምራች ህብረት ስራ ዩኒየኖች ጋር የገበያ ትስስር ፈጥረው ምርቶችን በማስገባት ነው እየሰሩ የሚገኙት፡፡ በበጀት ዓመቱ ብቻ ከ44 በላይ ከሚሆኑ አምራች ፋብሪካዎች ጋር የገበያ ትስስር በመፍጠር የፋብሪካ ምርቶችን በስፋት ማቅረብ ተችሏል፡፡ እነዚህ ማህበራት ባሏቸው ከ800 በላይ መደበኛ የመቸርቸሪያ ሱቆችና 193 በላይ የእሁድ ገበያዎች ላይ በተለያዩ በዓላት በሚዘጋጁ ባዛሮች ምርቶቻቸውን እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡ በምርት ወቅት ምርቱ ባልተገባ ሁኔታ እንዳይሰራጭና ማህበራት በሚፈለገው ልክ አከማችተው ለተጠቃሚው ህብረተሰብ ከማድረስ አንጻር ያለው ክፍተት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተቀረፈ የመጣ ቢሆንም አሁንም ደረጃውን የጠበቀ የምርት ማስቀመጫ መጋዘን ተግዳሮት አለ፡፡

ሌላው የማህበራት ተግዳሮት የፋይናንስ እጥረት ነበር፡፡ ይህንንም ችግር ለመፍታት ከተማ አስተዳደሩ የተዘዋዋሪ ብድር ፈንድ 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ፈቅዶላቸው እንደ ፍርኖ ዱቄትና ጤፍ በስፋት ገዝተው እንዲያቀርቡ አድርጓቸዋል፡፡ በተያዘው በጀት ዓመት እንኳን 3 ጊዜ አዘዋውረው 3 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ በተዘዋዋሪ ብድር ፈንድ ምርት ማቅረብ ችለዋል፡፡

አቶ ጥላሁን በማያያዝም፤ የማህበራትን የአቅርቦት አቅም በማሳደግ ረገድ ኮሚሽኑ የማህበራትን አመራሮች የመፈጸምና የማስፈጸም አቅማቸውን የማሳድግ ስራ እየሰራ ይገኛል። የህብረት ስራ አዋጅ 985/2009ን መሰረት በማድረግም የተለያዩ ደንቦችንና መመሪያዎችን በማዘጋጀት ማህበራት ለሌብነትና ብልሹ አሰራር እንዳይጋለጡ የአሰራር ስርአትም ተዘርግቷል። ከዚህ በተጓዳኝ ማህበራትን ኦዲት በማድረግ የማስተካከያ ስራ እየሰራ ነው፡፡ በቅርቡም ወደ ሪፎርም ስራ ገብቷል፡፡ ከ150 በላይ የሚሆኑ ሸማች ህብረት ስራ ማህበራት ላይ የሪፎርም ስራ ተሰርቷል፡፡ በአዳዲስ አመራር በተለይም በተማረ የሰው ኃይል እና የአገልጋይነት መንፈስ ባላቸው ግለሰቦች እንዲመራ ተደርጓል፡፡ ከቴክኖሎጂ አንጻር የተለያዩ ሶፍትዌሮችን በማበልጸግ ማህበራት የሚሰጧቸውን አገልግሎቶች ጊዜው በሚመጥን ደረጃ እንዲሰጡ የማድረግ ስራ ተጀምሯል። ማህበራት አገልግሎቱን ፍትሀዊ በሆነ መልኩ እየሰጡ መሆናቸውንም በቴክኖሎጂ ክትትል ለማድረግም በእቅድ ተይዟል፡፡ ማህበራት በ2016 በጀት ዓመት ከ11 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር በላይ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በእሁድ ገበያ እና በመደበኛ ሱቆቻቸው አቅርበዋል፡፡ ይህም በቂ ነው ማለት እንደማይችል አብራርተዋል፡፡

