ይህ መረጃ በሳምንት አንድ ቀን ዓለም በታሪክ ውስጥ ካስተናገደቻቸው ትላልቅ ክስተቶች መካከል ጥቂቶቹን መርጠን ወደ እናንተው የምናደርስበትና የምናስታውስበት ነው፡፡
ለዛሬም ባሳለፍነው ሳምንት ውስጥ በታሪክ ከተመዘገቡ ሁነቶች መካከል የሚከተሉትን መርጠን ልናስታውስ ወደናል፤ መልካም ንባብ።
1. ዶናልድ ትራምፕ ለመጀመሪያ ጊዜ 45ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው የተመረጡት እ.ኤ.አ ህዳር 8 ቀን በ2016 በዚህ ባሳለፍነው ሳምንት ነበር፡፡
በመሆኑም እ.ኤ.አ. ጥር 20 ቀን 2017 በይፋ ሥራ የጀመሩ ሲሆን እስከ ጥር 20 ቀን 2021 አሜሪካን በፕሪዚዳንትነት አገልግለዋል።
የዴሞክራቲክ እጩ የነበሩትን ሂላሪ ክሊንተንን በማሸነፍ ነበር ትራምፕ ለፕሪዚዳንትነት የበቁት፡፡
በዚህ የፕሬዝዳንትነት ዘመናቸውም የታክስ ማሻሻያዎችን፣ የኢሚግሬሽን ገደቦችን እና ቁጥጥርን ጨምሮ በርካታ ጠቃሚ ፖሊሲዎችን ተግባራዊ እንዳደረጉ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ትራምፕ ሰሞኑን በተካሄደው የአሜሪካ ፕሪዚዳንታዊ ምርጫም ካማላ ሃሪስን በማሸነፍ 47ኛው የአሜሪካ ፕሪዚዳንት ሆነው ለ2ኛ ጊዜ መመረጥ ችለዋል፡፡
2. የጀርመን ዋና ከተማ የሆነችውን በርሊንን ምስራቅ እና ምዕራብ በርሊን በማለት ክፍሎት የነበረው የግንብ አጥር እንዲፈርስ የተደረገው እ.ኤ.አ ህዳር 9 ቀን 1989 በዚህ ባሳለፍነወ ሳምንት ነበር፡፡
የበርሊን ግንብ እንዲፈርስ መደረጉ ከቤተሰቦቻቸውና ከዘመዶቻቸው ተለያይተው በነበሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ ከፍተኛ የሆነ ደስታ እንደፈጠረም መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
የምስራቅ ጀርመን መንግስት ዜጎቹ ወደ ምዕራብ ጀርመን በነፃነት መጓዝ እንደሚችሉ በድንገት ባሳወቀበት ወቅት አንድ ትልቅ ክስተት እንደተፈጠረ እና በምስራቅ ጀርመን ዜጎች በኩል ከፍተኛ ብስራት እንደሆነም ነው መረጃዎች የሚያመላክቱት፡፡
ማስታወቂያው እንደተነገረ በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት በምስራቅ እና በምዕራብ በርሊን መካከል ተዘግተው ከነበሩት የድንበር ማቋረጫዎች መካከል አንዱ እና ታዋቂ የሆነው የቼክ ፖይንት ቻርሊ በርን ጨምሮ ሌሎች ማቋረጫዎችን በመጠቀም በሺዎች የሚቆጠሩ ምስራቅ ጀርመናዊያን ወደ ምዕራብ በርሊን እንደጎረፉ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
3. የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት(ዩኔስኮ) የተመሰረተው እ.ኤ.አ ህዳር 4 ቀን በ1946 በዚህ ባሳለፍነው ሳምንት ነበር፡፡
ድርጅቱ የተቋቋመበት ዋና ዓላማ በትምህርት፣ በሳይንስ እና በባህል ጥበቃ ዙሪያ በሀገራት መካከል ትብብርን ለማበረታታት ሲሆን፤ በዓለም አቀፍ ትብብር ውስጥ ትልቅ ቦታ እንዳለው ነው የሚገለጸው፡፡
የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት ሲመሰረት በ37 ሀገሮች ፊርማ እንደነበር መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
ድርጅቱ ከትምህርት፣ የባህል ጥበቃ እና ሳይንሳዊ እድገት ጋር የተያያዙ ዓለም አቀፍ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ወሳኝ ሚና እየተጫውተ ይገኛል፡፡
ምንጭ፡- የተለያዩ የታሪክ ማህደሮች