AMN – ጥቅምት 5/2017 ዓ.ም
ሜታ (የፌስቡክ) ኩባንያ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመሆን በኢትዮጵያ የደንበኞችን ተሞክሮ የሚያሻሽል ፕሮግራም ተግባራዊ ሊያደርግ መሆኑ ተገልጿል።
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ ከሜታ የመካከለኛው ምስራቅ እና አፍሪካ የንግድ ልማት እና ስትራቴጂክ አጋርነት ዳይሬክተር ቪካስ ሜኖን እና ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡
ውይይቶ የደንበኞችን የዲጂታል ተሞክሮ ለማሻሻል በሚረዱ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መሆኑም ተገልጿል።
በውይይቱም ሜታ ከኩባንያው ጋር በመተባበር የደንበኞችን ዳታ አጠቃቀም የሚያሻሻል (flagship) ፕሮግራም በኢትዮጵያ ለመጀመር መወሰኑን አስታውቋል።
ይህም ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ያለውን ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያያርስ ነው የተገለጸው።
ማዕቀፉ ደንበኞች አካውንታቸው ውስጥ ሂሳብ ባይኖርም የሜታ-ፌስቡክ አገልግሎቶችን ለተወሰነ ጊዜ በነጻ በመጠቀም ግንኙነታቸውን እንዲያስቀጥሉ የሚያስችል መሆኑ ተጠቁሟል።
እንደ ጤና፣ ትምህርት እና የስራ እድሎች የመሳሰሉ ጠቃሚ መረጃዎችን ከክፍያ ነጻ በማቅረብ በመረጃ የበለጸገ ንቁ ዜጋ ለመፍጠር ያስችላልም ተብሏል።
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ መርሃ ግብሩ የዲጂታል እውቀት (digital literacy) እና አካታችነትን ማሳደግ ለዲጂታል ኢትዮጵያ ግንባታ ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።
ሀገራዊ የይዘት ፈጠራ እንዲጎለብት ማድረግ እና የዲጂታል ስነምህዳሩን የሚያሻሽሉ ፕሮግራሞችን መተግበር እንዲሁም የሳይበር ደህንነት እና መረጃ አያያዝን በጋራ አስተማማኝ ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝ መናገራቸውን ከኢትዮ ቴሌኮም ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
የስምምነቱ ትግበራ የዲጂታል አገልግሎት ተደራሽነትን እና አካታችነትን በመጨመር የሀገራችንን ዲጂታል እውቀት በማሳደግ ለደንበኞች የላቀ ተሞክሮ በማምጣት ለሀገራችን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እድገት የላቀ ሚና እንደሚጫወት ተጠቁሟል፡፡