ባለፉት ስድስት ተከታታይ ዓመታት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በፈተናዎች ውስጥም ሆኖ እድገት እያስመዘገበ ቆይቷል፤ አሁንም ቀጥሏል፡፡ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ በዩክሬንና ሩስያ ጦርነት የተነሳ የምርቶች ዋጋ መናር እና መሰል ፈተናዎች የነበሩ ቢሆንም ከ2010 እስከ 2015 ባሉት በጀት ዓመታት በአማካይ የሀገር ውስጥ ምርት በ7 ነጥብ 1 በመቶ እያደገ መምጣቱን የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን በተመለከተ ካወጣው መረጃ መረዳት ይቻላል፡፡
ምንም እንኳን በተከታታይ ዓመታት የኢኮኖሚ እድገት እየተመዘገበ፣ ምርታማነት እየጨመረ ቢመጣም፣ ከፍተኛ የዋጋ ንረት፣ የገቢና ወጪ ንግድ ገቢ አለመመጣጠን፣ የውጭ ዕዳ ጫና፣ ስራ አጥነት ያሉ ችግሮች ኢኮኖሚውን ክፉኛ እየተፈታተኑ ይገኛሉ። መንግስት እነዚህን የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት ችግሮችን በመቅረፍ ቀጣይነት ያለው እድገት ለማምጣትና ተወዳዳሪ የሆነ ኢኮኖሚ ለመገንባት ያስችላል የተባለውን ሁለተኛ ምዕራፍ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ቀርፆ በቅርቡ ወደ ሙሉ ትግበራ ገብቷል፡፡
ማሻሻያው በሚቀጥሉት አራት ዓመታት ሲተገበር፤ ለማሳካት ከተያዙትና ማሻሻያው ከቆመባቸው ምሰሶዎች መካከል የሀገር ውስጥ ምርትና ምርታማነት አቅምን ማጠናከር አንዱ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ካሏት ሰፊና ለም መሬት፣ መስራት የሚችል የሰው ሀይል፣ የተለያዩ የተፈጥሮ ሀብትና ሌሎች አቅሞች አኳያ በሚፈለገው ልክ እያመረተች አይደለም። ለብዙ የሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ችግሮችም የምርትና ምርታማነት አለማደግ እንደ ምክንያት ይነሳል።
ለመሆኑ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ምን ፋይዳ ይኖረዋል? ምርታማነትን ለማሳደግ ምን ላይ በማተኮር መሰራት አለበት? በሚሉና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የዝግጅት ክፍላችን የምጣኔ ሀብት ምሁራንን አነጋግሯል፤ የተለያዩ መረጃዎችንም ዳስሷል፡፡
ማሻሻያው ለምርታማነት ያለው አበርክቶ
የውጭ ምንዛሪ ተመን በገበያ ላይ የተመሰረተ እንዲሆን መደረጉ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ ከመጡ ለውጦች መካከል አንዱ ነው፡፡ በጅማ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ዲን እና የኢኮኖሚስ ትምህርት ክፍል መምህር ለታ ሴራ (ዶ/ር) ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለፁት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አንደኛው ህመም የወጪና ገቢ ንግድ ሚዛን ጉድለት ጋር ተያይዞ ያጋጠመው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ነው፡፡
የውጭ ምንዛሪ ግብይት ገበያ መር ወይም በአቅርቦትና ፍላጎት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን መደረጉ ወደ ጥቁር ገበያ ያደላውን የኢኮኖሚ ችግር ለመቅረፍ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡ በዋናው ገበያ አንድ የአሜሪካን ዶላር 58 ብር አካባቢ እየተመነዘረ በጥቁር ገበያ ከ100 ብር በላይ ነበር። ይህም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ፍላጎት መኖሩን ያሳያል፡፡ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት አነስተኛ ከመሆኑ የተነሳ የውጭ ምንዛሪ ፈላጊዎች ወደ ጥቁር ገበያ ይሄዱ ነበር፡፡ በሀገር ውስጥ ጥቅም ላይ የሚውሉ በርካታ ምርቶች ከውጭ የሚገቡ እንደመሆናቸው በጥቁር ገበያ ምንዛሬ ተገዝተው የሚቀርቡ ምርቶች በከፍተኛ ዋጋ የሚሸጡበት፣ ህገ- ወጥነት፣ የዋጋ ንረትና ኑሮ ውድነት የተባባሰበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ከዚህ አኳያ ማሻሻያው በህጋዊና ጥቁር ገበያ መካከል ያለውን ልዩነት ለማጥበብ ያለመ እንደሆነ ለታ (ዶ/ር) ያስረዳሉ፡፡
ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ የምታገኘው ከብድር፣ እርዳታ፣ ወደ ውጭ ምርት በመላክና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከሚልኩት ገንዘብ (ሪሚታንስ) ነው፡፡ ወደ ውጭ በዋናነት እንደ ቡና፣ ሰሊጥ፣ አበባ ያሉ የግብርና ምርቶችን፣ ቆዳና የቁም እንስሳትን ትልካለች። እነዚህ ምርቶች እሴት ተጨምሮባቸው ስለማይላኩ የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ አነስተኛ ነው። በሌላ በኩል ከምግብ አንስቶ እስከ ትላልቅ የግንባታና የተለያዩ ማሽነሪዎች፣ ትራክተር፣ ኮምባይነር… ከውጭ የሚገቡና ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚጠይቁ ናቸው፡፡ ይህንን ክፍተት ኢኮኖሚው መሙላት ሲያቅተው ግብይቱ በጥቁር ገበያ ይከናወን ነበር፡፡
ምርታማነት የሚያድግበት አንደኛው መንገድ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ አልቀው (በምርት ሂደት አልፈው) እንዲላኩ ሲደረግ ነው፡፡ ለምሳሌ፡- እንደ መኮረኒና ፓስታ ያሉ ስንዴን በመጠቀም የሚዘጋጁ ምርቶች፤ ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ ይገባሉ፡፡ እነዚህን ምርቶች የስንዴን ምርታማነት በማሳደግ በሀገር ውስጥ ማምረት ከተቻለ ከውጭ የሚገቡትን በማስቀረት የንግድ ጉድለቱን መሙላት ይቻላል፡፡ ስንዴን በጥሬው ከመላክ ይልቅ ወደ ዱቄት፣ ዳቦ እና ሌሎች ምርቶች በመቀየር ለሀገር ውስጥ ገበያ ብቻም ሳይሆን ለውጭ ገበያ ማቅረብ የሚያስችል ኢኮኖሚ መፍጠር እንደሚገባ ለታ (ዶ/ር) ይናገራሉ፡፡
የውጭ ምንዛሪ ማሻሻያው በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር ቤት በጥቁር ገበያ ሲልኩት የነበረውን የውጭ ምንዛሪ በህጋዊ መንገድ እንዲልኩ ዕድል ይፈጥራል፡፡ ምክንያቱም በሁለቱ ገበያዎች መካከል ያለው ልዩነት እየጠበበ ወደ አንድ ይመጣል፡፡ በዚህ ጊዜ በባንክ የሚንቀሳቀሰው የውጭ ምንዛሪ ከፍ እንዲል በማድረግ ባንኮች ለኢንቨስትመንት የሚያበድሩትን ገንዘብ ያሳድጋል፡፡ የሚሰጠው ብድር ከፍ ማለቱ ደግሞ ኢንቨስትመንት እንዲበረታታና ምርታማነት እንዲያድግም ዕድል እንደሚፈጥር ነው የምጣኔ ሀብት ምሁሩ ለታ (ዶ/ር) የሚያስረዱት፡፡
የአምራች ዘርፉን ምርታማነት መጨመር
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ ከአለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት በብድርና እርዳታ የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ምርት ወይም ሀብት ለመጨመር ጠቃሚ እንደሆነ በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህርና ተመራማሪ ተስፋዬ ጮፋና (ዶ/ር) ይናገራሉ። የተገኘው ገንዘብ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ተደራሽ ለማድረግ፣ ለመሰረተ- ልማት ዝርጋታ፣ የኢንዱስትሪ ሽግግር ለመፍጠር ጥቅም ላይ የሚውል ከሆነ ምርትና ምርታማነት ያድጋል፡፡
አምራች ኢንዱስትሪዎች ምርት ለማምረት ከሚያስፈልጋቸው ግብአቶችና ማሽነሪዎች አብዛኞቹን የሚያገኙት ከውጭ ገበያ ነው፡፡ እነዚህን ለማምጣት የውጭ ምንዛሪ እጥረት በመኖሩ በሚፈለገው ልክ ምርታቸውን እንዳያዘምኑና በስፋት እንዳያመርቱ ማነቆ ሆኖ ቆይቷል፡፡ በሀገር ውስጥ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት መኖሩ አምራቹ ግብአቶችንና ማሽነሪዎችን በማስገባት፣ ብዙ ምርት በማምረት ለውጭና ለሀገር ውስጥ ገበያ ማቅረብ ያስችለዋል፡፡ ይህም የውጭና ገቢ ንግድ ሚዛን ጉድለቱን በመሙላትና የኑሮ ውድነትን በማርገብ የራሱ የሆነ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው የሚገልጹት ደግሞ በጅማ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህር ለታ (ዶ/ር) ናቸው፡፡