እንደ ሀገር ከተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ጋር ተያይዞ በከተማዋ ነጋዴዎች በፈጠሩት የምርት በተለይም ዘይት መደበቅ በአሁኑ ወቅት በሸማች ሱቆች ጭምር ካለመኖር ጋር ተያይዞ ገበያውን በማረጋጋት ረገድ ምን እርምጃ እየተወሰደ እንዳለ ለዳይሬክተሩ ላነሳንላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ ማህበራት ከሚያቀርቡት ምርት ጥራትና ዋጋ አንጻር ህብረተሰቡ በሸማች ህብረት ስራ ማህበራት የመገልገል ፍላጎቱ እያደገ መጥቷል፡፡ ኢኮኖሚያዊ አቅም ባላቸው እና በሌላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ተመራጭ እየሆነ መጥቷል፡፡ በዚህም የማህበራት የማቅረብ አቅምና የህብረተሰቡ ፍላጎት የተጣጣመ አይደለም። ይህም ሆኖ ገበያ የማረጋጋት ስራ እየሰሩ ነው፡፡ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ጋር ተያይዞ የተፈጠረው ችግር በህብረተሰቡ ላይ የምርት እጥረትና የዋጋ ንረት ይከሰታል በሚል የስነ ልቦና ጫና በመፈጠሩ በብዛት  ምርት በመሰብሰብ ነጋዴው ቀድሞ ከገዛው ዋጋ በላይ ጭማሪ አድርጎ በመሸጥ ያልተገባ ጥቅም የማግኘት ፍላጎት ማሳየታቸው ነው፡፡ ይህ ችግር በተከሰተበት ወቅትም ኮሚሽኑ ከህብረተሰቡና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ከ800 ሺህ በላይ ካርቶን ዘይት እንዲያዝ በማድረግ በሸማች ማህበራት በኩል እንዲከፋፈል ተደርጓል፡፡ ይህም ከህብረተሰቡ ፍላጎት አንጻር በቂ ባለመሆኑ አሁንም በአብዛኛው ሸማች ሱቆች የዘይት ምርት አቅርቦቱ እንዳይኖር አድርጓል። የዘይት ምርት እጥረት እንዳለ ሆኖ ምርቱ ወደ ማህበራት ይገባል ወዲያውኑ ያልቃል። ይህ ሊሆን የቻለው ማህበረሰቡ በሸማች ሱቆች የመገልገል ፍላጎት እያደገ በመምጣቱ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት የዘይት ምርት እጥረት እንዳያጋጥም ማህበራት ከፋብሪካዎች ጋር የገበያ ትስስር ፈጥረው የፓልምና ፈሳሽ ዘይቶችን እያስገቡ ይገኛሉ፡፡ ወደፊትም አቅርቦት ላይ በስፋትና በትኩረት መሰራት ስላለበት ከማክሮ ኢኮኖሚው ማሻሻያ እና በዓል ጋር በተያያዘ የምርት እጥረት እንዳያጋጥም ከዩኒየን አመራሮች፣ ስራ አስኪያጆችና ቦርድ አመራሮች ጋር አቅርቦቱ እንዴት ይሻሻል? በሚል ሰፊ ውይይት ተደርጓል፤ ስራዎችም እየተሰሩ  ነው ብለዋል፡፡

አንዳንድ ሸማቾች በፋብሪካ ምርቶች ላይ በሸማች ሱቆችና በነጋዴው መካከል ያለው የዋጋ ልዩነት ብዙ አይደለም፡፡ ለዚህ ደግሞ የግብይት ሰንሰለቱ ስለረዘመ እንደሆነ ያነሳሉ በማለት ላነሳንላቸው ጥያቄ አቶ ጥላሁን በሰጡን ምላሽ፡፡ ሁሉም ከ150 በላይ የሆኑት መሰረታዊ ህብረት ስራ ማህበራት ገበያ ፍለጋ ወደ ክልል ከወጡ ትርምስ ይፈጠራል፡፡ ራሳቸው ማህበራት በመሰረቱት ዩኒየኖች አማካኝነት ምርት እንዲያገኙ ነው አሰራር የተዘረጋው፡፡ ዩኒየኖች የተቋቋሙበት ዋና አላማ ምርት አፈላልጎና ሰብስቦ ለመሰረታዊ ማህበራት እንዲሸጡ ነው፡፡ እነሱ ይህን ማድረግ የማይችሉ ከሆነ ግን ለማህበራት ይፈቀዳል፡፡ ይሁን እንጂ ለብልሹ አሰራር በር እንዳይከፍትና ስርጭቱ ላይ ክፍተት እንዳይፈጠር እያሳወቁ መስራት ይቻላሉ። ከዚህ ባለፈ የዋጋ ልዩነቱ ትንሽ ነው ለተባለው ትክክል አይደለም። ለምሳሌ፡- ጤፍ ላይ በኩንታል ከ1 ሺህ እስከ 1 ሺህ 300 ብር ልዩነት አለ፡፡

እንደ  ዘይቱ አይነት ከ900 እስከ 1 ሺህ 20  ብር ባለፈው ሳምንት የእሁድ ገበያ ላይ ተሽጧል። በሌሎች ምርቶችም አንጻራዊ የዋጋ ልዩነት አለ። ማህበራት ምርቱ ካለበት ቦታ አስመጥተው ሸማቹን ካልተገባ የዋጋ ንረት መከላከል ላይ አላማ አድርገው የሚሰሩ ናቸው። ይህ ማለት ግን በቂ ነው ማለት አይደለም፡፡ አቅርቦት ላይ ሰፊ ስራ መስራት ያስፈልጋል፡፡ ይህም ሆኖ የማህበራት የማቅረብ አቅም ከአምናው ዘንድሮ አድጓል። ለምሳሌ አምና ከ9 ቢሊየን ብር ያነሰ ነበር፡፡ በበጀት ዓመቱ ግን ወደ 12 ቢሊየን ብር ይጠጋል ሲሉ አቶ ጥላሁን ገልጸዋል፡፡

በለይላ መሀመድ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review