ማህበራዊ ፍትህን በማረጋገጥ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነታችንን ለማረጋገጥ በትጋት እንሰራለን-ከንቲባ አዳነች አቤቤ

AMN – ታኅሣሥ 27/2017 ዓ.ም

በምግብ ዋስትና ሴፍቲኔት ፕሮግራም የስራ እድል አግኝተው ሲሰሩ የነበሩ ከተረጂነት ወደ አምራችነት የተሸጋገሩ 31ሺ 2 የከተማዋን ነዋሪዎች ከንቲባ አዳነች አቤቤ በተገኙበት ተመርቀዋል፡፡

መርሐግብሩን አስመልክተው ከንቲባዋ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባጋሩት መልዕክት ፣ የከተማዋ ነዋሪዎች ሰርቶ በመለወጥ፣ በትጋት፣ የተገኘውን እድል ወደ ድል በመቀየር፣ ኑሯቸውን በማሻሻል እና ከተረጂነት በመላቀቅ አምራች ዜጋ እና ተወዳዳሪ በመሆን ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች ዜጎች የስራ ዕድል በመፍጠር ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት ተተኪ የሌለው ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

“ከተረጂነት ወደ አምራችነት የተሸጋገራችሁ ነዋሪዎቻችን ኑሯችሁን በራሳችሁ አቅም በዘላቂነት ለመምራት በመቻላችሁ እና ለምረቃ በመብቃታችህ እንኳን ደስ አላችሁ” ሲሉም አስፍረዋል፡፡

ከጥር 1 ጀምሮ በመንግስት በጀት 154 ሺሕ ነዋሪዎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑም ነው የገለጹት ከንቲባዋ፡፡

“ማህበራዊ ፍትህን በማረጋገጥ ለብዙ ዘመን አንገት ያስደፋንን እና ለተረጂነት የዳረገንን ድህነትን በማሸነፍ በልተን ማደር ብቻ ሳይሆን የኢኮኖሚ ሉዓላዊነታችንን ለማረጋገጥ በትጋት የምንሰራ ይሆናል” ሲሉም ገልጸዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review