ኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት ተጋርጦባት የቆየውን ኢኮኖሚያዊ ምስቅልቅሎሽ ለማቃናት የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ ላይ እንዳለች ይታወቃል። ሰሞኑን የተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያም የዚሁ ተግባር አካል ነው ተብሏል። ማሻሻያው የውጭ ምንዛሬ ተመን በገበያው የሚወሰንበት ዕድል መፍጠሩን ተከትሎ አንዳንድ የንግዱ ማህበረሰብ ክፍሎች አግባብነት የጎደለው የዋጋ ጭማሪና ምርት መሰወርን የመሳሰሉ ጥፋቶች ሲፈፅሙ ይስተዋላል፡፡ ለመሆኑ እንዲህ ያለ እሳቤ ከምን የመነጨ ነው? ድርጊቱን ፈጽመው በተገኙት ላይስ ምን እርምጃ ይወሰዳል በሚሉ ነጥቦች ዙሪያ ሙያዊ ማብራሪያ ይዘናል፡፡
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የስነ ምጣኔ ሀብት መምህርና ተመራማሪ የሆኑት ይንገስ ዓለሙ (ዶ/ር) ሀገራት በተለያዩ ምክንያቶች የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎችን እንደሚ ወስዱ ጠቁመው፣ እንዲህ አይነት እርምጃዎች ሲወሰዱ ከግንዛቤ እጥረት የሚፈጠሩ ሌሎች ችግሮች አሉ ብለዋል። ከችግሮቹ መካከል ሰው ሰራሽ የምርት እጥረትን መፍጠርና የሸቀጦች ዋጋ መጨመር ተጠቃሽ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
ይንገስ (ዶ/ር) በሀገራችን ውስጥ ከኢኮኖሚ ማሻሻያ ጋር በተገናኘ የሚደረገው የዋጋ ጭማሪ ምንም ዓይነት ኢኮኖሚያዊ ምክንያት እንደሌለው ጠቅሰው፣ ምክንያቱም ነጋዴው አሁን እየሸጠ የሚገኘው ምርት ቢያንስ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት ገብቶ በእጃቸው የያዙት ምርት በመሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ የዋጋ ጭማሪውም ሆነ የምርት ስወራው ስግብግብነት ብቻ ነው ብለዋል፡፡
“በዚህ ጊዜ የሚደረግ የዋጋ ጭማሪ ምንም አይነት ኢኮኖሚያዊ ምክንያት ስለሌለው ማህበረሰቡ በአካባቢው የሚያስተውለውን መሠል ድርጊት ለተቆጣጣሪ አካል ከማሳወቅ መቦዘን የለበትም፡፡ መንግስትም አስፈላጊውን እርምጃ ሊወስድ ይገባል” ሲሉ አክለዋል፡፡
የገበያ መረጋጋት እንዲኖር ተፈላጊ ምርቶችን በገበያ ውስጥ እንዲበዙ ማድረግ አንዱ መፍትሄ ነው ያሉት ይንገስ (ዶ/ር)፣ በሌላ መንገድ ደግሞ መንግስት ከዚህ ቀደም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የማህበረሰብ ክፍሎች ታሳቢ ያደረገ በተለይም መሰረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ላይ የሚደረገው ድጎማ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የእሁድ ገበያዎችን ከአዲስ አበባ ከተማ በተጨማሪ በክልል ከተሞችም በማብዛት ችግሩን መቅረፍ ይቻላል ባይ ናቸውየማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው መስመር ይዞ መጓዝ እስከሚችል ድረስ የገበያ መዋዠቅ ይጠበቃል የሚሉት ይንገስ (ዶ/ር)፣ ስለዚህ የመንግስት ጣልቃ ገብነት አስፈላጊ መሆኑን አስምረውበታል፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ጀምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችም ሀሳብ ሰጥተውበታል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ዙሪያ በሰጡት ማብራሪያ፣ አግባብነት የሌለውን የዋጋ ጭማሪ እና ምርት በሚደብቁ ነጋዴዎች ላይ ሁሉም የህግ አስከባሪ አካል ጠንከር ያለ እርምጃ እንዲወስዱ ማሳሰባቸው ይታወሳል፡፡
