ምክር ቤቱ የአረንጓዴ አሻራና የተጎሳቆለ መሬት ማገገሚያ ልዩ ፈንድ ማቋቋሚያና አስተዳደር አዋጅን አጸደቀ

AMN-ታህሣሥ 15/2017 ዓ.ም

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርን ውጤታማ በሆነ መልኩ ያስችላል የተባለውን የአረንጓዴ አሻራና የተጎሳቆለ መሬት ማገገሚያ ልዩ ፈንድ ማቋቋሚያና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅን በሙሉ ድምፅ አጸደቀ።

በምክር ቤቱ 12ኛ መደበኛ ስብሰባ የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ደሳለኝ ወዳጆ አዋጁን የተመለከተ ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ አቅርበዋል።

አዋጁ በኢትዮጵያ የተጀመረውን የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ውጤታማና ቀጣይነት ባለው መልኩ ለመምራት በልዩ ፈንድ እንዲደገፍ የሚያስችል መሆኑ ተጠቅሷል።

አቶ ደሳለኝ ባለፉት ስድስት ዓመታት የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ የተጎሳቆለ መሬት እንዲያገግም ከማድረግ አኳያ ጉልህ ሚና ማበርከቱን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በደን ዘርፍ ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ምንጮች የምታገኘውን ጥቅም ለማሳደግ ከማስቻል ባለፈ መንግስት ለመርሐ ግብሩ ተገቢውን በጀት እንዲመድብ የሚያስችል መሆኑንም ጠቁመዋል።

በአዋጁ መንግስት በየዓመቱ ከሚመድበው ከጠቅላላ በጀት ከ0 ነጥብ 5 እስከ 1 በመቶ የሚሆን በጀት ለልዩ ፈንዱ የሚመድብ ሲሆን ክልሎች በራሳቸው አቅም ልክ በጀት ሊመድቡ እንደሚችሉ ተመላክቷል።

ገንዘብ ሚኒስቴር ፈንዱን እንደሚያስተዳድረውም ማመላከቱን ኢዜአ ዘግቧል።

ምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴው የሚያቀረበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ መርምሮ አዋጁን እንደሚያፀድቅም ይጠበቃል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review