ሩሲያ በብሪክስ የትብብር ማዕቀፍ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን አጋርነት ታጠናክራለች

You are currently viewing ሩሲያ በብሪክስ የትብብር ማዕቀፍ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን አጋርነት ታጠናክራለች
  • Post category:ዓለም

AMN – ሐምሌ 4/2016 ዓ.ም

ሩሲያ በብሪክስ የትብብር ማዕቀፍ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን አጋርነት ይበልጥ አጠናክራ ለመቀጠል እንደምትሰራ በኢትዮጵያ የሀገሪቱ አምባሳደር ኤቭጌኒ ቴርኪን ተናገሩ። 

አምባሳደር ኤቭጌኒ ቴርኪን እንዳሉት ኢትዮጵያ ብሪክስን ከተቀላቀለች ጀምሮ በሚደረጉ ሁነቶች እያደረገች ያለው የነቃ ተሳትፎ የሚደነቅ ነው።

ሩሲያ የተያዘው የፈረንጆች ዓመት የብሪክስ ሊቀመንበር መሆኗን አስታውሰው፤ ጥምረቱን ማጠናከር የሚያስችሉ የተለያዩ ሁነቶችን እያካሄደች መሆኗን ጠቁመዋል።

ለአብነትም በቅርቡ የብሪክስ አባል ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን ጨምሮ የሌሎች ተቋማት ተወካዮች በሩሲያ ሞስኮ ከተማ ስብሰባ መካሄዱን ገልፀዋል።

በዚህም ስብሰባ ኢትዮጵያ ውጤታማ ተሳትፎ ማድረጓን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በሙያተኞችና ሚኒስትሮች ደረጃ የምታደርገው ተሳትፎ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያሳድግ እንዲሁም ብሪክስን የሚያጠናክር መሆኑን ነው ያስረዱት።

ኢትዮጵያ በብሪክስ እያደረገች ያለው ተሳትፎ በትብብር ማዕቀፉ ለጋራ እድገት መረጋገጥ ያላትን ቁርጠኝነት በተግባር የሚያሳይ መሆኑን አብራርተዋል።

እንደ አምባሳደሩ ገለፃ፤ አባል ሀገራቱ በሚቀይሱት የትብብር አቅጣጫ መሠረት ሩሲያ ከኢትዮጵያ ጋር በተለያዩ የትብብር መስኮች አጋርነቷን ታጠናክራለች።

ጎን ለጎንም ኢትዮጵያ የብሪክስ የልማት ባንክ አባል ለመሆን የምታደርገውን ጥረት ሩሲያ እንደምትደግፍም አምባሳደሩ አረጋግጠዋል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2006 ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ሕንድና ቻይና “ብሪክ” ቡድን የፈጠሩ ሲሆን በ2010 ደቡብ አፍሪካ ቡድኑን በመቀላቀሏ “ብሪክስ” ወደሚለው ስያሜ መጥቷል።

ከዘንድሮ የፈረንጆች ዓመት ጀምሮ ኢትዮጵያን ጨምሮ ግብጽ፣ ኢራን፣ ሳዑዲ አረቢያና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ይህንን በመስፋፋት ላይ ያለውን ጥምረት በይፋ ተቀላቅለዋል።

የብሪክስ አባል ሀገራት አሁን ላይ 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን የሚሆነውን የዓለም ሕዝብ የሚይዙ ሲሆን፤ ይህም ከአጠቃላይ የዓለም ሕዝብ ቁጥር አንጻር 45 በመቶ ማለት ነው።

የሀገራቱ ምጣኔ ኃብት 28 ነጥብ 5 ትሪሊየን ዶላር የሚገመት ሲሆን፤ ይህም ከወቅታዊው የዓለም ምጣኔ ኃብት አንጻር ሲታይ 28 በመቶ መሆኑን መረጃዎች እንደሚያሳዩ ኢዜአ ዘግቧል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review