የኢፌዴሪ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሽዴ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ትግበራው የተረጋጋ፣ የተሟላና ቀጣይነት ያለው ሀገራዊ እድገት የሚያመጣ መሆኑን ከሰሞኑ ለሚዲያዎች በሰጡት መግለጫ አንስተዋል። በመጀመሪያና በሁለተኛው ምዕራፍ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሂደት ወደ ተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ትግበራ ለመግባት ሰፊ ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱንና በሂደቱ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ቀርፎ ውጤታማ ለማድረግ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
የማሻሻያ ሂደቱም ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ.ኤም.ኤፍ) እና ዓለም ባንክን ጨምሮ በዓለም አቀፍ አጋሮች ድጋፍ የሚተገበር መሆኑን ተናግረዋል። የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፉ በገበያው እንዲመራ፣ ዕዳን በማቃለል፣ የገንዘብና ፋይናንስ ፖሊሲ፣ የመንግስት ገቢና ወጪ ፊስካል ፖሊሲን በማሻሻልና ዕዳን በማቃለል ረገድ የላቀ ጠቀሜት አንዳለው አቶ አሕመድ አንስተዋል። ሚኒስትሩ የፖሊሲ ትግበራው የዋጋ ንረትና የምንዛሬ ገበያ መዋዠቅን እንዲሁም የአጭር ጊዜ ጫናን በመቋቋም የተረጋጋ ኢኮኖሚ መፍጠር ዋነኛ ዓላማው መሆኑን ማሳወቃቸው ይታወሳል፡፡
የፌዴራል የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርም ሀሳቦች ተቀርጸው ባለፉት ስድስት ዓመታት በተለያየ ደረጃ ሲተገበር መቆየቱን ገልጸዋል። በዚህም መዋቅራዊ በሆኑ የአሰራር ግድፈቶች ታንቆ የነበረውን የግሉን ዘርፍ በማነቃቃት የኢኮኖሚው መሪ የሚሆንበት ሁኔታ መፈጠሩን ጠቁመዋል። የፕሮጀክቶች ግንባታ በታለመላቸው ጊዜ፣ ጥራትና በተመደበላቸው ሀብት ማጠናቀቅ መቻሉን አንስተው፣ የነበሩ ልምምዶች ለተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ትግበራ ጥሩ መነሻ እና አስቻይ ሁኔታ ይሆናሉ ብለዋል፡፡
ማሻሻያው የኑሮ ውድነትን ያስከትላል የሚለው ስጋት በብዙዎች ዘንድ ሲንፀባረቅ ይስተዋላል፡፡ ይህም የንግዱ ማህበረሰብና ሸማቹ ስለጉዳዩ ከሚኖራቸው የግንዛቤ ማነስ ሊሆን እንደሚችል መምህር ይንገስም (ዶ/ር) ይናገራሉ፡፡
ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ባልተገባ ሁኔታ በመተርጎም አላግባብ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ ከ7 ሺህ በላይ ነጋዴዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ መወሰዱ ተገልጿል፡፡ የኢፌዴሪ ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ህገ ወጥ ነጋዴዎች ላይ የሚወሰደው ይህ እርምጃ በተቀናጀ መልኩ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር መመሪያ መውጣትን ተከትሎ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉና ምርትን በማከማቸት ወይም በመሰወር እጥረት እንዲፈጠር በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ ጥብቅ እርምጃ እየተወሰደ እንደሆነም ሚኒስትሩ ተናግረዋል። በምንም መልኩ ዋጋ ለመጨመር የሚያበቃ ምክንያት ባለመኖሩ ድርጊቱን ፈጽመው የተገኙትን የንግድ ተቋማት ከማሸግ ባለፈ የንግድ ፍቃዳቸውን መሰረዝና ከንግዱ መስመር እንዲወጡ የማድረግ ስራ በዘላቂነት እንደሚሰራም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ አቶ ማሞ ምህረቱ በበኩላቸው፣ ማሻሻያው የገቢ አስተዳደርና አሰባሰብ፣ የገንዘብ እንዲሁም የውጭ ምንዛሬ አስተዳደርን ጨምሮ ሁሉንም ዘርፎች በማስተሳሰር የሚተገበር መሆኑን አንስተው፣ የውጭ ምንዛሬ ችግርን በዘላቂነት የሚፈታ ቁልፍ ውሳኔ ስለመሆኑም አብራርተዋል፡፡
