AMN – ጥር 8/2017 ዓ.ም
በማእከላዊ ዕዝ የጊቤ ኮር በተሰማራበት ምእራብ ወለጋ ዞን ሠላም ያልተቀበለውን ሸኔ በመደምሰስ ዞኑን ወደ ሰላማዊ ሁኔታ መመለሱን የምእራብ ወለጋ ዞን ኮማንድ ፖስት አስተባባሪ ሜጄር ጄኔራል ኩመራ ነጋሪ ገልፀዋል።
በምእራብ ወለጋ ዞን ጊሊሶ ወረዳ ነዋሪዎች ከጊዚያዊ ኮማንድ ፖስቱ ሃላፊዎች ጋር ባደረጉት ውይይት የሰላምን አማራጭ ባልተቀበሉ የሽብር ቡድኑ አባላት ላይ እየተወሰደ ባለው እርምጃ በአካባቢው አሁን ያለው የሰላም ሁኔታ አስተማማኝ መሆኑን ተናግረዋል።
በቀጣይ ለሚወሰዱ እርምጃዎች ከሠራዊቱ ጎን በመቆም የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚያበረክቱ ነዋሪዎቹ መግለፃችውን የዞኑ ኮማንድ ፖስት አስተባባሪ ሜጄር ጄኔራል ኩመራ ነጋሪ ገልፀዋል።
ብርጋዲየር ጄኔራል ተገኝ ለታ በበኩላቸው በምእራብ ወለጋ ዞን መነሲቡ ወረዳ እና መንዲ ከተማ ነዋሪዎች ጋር የአካባቢውን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ህዝባዊ ውይይት አድርገዋል።
ነዋሪዎች ሠራዊቱ ከህዝብና ከፀጥታ አካላት ጋር በመሆን የሰላምን አማራጭ ባልተቀበሉ የአሸባሪው ሸኔ ቡድን ላይ እየወሰደው ባለው እርምጃ በአካባቢው አስተማማኝ ሰላም መፈጠሩን ተናግረዋል።
በተካሄደው ህዝባዊ ውይይት ከፍተኛ የሠራዊቱ አመራሮች የዞን እና የወረዳ አስተዳደሮች እንዲሁም የፀጥታ ሃይል አመራሮች መሳተፋቸውን ከመከላከያ ሰራዊት የማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።