ሠራዊቱ ከፀጥታ ኃይሎች ጋር ተቀናጅቶ ባከናወነው ስራ በክልሉ አንፃራዊ ሰላም ሰፍኗል – አቶ አሻድሊ ሀሰን

You are currently viewing ሠራዊቱ ከፀጥታ ኃይሎች ጋር ተቀናጅቶ ባከናወነው ስራ በክልሉ አንፃራዊ ሰላም ሰፍኗል – አቶ አሻድሊ ሀሰን

AMN- መስከረም 27/2017 ዓ.ም

የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከፀጥታ ኃይሎች ጋር ተቀናጅቶ ባከናወነው ስራ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አንጻራዊ ሰላም መስፈኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ገለጹ።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እና አጎራባች ቦታዎች የተገኘውን አንፃራዊ ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ ያለመ ውይይት ተካሄዷል።

በውይይቱ ላይ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እና የሠራዊቱ አመራሮች ተገኝተዋል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እና አጎራባች ክልሎች በሕገ ወጥ ታጣቂዎች ተፈጥረው የነበሩ ችግሮችን ለማስተካከል በተሰራው ስራ ሰራዊቱ መስዋዕትነት ከፍሎ አካባቢው እንዲረጋጋ ማድረጉን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሃሰን ገልጸዋል።

ማህበረሰቡን የሰላም ተሳታፊ በማድረግ በሰላምና ፀጥታ ላይ ውይይት በማከናወን ሲከሰቱ የነበሩ ችግሮችን ማስተካከል መቻሉንም አመልክተዋል።

ክልሉ እንደታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ያሉ የኢትዮጵያ ግዙፍ ፕሮጀክት የሚገኝበት በመሆኑ በቀጣናው የሚከናወን የልማት ስራ በውጭና በውስጥ ጠላቶች እንዳይደናቀፍ በተስራው የተቀናጀ ስራ ስኬታማ ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል።

የምዕራብ ዕዝ ምክትል አዛዥ ለውጊያ ድጋፍ አገልግሎት ሜጄር ጀኔራል ሙላት ጀልዱ፤ በቀጣናው የተፈጠረውን አንፃራዊ ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ እንደ ወትሮው ሁሉ ሁሉም የፀጥታ ኃይሎች እና የፖለቲካ አመራር በቅንጅት በመስራት እና በአጭር ጊዜ አካባቢውን ከፀረ ሰላም ኃይሎች በማፅዳት ክልሉ ራሱ የሚረከብበትን ጠንካራ ስራ መስራት ይገባል ብለዋል።

ሕዝቡ ሰላሙ ተጠብቆ በሀገሪቱ በሚከናወኑ ልማቶች ተጠቃሚ እንዲሆን በቀጣናው አልፎ አልፎ የሚንቀሳቀሱ የሸኔ ሽብር ቡድንና ፅንፈኛውን ሀይል ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ስር ማዋል ይገባል ማለታቸውን ከመከላከያ ሰራዊት የማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review