ምክር ቤቱ የፌዴራል የህግና ፍትህ ኢንስቲትዩት ማቋቋሚያ አዋጅን አፀደቀ
AMN – ጥር 29/2017 ዓ.ም
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 18ኛ መደበኛ ስብሰባ የፌዴራል የህግና ፍትህ ኢንስቲትዩት ማቋቋሚያ አዋጅን አጽድቋል።
በምክር ቤቱ የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እጸገነት መንግስቱ አጠቃላይ ሪፖርቱንና የውሳኔ ሀሳቡን አቅርበዋል።
ሰብሳቢዋ በዚህ ወቅት እንደገለጹት ጠንካራ የህግና ፍትህ ኢንስቲትዩት መገንባት በእውቀቱ፣ በአመለካከቱና በስነምግባሩ ብቁና የተሟላ ስብዕና ያለው የዳኝነትና የፍትህ ባለሙያ ለማፍራት ያግዛል።
በጥናትና ምርምር እንዲሁም በቴክኖሎጂ የታገዘ ዘመናዊና ቀልጣፋ የፍትህ አገልግሎት ለመስጠትም ሚናው የጎላ መሆኑን አብራርተዋል።
ህጎችን ከወቅታዊ ሁኔታ፣ ከአለምና የአገሪቱ የዕድገት ደረጃ ጋር እንዲጣጠሙ ለማድረግ ጠንካራ የህግና ፍትህ ኢንስቲትዩት መገንባት አስፈላጊና ተገቢ መሆኑንም ገልጸዋል።
የዳኝነት አካሉ ነጻነትና ገለልተኛነት የበለጠ ለመጠበቅ ሲባል ኢንስቲትዩቱ እንደገና ማቋቋም አስፈላጊ መሆኑንም አመልክተዋል።
ገለልተኛ በሆነ መልኩ የህግና ፍትህ ኢንስቲትዩት በማቋቋም ጠንካራ የዳኝነትና የፍትህ ተቋማት ለመፍጠር የህግና ፍትህ ኢንስቲትዩትን ተጠሪነት ማሻሻል ተገቢ መሆኑንም መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ረቂቅ አዋጁ ነጻና ገለልተኛ የፍትህ ስርዓት ለመፍጠርና ህዝቡ በፍትህ አሰጣጥ ላይ ያለውን እርካታ ለመጨመር ያግዛል ብለዋል።
ምክር ቤቱ የፌዴራል የፍትህና ህግ ኢንስቲትዩት ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ውይይት ካደረገ በኋላ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።