የመከላከያ ኢንተርፕሪነርሺፕና ኢኖቬሽን ማዕከል በመከላከያ ሠራዊት በተከናወኑ የሪፎርም ስራዎች በተመዘገበ ለውጥ የተገኘ ውጤት ነው ሲሉ የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ገለጹ።
የመከላከያ ኢንተርፕሪነርሺፕ እና የኢኖቬሽን ማዕከል የምስረታ መርሃ-ግብር ተካሂዷል።
የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በመርሃ-ግብሩ ላይ እንደተናገሩት፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት መከላከያን ሪፎርም ለማድረግ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል።

በዚህም መከላከያ ከሪፎርም ወደ ትራንስፎርሜሽን ያሸጋገረ ውጤት መገኘቱን ጠቅሰው፤ በተግባሩም የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም የሚያስከብር የመከላከያ ሠራዊት እንዲገነባ ማስቻሉን ተናግረዋል።
መከላከያ ሠራዊት በአስተሳሰቡ የተለየ እንዲሆን ዓመታትን የጠየቀ ከፍተኛ ስራ መከናወኑን ጠቁመው፤ ወደ ሪፎርም ተገብቶ በርካታ ለውጦች መገኘታቸውን ገልጸዋል።
እነዚህ ለውጦች እየተደመሩ ከሪፎርም ወደ ትራንስፎርሜሽን መድረሱንም ተናግረዋል።
ከዘመኑ ጋር እየዘመነ የሚሄድ የመከላከያ ሰራዊት ለመገንባት በተከናወነው ስራ በቴክኖሎጂ የዘመነ ሰራዊት መገንባቱን አስታውቀዋል።
መከላከያ ሠራዊትን የመለወጥ ሂደት ተጠናክሮ ቀጥሏል ያሉት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ ዛሬ የተቋቋመው ኢኖቬሽን ማዕከል የለውጡ አንዱ አካል መሆኑን ገልጸዋል።
ኢኖቬሽን ማዕከሉ ተቋሙን በቴክኖሎጂ ከማበልጸግ በተጨማሪ ለሠራዊቱ በርካታ ጠቀሜታዎች ያሉት ትልቅ ተቋም መሆኑን ተናግረዋል።

ማዕከሉ የሰራዊቱ አባል በተለያዩ ምክንያቶች ከተቋሙ ሲሰናበት የተለያዩ ስልጠናዎችን በመከታተል ራሱን እንዲችል የሚያደርግ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ሠራዊቱ በመከላከያ ተቋም ውስጥ በሚኖርበት ጊዜ ሊደገፍ፣ ኑሮው ሊስተካከል እንደሚገባ ገልጸው በሀገር አቅም ደረጃም አስፈላጊው ሁሉ ይደረግለታል ብለዋል።
ማዕከሉ ውድ ሕይወቱን ለሀገሩ እየሰዋ ያለውን መከላከያ ሰራዊት ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን አንስተው፤ በቀጣይም ሁለንተናዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተከናወነ ያለው ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
በቀጣይም ታላቅ ተቋም እንዲሆን አስፈላጊው ሁሉ ይደረጋል ማለታቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