ዛሬ ከአዘርባጃን የፐብሊክ ሰርቪስ እና ማኅበራዊ ፈጠራ ተቋም ሊቀ መንበር ኦልቪ ሜዲዬቭ እና በኢትዮጵያ የአዘርባጃን አምባሳደር ሩስላን ናሲቦቭ ጋር ኢትዮጵያ እና አዘርባጃን በጋራ በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸውን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገልጸዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎቹ በቅርቡ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት የሆነውን ሞሰብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን መጎብኘታቸውን አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ ይህን አገልግሎት በማስጀመር የሲቪል ሰርቪስ አገልግሎትን ለማዘመን እና ለማቀላጠፍ እያከናወነች ያለችው ተግባር የሚበረታታ መሆኑን መናገራቸውንም ጠቁመዋል።
በተጨማሪም ሊቀ መንበሩ ከሁለት ዓመት በፊት ኢትዮጵያን ሲጎበኙ ያዩት የአዲስ አበባ ከተማ ገፅታ በእጅጉ የተለወጠ መሆኑ እንዳስገረማቸው መናገራቸውን ገልጸዋል።
በብሔራዊ ቤተመንግሥት በመገኘትም የኢትዮጵያን ታሪካዊ እሴቶች የሚያሳየውን ሙዚየም እንደጎበኙ ነው ያነሱት።
በስፍራው የተመለከቷቸው ነገሮችም እጅግ አስደናቂ መሆናቸውን እንደተናገሩ ገልጸዋል፡፡