ሪፎርሞች የኢትዮጵያን ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻነት አሳድገዋል -ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር)
AMN – ጥር 27/2017 ዓ.ም
ባለፉት ዓመታት ገቢራዊ የተደረጉ አይነተ ብዙ መንግስታዊ ሪፎርሞች የተንዛዙ አሰራሮችን በማስቀረት ኢትዮጵያ ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እንድትሆን ማስቻላቸውን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) ገለጹ።
ኢትዮጵያ በ2017 ዓ.ም በጀት ዓመት የመጀመሪያ አራት ወራት 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በላይ ስባለች።
መንግስት በኢትዮጵያ ምቹ እና ሳቢ የኢንቨስትመንት ምህዳር ለመፍጠር የሚያስችሉ በርካታ ሪፎርሞችን አድርጓል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም አዘጋጅነት በሚቀርበው ”ኢትዮጵያ ኢን ፎከስ” በተሰኘው ፕሮግራም ላይ ቆይታ አድርገዋል።
ኮሚሽነሩ በኢትዮጵያ የንግድ ስራ ምቹነትን ለማሻሻል እና ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታን ለመፍጠር እየተከናወኑ ያሉ የሪፎርም ስራዎች አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በዋናነት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳብ ላይ ትኩረቱን አድርጎ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
መንግስት ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የተለያዩ ሪፎርሞችን እየተገበረ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
የውጭ ባለሀብቶች ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ በአንድ መስኮት አገልግሎት ሁሉንም ጉዳያቸውን እንደሚጨርሱና ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታን መፍጠሩን ተናግረዋል።
ባለሀብቶቹ የባንክ፣ የኢንቨስትመንት ቪዛን፣ ፈቃድ ማግኘት እና የተለያዩ ግልጋሎቶችን አንድ ቦታ ማግኘታቸው ቀልጣፋ መስተንግዶ ለመስጠት ማስቻሉን ነው ኮሚሽነሩ የገለጹት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እ.አ.አ በ2018 የንግድ ስራ ምቹነት ማሻሻያ ፕሮጀክት ይፋ አድርገዋል።
በፕሮጀክቱ ከተቀመጡ 100 የሪፎርም አይነቶች መካከል መንግስት ከ80 በላይ የሚሆኑትን መተግበሩን ጠቁመዋል።
የኢንቨስትመንት ፈቃድ አሰጣጥን ማሻሻያ፣ ዲጂታል አሰራርን ማስፋት፣ የህግ ማዕቀፎችን ማሻሻል፣ እና ለንግድ ስራው ማነቆ የሆኑ የአሰራር መንዛዛቶችን ለማስቀረት በርካታ ሪፎርሞች መደረጋቸውን ገልጸዋል።
ሪፎርሞቹ መንግስት ለውጭ ባለሀብቶች ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታን ለመፍጠር ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ብለዋል ኮሚሽነሩ።
የመሬት እና መሰረተ ልማት አቅርቦትን ጨምሮ ባለሀብቶች የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች አጥጋቢ ምላሽ መስጠት መቻሉን አንስተዋል።
ግብርና፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ ኢነርጂ፣ ኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ እና ቱሪዝም ኢንቨስተሮች በስፋት ከተሰማሩባቸው መስኮች መካከል ይጠቀሳሉ ነው ያሉት።
መንግስት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት የማጠናከር እና አዳዲስ መደረሻዎችን የመፍጠር እንዲሁም ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በተለያዩ መስኮች እንዲሰማሩ የሚያስችሉ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
በአጠቃላይ በኢትዮጵያ የንግድ ስራ ምቹነት እና የኢንቨስትመንት ሳቢነትን ለማሻሻል የተከናወኑ ስራዎች ኢትዮጵያ ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ አድርጓታል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
መንግስት የውጭ ባለሀብቶች የሚያገኙትን አገልግሎት ለማሳለጥ እያደረገ ያለውን ድጋፍና እና የኢንቨስትመንት ምቹነት ለማሳደግ እያከናወነ ያለውን ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።