ነገር ግን ይህንን ማሻሻያ ተገን በማድረግ የተለየ ጥቅም ለማግበስበስ የሚደረገው ሩጫ በምንም ዓይነት መመዘኛ ተቀባይነት የለውም ብለዋል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ የህግ አገልግሎት ክፍል ኃላፊ የሆኑት አቶ መለሰ ተገኑ፣ አጠቃላይ የንግድ እንቅስቃሴውንና በሂደቱ የሚፈፀሙ ጥፋቶችን ተጠያቂነት ከማስፈን አንጻር ለዝግጅት ክፍላችን ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም የንግድ ስርዓቱ ጤናማ ያልሆኑ እንቅስቃሴዎች በወንጀል የሚያስጠይቁ መሆናቸውንና የግብይት እቃዎችን መደበቅ ማከማቸትና መሰወርም የደንብ መተላለፍ መሆኑን አስረድተዋል። እንደዚህ ዓይነት ድርጊቶች በሸማቾች ጥበቃ አዋጅ 813/2006 በግልጽ የሚከለከሉ በመሆኑ በዚህ ድርጊት ላይ ተሳትፈው የሚገኙም ነጋዴዎች ከዓመታዊ ሽያጫቸው ከ5 እስከ 10 በመቶ ቅጣት እንዲሁም እስከ አምስት ዓመት የሚደርስ ፅኑ እስራት የሚያስቀጣ መሆኑን አብራርተዋል።
በመሆኑም ቢሮው ከመቅጣት አስቀድሞ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ሲሰራ የቆየ ሲሆን፣ ደንብ ተላልፈው በተገኙ ነጋዴዎች ላይ እርምጃዎች መወሰድ መጀመሩን አቶ መለሰ ተናግረዋል፡፡ የኑሮ ውድነት እንዲፈጠር እንዲሁም ሰው ሰራሽ የዋጋ ንረት መፍጠርም በተመሳሳይ የህግ ተጠያቂነት የሚያመጣ መሆኑን የህግ ባለሙያው ገልጸዋል።
በንግድ ስራ ላይ ያልተሰማሩም ቢሆኑ የድርጊቱ ተባባሪ ሆነው ከተገኙ እስከ 50 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣትና እስከ 5 ዓመት የሚደርስ ጽኑ እስራት የሚያስቀጣ መሆኑን በአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ የሕግ ክፍል ኃላፊው አንስተዋል። በመሆኑም የንግዱ ማህበረሰብና ሸማቾችም ቢሆኑ የንግድ እንቅስቃሴውን ህጋዊ አካሄድ በውል በመረዳት መብትና ግዴታቸውን ማወቅ አለባቸው ነው ያሉት። ለዘርፉ እንቅስቃሴ ስኬታማነት ቀጣይነት ያለው የግንዛቤ መፍጠር ስራ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፣ በሂደትም በጥብቅ ዲሲፕሊን ህጉን ማስከበር አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በአጠቃላይ መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎችን በመደበቅ እና ሰው ሰራሽ የሸቀጥ እጥረት እንዲፈጠር በማድረግ በምርቶች ላይ ተገቢ ያልሆነ ዋጋ በሚጨምሩ እና ምርት በሚሰውሩ አካላት ላይ ጠንካራ የሆነ ቁጥጥር እና ህግ የማስከበር ስራ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፣ የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለስልጣንን ያካተተ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደ ስራ ገብቷል። እንዲሁም በገበያ ውስጥ ተሳታፊ የሆነ ሸማችም ሆነ የንግዱ ማህበረሰብ መብቶቹን አውቆ እና ግዴታውን አክብሮ በመገበያየት፣ ችግሮች ሲያጋጥሙም ህጋዊ ስርዓቱን ተከትሎ በመፍታት የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ያስፈልጋል ሲሉ አቶ መለሰ አሳስበዋል፡፡
በቶሎሳ መብራቴ