የውጭ ምንዛሪ አቅርቦቱ ምርትና ምርታማነትን ሊያሳድጉ በሚችሉ ዘርፎች ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግ እንደሚገባ በተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት የምጣኔ ሀብት ጉዳዮች አማካሪ በመሆን ያገለገሉትና በአሁኑ ወቅት በግል የፕሮጀክት ስራዎች ላይ በማማከር ላይ የሚገኙት አቶ በየነ ግዛው ይናገራሉ፡፡ “ብዙ ብድሮችን ስንፈራረም ነው የኖርነው፡፡ ዋናው ብድርና እርዳታው ከመጣ በኋላ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ለሚያስችሉ ዘርፎች እንዲውል መደረጉ ነው። ለምሳሌ፡- ማዳበሪያ ለምን በሀገር ውስጥ አናመርትም? ማዳበሪያን ማምረት ብንችል እኮ ብዙ የውጭ ምንዛሪ ገቢ መቆጠብ እንችላለን” ሲሉ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመተካት ለሚሳተፉ አምራቾች ቅድሚያ በመስጠት መስራት እንደሚገባ መክረዋል፡፡
በኢኮኖሚ ማሻሻያው ወደ ውጭ ምርቶችን የሚልኩ አምራቾች ከሚያገኙት የውጭ ምንዛሪ ውስጥ ለራሳቸው የሚያስቀሩት የውጭ ምንዛሪ ከ40 በመቶ ወደ 50 በመቶ ከፍ እንዲል ተደርጓል፡፡ በልዩ ኢኮኖሚ ዞን ውስጥ ያሉ ደግሞ ልከው የሚያገኙትን መቶ በመቶ መውሰድ ይችላሉ፡፡ ይህም አምራች ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅማቸው እንዲያድግና የስራ ዕድል መፍጠር እንዲችሉ የሚያበረታታ መሆኑን በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የግብአትና መሰረተ ልማት ዘርፍ አማካሪ አቶ ዳንኤል ኦላኒ በሚኒስቴሩ ማህበራዊ ገፅ ላይ የሰጡት ማብራሪያ ያሳያል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ከሳምንት በፊት በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አመራሮችና የንግድ ማህበረሰቡ ጋር በተደረገ ውይይት ላይ፣ “የኢኮኖሚ ሪፎርሙ በመሰረታዊነት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ የሚቀይር ነው፡፡ የውጭ ኢንቨስትመንት በተመለከተ በውጭ ባለሀብቶች የውጭ ምንዛሪ ችግር ያለባት ሀገር የሚለውን ምስል የሚቀይር ነው፡፡” ብለዋል፡፡
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አስፋው (ዶ/ር) የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን በተመለከተ የሰጡት ማብራሪያ ይህንን ሀሳብ ያጠናክራል፡፡ በሀገራችን ከ13 በላይ የመንግስት የኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ አራት አግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ፓርኮችና በርካታ የግል አምራች ኢንዱስትሪዎች ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ኢንዱስትሪዎች በውጭ ምንዛሪ እጥረት የሚፈልጉትን ግብአት ማግኘት ባለመቻላቸው በአቅማቸው ልክ አያመርቱም ነበር፡፡ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ያሉ አምራቾች ካላቸው የማምረት አቅም ከ50 በመቶ በታች ሲያመርቱ ነበር፡፡ የኢኮኖሚ ማሻሻያው ሌላ ኢንዱስትሪዎችን ማቋቋም ሳያስፈልግ ያሉትን በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ በማስቻል ምርታማነትን በከፍተኛ ደረጃ መጨመርና የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ማሳደግ እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡
ምርታማነትን ለማሳደግ ምን መሰራት ይኖርበታል?
ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር በተለያዩ ዘርፎች በርካታ ስራዎችን መስራት እንደሚገባ የምጣኔ ሀብት ምሁራን ይናገራሉ። አርሶ አደሩ ትራክተር፣ ማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘር፣ ፀረ አረምና ፀረ ተባይ መድሃኒት ያሉ የግብርና ቴክኖሎጂና ግብአቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ በሰፊው ተደራሽ ማድረግ ምርታማነትን የማሳደጊያ አንዱ መንገድ እንደሆነ በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህርና ተመራማሪ ተስፋዬ ጮፋና (ዶ/ር) ይናገራሉ፡፡
በአነስተኛና በተበጣጠሰ ማሳ ከማምረት ይልቅ፤ አርሶ አደሮች ያላቸውን መሬት የግብርና ቴክኖሎጂዎችንና ግብአቶችን በጋራ ተጠቅመው (በክላስተር) ቢያመርቱ ምርታማነትን እንደሚጨምር የምጣኔ ሀብት ምሁሩ ያነሳሉ፡፡
“ግብርናውን ለማሳደግ፣ ግብርናው ለማደግ ምን ይፈልጋል? የሚለውን ማየት ይፈልጋል፡፡” የሚሉት የምጣኔ ሀብት ጉዳዮች አማካሪ አቶ በየነ በበኩላቸው፤ በዘርፉ መሰማራት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች የንግድ ፈቃድ ከማውጣት ጀምሮ እንደ መሬትና ብድር አቅርቦት እና የታክስ እፎይታ ያሉ ንግድን ለመጀመር የሚያስፈልጉ ምቹ ከባቢያዊ ሁኔታዎችን መፍጠር (Ease of Doing Bussiness) ያስፈልጋል፡፡
ለምሳሌ ለኢንቨስትመንት መሬት ከማግኘት ጋር ተያይዞ በክልሎች አካባቢ ችግሮች ይታያሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ባለሀብቶች ወደ አንድ አካባቢ ሄደው መዋዕለ ንዋያቸውን አፍስሰው፣ የስራ ዕድል ፈጥረው ሲሰሩ “ይኼ እኮ የእኔ አካባቢ ነው፤ እንዴት መጣህ” በማለት ባለሀብቶችን ስጋት ላይ የሚጥሉ እንቅስቃሴዎች ይስተዋላሉ፡፡ ከባለሀብቶች ጋር በተያያዘ በክልሎች ያለው አሰራር ምን ያህል ቀላልና ምቹ ነው? የሚለውን መፈተሽ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ አኳያ ባለሀብቱ በቀላሉ መሬት አግኝቶ ሳይረበሽና ተረጋግቶ እንዲያመርት ዋስትና የሚሰጥ አሰራር መፍጠር እንደሚገባ አቶ በየነ ይመክራሉ፡፡
የምጣኔ ሀብት ምሁራኑ እንደሚናገሩት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በመስኖ የሚታረሰውን መሬት ማሳደግ ላይ መስራት ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ በመስኖ መልማት የሚችል ብዙ መሬት እያላት ጥቅም ላይ ያዋለችው በጣም አነስተኛ ነው፡፡ በመስኖ የሚለማውን መሬት በማሳደግና የመስኖ ልማት በተጀመረባቸው አካባቢ ያሉ የአጠቃቀም ክፍተቶችን በማሻሻልና በሙሉ አቅም በመስራት በዓመት ሁለት ጊዜና ከዚያ በላይ ማምረት ይቻላል፡፡ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር በ2015 በጀት ዓመት በዓለም ባንክ ድጋፍ በሰራው ጥናት መሰረት ኢትዮጵያ በመስኖ ሊለማ የሚችል 10 ሚሊዮን ሄክታር መሬት አላት፡፡ ከዚህ ውስጥ በመስኖ የለማው ከአስር በመቶ በታች እንደሆነ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
