ሩዋንዳ አስከፊውን ምዕራፍ በይቅርታ እና በእርቅ ተሻግራ አሁን ላይ በአገር መልሶ ግንባታ ተምሳሌታዊ አገር መሆኗን አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ገለጹ፡፡
በሩዋንዳ ቱትሲዎች ላይ የተፈፀመው የዘር ጭፍጨፋ 31ኛ ዓመት መታሰቢያ መርሃ ግብር በአፍሪካ ህብረት መሰብሰቢያ አዳራሽ ተካሂዷል፡፡
በመታሰቢያ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ባደረጉት ንግግር፣ መታሰቢያው በጭፍጨፋው ሕይወታቸውን ያጡ ንፁሃን ዜጎች የሚታወሱበት ብቻ ሳይሆን የሩዋንዳዊያን ፅናት እውቅና የሚሰጥበት ነው ብለዋል።
ሩዋንዳ አስከፊውን ምዕራፍ በይቅርታ እና በእርቅ ተሻግራ ዛሬ ላይ በአገር መልሶ ግንባታ ተምሳሌታዊ አገር መሆን መቻሏን አምባሳደር ብርቱካን ገልጸዋል።
በአፍሪካ ተመሳሳይ አይነት ጥፋት መደገም የለበትም ያሉት የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማሃሙድ አሊ የሱፍ፣ ግጭትን ቀድሞ ለማስቀረት የሚያስችሉ አቅሞችን ህብረቱ እንዲፈጥር ማድረግ ወሳኝ በመሆኑ፣ በትኩረት እንደሚሰራ ሊቀ መንበሩ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የሩዋንዳ አምባሳደር ቻርልስ ካራምባ በዘር ጭፍጨፋ ማግስት በሩዋንዳ ሰላም እና መረጋጋትን ለማስፋን ቀዳሚ ከሆኑ አገራት ኢትዮጵያ ዋነኛዋ እንደነበረች ገልፀው፣ ለዚህም ምስጋና አቅርበዋል።
በመታሰቢያ መርሃ ግብሩ ላይ የህሊና ጸሎት እና ሻማ ማብራት የተከናወነ ሲሆን የሃይማኖት አባቶች፣ የዲኘሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት እና ተማሪዎች መገኘታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ከዛሬ አስራ አምስት ዓመት ጀምሮ በየዓመቱ መጋቢት 30 ቀን የሩዋንዳ ዘር ጭጨፋ መታሰቢያ ዕለት ሆኖ በአፍሪካ ህብረት በተለያዩ መርሃግብሮች ታስቦ እንደሚውልም ተመላክቷል