AMN – ታኅሣሥ 8/2017 ዓ.ም
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ11ኛ መደበኛ ስብሰባው፤ የፋይናንስ ስርዓቱን ለማሳለጥ የሚያግዝ ረቂቅ አዋጅ መርምሮ በሙሉ ድምጽ አጸድቋል፡፡
የፕላን፤ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ወዳጄ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ረቂቅ አዋጅን ሪፖርት እና የውሳኔ ሃሳብ ለምክር ቤቱ አቅርበዋል፡፡
በዚሁ ወቅት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ረቂቅ አዋጅ ባንኩ ዋጋን ለማረጋጋት፤ ጤናማ የፋይናንስ ስርዓት ለማስፈንና ለኢኮኖሚው ዕድገት መፋጠን እና ተልዕኮውን በአግባቡ ለመወጣት እንደሚረዳው አስረድተዋል፡፡
የሀገርን ኢኮኖሚ ለማሻሻል ምርታማነትን ለማሳደግ፣ ቁጠባና ኢንቨስትመንትን ለማጠናከርና ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሞችን ለመተግበር ረቂቅ አዋጁ የሚያግዝ መሆኑን የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አስገንዝበዋል፡፡
ብሔራዊ ባንክ ከብድር ዋስትና አሰጣጥ እና መመሪያን ከማዘጋጀት እንዲሁም ባንኮችን ከመከታተልና ከመቆጣጠር እንጻር ኃላፊነትን ባገናዘበ መልኩ ማየት እና መረዳት እንዳለበት የምክር ቤቱ አባላት አንስተዋል፡፡
አክለውም ባንኩ አሰራሩን በማዘመን እና ተወዳዳሪ ሆኖ እንዲቀጥል ለማድረግ ረቂቅ አዋጁ የሚያግዘው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምህረቱ ዋጋን ለማረጋጋት፤ የፋይናንስ ስርዓቱን ለማዘመን እና በሀገራችን ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት ረቂቅ አዋጁ እንደሚያግዝ አስረድተዋል፡፡
ረቂቅ አዋጁ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ ልምድና ተሞክሮዎችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ የተዘጋጀ መሆኑን ጠቁመው፤ በኢኮኖሚው ዘርፍ ተወዳዳሪ እና እምርታዊ ለውጥ ለማምጣት አቅም የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የዓለም የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተለዋዋጭ በመሆኑ ይህን ታሳቢ ያደረገ መመሪያና አዋጅ በማውጣት ተወዳዳሪ ለመሆኑ ጊዜው ያስገድዳል ሲሉ መግለፃቸውን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ምክር ቤቱ የቀረበለትን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ረቂቅ አዋጅ፤ አዋጅ ቁጥር 1359/2017 አድረጎ በሙሉ ድምጽ አጸድቋል፡፡