አርሶ አደሩ ያመረተውን ምርት ወደ ገበያ፣ ከተሞችና አምራች ኢንዱስትሪዎች ማቅረብ እንዲችል የመንገድና ትራንስፖርት ተደራሽነትን ማሳደግ ሌላኛው ምርታማነት እንዲጨምር እንደሚያደርግ ነው ተስፋዬ (ዶ/ር) ያብራሩት፡፡
ምርታማነትን የማሳደግ ስራው፤ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት፣ ወደ ውጭ የሚላኩትን በዓይነት፣ መጠንና ጥራት በማሳደግ ላይ ያተኮረ መሆን እንዳለበት የምጣኔ ሀብት ምሁራን ያስረዳሉ፡፡ ኢትዮጵያ ከግብርና እስከ ኢንዱስትሪ በርካታ ምርቶችን ከውጭ ታስገባለች፡፡ ለምሳሌ እንደ ሩዝ፣ ስንዴ፣ የፍራፍሬ፣ የእንጨት ውጤቶችና ሌሎች ምርቶች ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ ይገባሉ፡፡ እነዚህን በሀገር ውስጥ በሰፊው ማምረት ላይ መስራት፣ የግብርና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችንና የስልጠና ማዕከላትን በአግባቡ መጠቀም፣ አርሶ አደሩ ለሚያመርታቸው ምርቶች የገበያ ትስስር መፍጠር ይገባል፡፡
ወደ ውጭ የሚላኩ የግብርና ምርቶችንም ቢሆን፤ በጥሬው ከመላክ ይልቅ እሴት በመጨመር መላክ ላይ መስራት ያስፈልጋል። ለምሳሌ:- ደቡብ ኮሪያ ከኢትዮጵያ ቡና በመግዛት ተጨማሪ እሴት በመጨመር ትልቅ ቡና ላኪ ከሚባሉ ሀገራት አንዷ መሆን ችላለች። እኛስ ለምን አናደርግም? የሚለውን በደንብ ማሰብ፣ አስቦም መስራት እንደሚገባ የምጣኔ ሀብት ምሁሩ ተስፋዬ (ዶ/ር) ይናገራሉ፡፡
ይህንን ሀሳብ የሚጋሩት የምጣኔ ሀብት ጉዳዮች አማካሪ አቶ በየነ ለምሳሌ የጨርቃ ጨርቅ ዘርፍን ብንወስድ አሁንም ግብአቶቹ ከውጭ ነው የሚገቡት፡፡ ለጥጥ እርሻ የሚሆን መሬት በአፋርና ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎችና ሌሎች አካባቢዎች ያለ ቢሆንም አሁንም ጥጥ ከውጭ የምናስገባው ለምንድን ነው? የሚለውን በጥናት ማየት ይገባል፡፡
በኢንዱስትሪ ዘርፍ ያለውን ምርታማነት ለማሳደግ ዘርፉ የሚፈልገውን ብቃት ያለውና የሰለጠነ የሰው አቅም መገንባት፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም፣ ጎን ለጎንም የሰው ሀይሉ ጉልበቱ እንዳይበዘበዝና እንዲተጋ የሚበረታታበትን ሁኔታ በመፍጠር መስራት እንደሚገባ ተስፋዬ (ዶ/ር) ያነሳሉ፡፡
