ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ረቂቅ አዋጅን መርምሮ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መራ

You are currently viewing ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ረቂቅ አዋጅን መርምሮ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መራ

AMN – መጋቢት 9/2017 ዓ.ም

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 20ኛ መደበኛ ስብሰባ የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ረቂቅ አዋጅን መርምሮ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።

በምክር ቤቱ የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) ረቂቅ አዋጁን አስመልክቶ አጭር ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር የቅድመ አደጋ፣ የአደጋ ወቅት እና ድህረ አደጋ ተግባራትን ውጤታማ ለማድረግ የፌደራል እና የክልል አስተዳደር ተቋማት የውስጥ አቅም ለመገንባት መዘጋጀቱን አመላክተዋል፡፡

ቅጽበታዊ አደጋ ሲከሰትና ከአቅም በላይ ሲሆንም የአስቸኳይ ጊዜ እወጃ ስርአት ለመዘርጋትና ተግባራዊ ለማድረግ እንዲሁም የሰብአዊ ድጋፍ፣ የዘላቂ ልማት እና የሰላም ግንባታ እቅዶችን ለማስተሳሰር የሚያስችል የተሟላ የህግ ማዕቀፍ ለመዘርጋት እንዲያስችል የተዘጋጀ ረቂቅ አዋጅ መሆኑን ገልጸዋል።

ረቂቅ አዋጁ የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ምክር ቤት መቋቋምን የተመለከቱ ድንጋጌዎች እና ስለ ኮሚሽኑ ተግባር እና ኃላፊነት የምክር ቤቱ ስልጣንና ተግባራት፣ ስለፌደራል መሪ ዘርፍ ተቋማት እና የክልል መንግስታት ተግባርና ኃላፊነት እንደተካተቱበት ተገልጿል፡፡

ስለአደጋ ተጋላጮችና ተጎጂዎች መብትና ግዴታ እንዲሁም ስለ ኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ምላሽ ፈንድ መቋቋም የሚመለከቱ እና ሌሎች ድንጋጌዎች መካተታቸውን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

አዋጁ የሚደረጉ ድጋፎች በተቀናጀ መልኩ እንዲደረጉና ለተጎጂዎች እኩል ተደራሽ ለማድረግ እንዲሁም ከእርዳታ ጠባቂነት በመላቀቅ እራስን ለመቻል አስፈላጊ መሆኑን የምክር ቤት አባላትም አመላክተዋል።

ረቂቅ አዋጁ የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 16/2017 ሆኖ በሙሉ ድምጽ ለውጭ ግንኙነት እና ለሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር እይታ መመራቱን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review