ይህ መረጃ በሳምንት አንድ ቀን ዓለም በታሪክ ውስጥ ካስተናገደቻቸው ትላልቅ ክስተቶች መካከል ጥቂቶቹን መርጠን ወደ እናንተው የምናደርስበትና የምናስታውስበት ነው፡፡
ለዛሬም ባሳለፍነው ሳምንት ውስጥ በታሪክ ከተመዘገቡ ሁነቶች መካከል የሚከተሉትን መርጠን ልናስታውስ ወደናል፤ መልካም ንባብ።
1.ሳሙኤል ሞርስ የቴሌግራፍ ፈጠራውን ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ ያደረገው እ.ኤ.አ ጥር 6 ቀን በ1838 በዚህ ባሳለፍነው ሳምንት ነበር፡፡
የሞርስ የኤሌክትሪክ ቴሌግራፍ ፈጠራ ለመጀመሪያ ጊዜ የርቀት ግንኙነትን በአስደናቂ ሁኔታ እንዳስከተለ ነው መረጃዎች የሚያመላክቱት።
ሞርስ፣ ቴሌግራፍን ከመስራቱ በፊት፣ በረጅም ርቀት ላይ የሚደረጉ ግንኙነቶች ይከናወኑ የነበሩት በሰው መልክተኞች፣ በጭስ ምልክቶች እና ሌሎች ጥንታዊ በሆኑ ዘዴዎች ብቻ የተገደበ እንደነበር ነው የሚገለጸው።
ሆኖም ግን የሞርስ ቴሌግራፍ፣ በመዳብ ሽቦዎች አማካኝነት እና በሚሰጡ ‹ኮዶች› መልዕክቶች በፍጥነት እንዲተላለፉ አስችሏል፡፡ ይህ ትልቅ ግኝት በህብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ የሆነ አወንታዊ ተጽዕኖ እንዳሳደረ ነው የሚነገረው፡፡
2. ጥቁር አሜሪካዊያን ወንዶች በዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ የመምረጥ መብት ያገኙት እ.ኤ.አ ጥር 8 ቀን 1867 በዚህ ባሳለፍነው ሳምንት ነበር፡፡
በወቅቱ በዲሲ የሚኖሩ ጥቁር አፍሪካ አሜሪካዊያን ዜጎች ለአካባቢ ምክር ቤት ድምጽ የሰጡ ሲሆን፣ ነገር ግን በኮንግረስ ውስጥ ምንም ውክል ስላልነበራቸው በፕሬዚዳንታዊ ምርጫዎች ላይ እንዳልተሳተፉ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
3.ጣሊያናዊው የሥነ ፈለግ ተመራማሪ ጋሊልዮ ጋሊሊ በተወለደ በ77 ዓመቱ በጣሊያን ያረፈው እ.ኤ.አ ጥር 8 ቀን 1642 በዚህ ባሳለፍነው ሳምንት ነበር፡፡
ጋሊልዮ በሳይንሳዊ ግኝቶቹ ምክንያት የዘመናዊ የሥነ ፈለክ፣ የዘመናዊ ፊዚክስ እና የሳይንስ አባት እየተባለ ይጠራል።
ጋሊሊዮ፣ ሰማይን ለማየት ቴሌስኮፕን የተጠቀመ የመጀመሪያው ሰው ከመሆኑ በተጨማሪ የጁፒተርን ጨረቃዎች፣ የሳተርን ቀለበቶች፣ የፀሐይ ነጠብጣቦችን እና የፀሐይ ሽክርክርን በሳይንሳዊ ምርምሩ ማግኘቱ ይነገርለታል፡፡
ምንጭ፡-የተለያዩ የሂስትሪ ቻናሎች