ሌላው ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ሰላምና መረጋጋት መፍጠር ወሳኝ እንደሆነ የምጣኔ ሀብት ምሁራን ያስረዳሉ። ኢንቨስተሮች በሰላም ከቦታ ወደ ቦታ ተንቀሳቅሰው መስራት የሚችሉበት ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ኢንቨስተሮች ወደ ሀገር ቤት ሲመጡ ቢያንስ አምስትና አስር ዓመት ያለምንም ችግር ስራ መስራት የሚችሉበት ምቹ ሁኔታ ስለመኖሩ ዋስትና ይፈልጋሉ፡፡ በዚህ ረገድ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩ የሰላምና ፀጥታ ችግሮች እልባት ማግኘት እንዳለባቸው ነው ተስፋዬ (ዶ/ር) የሚያስረዱት፡
ሙስና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ማነቆ በመሆኑ የሙስናና ብልሹ አሰራሮችን እያረሙ መሄድ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ የምጣኔ ሀብት ምሁሩ ተስፋዬ (ዶር) ያነሳሉ። ለምሳሌ፦ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ተገዝቶ የገባ ማዳበሪያ በቀጥታ ለአርሶ አደሩ በማድረስ ረገድ ክፍተቶች እንዳሉ ይነሳል፡፡ ታች ያለው አስተዳደር በቀጥታ ለአርሶ አደሩ ከማድረስ ከነጋዴዎች በመሻረክ ያለአግባብ ጥቅም ለማግኘት ሲሞክር ተስተውሏል፡፡ እንደዚህ ዓይነት ብልሹ አሰራሮችን እየቀረፉ መሄድ ያስፈልጋል፡፡
ከአስር ያላነሱ የስኳር ፋብሪካዎች እየተገነቡ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡ እነዚህ ፋብሪካዎች ምን ያህሉ ግንባታቸው አልቆ ወደ ስራ በሙሉ አቅማቸው እያመረቱ ነው? የሚለውን እንደገና መፈተሽ እንደሚገባ የምጣኔ ሀብት ጉዳዮች ባለሙያው ያነሳሉ፡፡
ምርታማነትን ለማሳደግ በቅርብ ዓመታት መንግስት የበጋ መስኖ የስንዴ ልማትን በማስፋፋት እየሰራቸው ያሉ ስራዎች ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን ያነሱት አቶ በየነ ከመንግስት ባሻገር የግሉ ዘርፍ በስፋት የሚሳተፍበት ሁኔታ ቢፈጠር ምርታማነት የበለጠ ሊያድግ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡
አቶ በየነ እንደሚሉት፣ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የአንድ ተቋም ኃላፊነት ብቻ አይደለም፡፡ በዚህ ረገድ የኢኮኖሚ ማሻሻያውን “የእኔም ጉዳይ ነው፤ የሚመጣው ኢንቨስትመንት የእኔ ነው፤ እኔና ቤተሰቦቼ ስራ እናገኝበታለን፤ ያገኙበታል፤ የሀገሬን ኢኮኖሚ ይደግፋል” ብሎ ማህበረሰቡ እንዲደግፈው ፖሊሲውን በደንብ ማሳወቅና ማስረፅ ያስፈልጋል፡፡
ማሻሻያውን ተከትሎ ምርቶች ላይ የሚስተዋሉ የዋጋ ጭማሪዎች በአጭር ጊዜ የኑሮ ውድነቱን በማባባስ ፈተና መጋረጣቸው እንደማይቀር የሚያነሱት ለታ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በረጅም ጊዜ ነጋዴው ማህበረሰብ ከመንግስት ጋር አብሮ ከሰራ፣ ማህበረሰቡም ማሻሻያው ወደ ፊት የሚያመጣውን ጥቅም ተገንዝቦ በስራ ከተጋ፣ ስንፍናንና ሙስናን ከተጠየፈ፣ ሰላሙን መጠበቅ ከቻለ መንግስት አርቆ ያየውን የበለፀገች ኢትዮጵያን የመፍጠር ርዕይ እውን ማድረግ ይቻላል፡፡
በስንታየሁ ምትኩ