በጊዜው አማረ
ሴት ማለት ምህረት ነች፣ ማህደር የህይወት፣
እውነተኛ ሰላም፣ ሙሉ ፍቅር አይነት
ሴት ማለት ብርሃን፣ በጨለማ ጮራ
በልዝብ አንደበት ባህሪ የምትገራ
ሴት ማለት ሀገር ነች፣ ታሪክ የህዝብ መንገድ፣
ቂምን ሳይቋጥሩ፣ ትናንትን ረስቶ ከነገ ጋር መሄድ… ይላል ወጣቱ ገጣሚ አክሊሉ ሁናቸው፡፡ ገጣሚው ስለ ሴት ከተቀኙ የሀገራችን ገጣሚዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ በእርግጥም ጥበብ የጊዜና የአእምሮ ውጤት ነው። የተፈጠረበት ዘመን፣ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ሃይማኖታዊ አውድ ውጤት ነው። ጥበብ በባህሪው የታዳጊዎች፣ የአንጋፋዎች፣ የሴቶች እና ወንዶች፣ በሁሉም ቦታ የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች ረቂቅ በረከት እንደመሆኑ የታሪክ ተመራማሪዎች የትኩረት ማዕከል ሆኖ፣ በርካቶችን እያስደመመ ዛሬም ድረስ ዘልቋል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ደግሞ የሴቶች አበርክቶ ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም፡፡ ሴቶች ራሳቸው የጥበብ ባለሙያ ሆነው ብዙ አበርክተዋል። በተጨማሪም ሴቶች በኪነ ጥበብ ተገልጸዋል፡፡ በዚህ ጹሑፍ በየዓመቱ በፈረንጆች መጋቢት 8 የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን መነሻ በማድረግ ሴቶች በኪነ ጥበብ እንዴት ተገለጹ የሚለውን በአጭሩ ለመዳሰስ ሞክረናል፡፡
ጥቂት ስለዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን
ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በየዓመቱ መጋቢት 8 ይከበራል፡፡ ታሪካዊ መነሻው የሰራተኞች እንቅስቃሴ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዕውቅና የተሰጠው ዓመታዊ በዓል ነው፡፡ የክብረ በዓሉ ጅማሮ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር 1908 ነው። በወቅቱ 15 ሺህ የሚሆኑ ሴቶች በኒውዮርክ ከተማ ላይ የሥራ ሰዓት መሻሻል (ማጠር)፣ የተሻለ ክፍያና ሴቶች በምርጫ መሳተፍ አለባቸው በሚል የተቃውሞ ሰልፍ አካሄዱ። ከአንድ ዓመት በኋላም የአሜሪካ ሶሻሊስት ፓርቲ የመጀመሪያውን ብሔራዊ የሴቶች ቀን አወጀ። ይሁን እንጅ ቀኑን ዓለም አቀፍ የማድረግ ሃሳቡ የመጣው ክላራ ዜትኪን በምትባል ግለሰብ አማካኝነት ነው ይላል ቢቢሲ እ.ኤ.አ. በ2024 ስለጉዳዩ በሰራው ዘገባ።
እንደዘገባው ክላራ ዜትኪን በዴንማርኳ ኮፐንሃገን በአውሮፓውያኑ 1910 የሴት ሠራተኞች ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ ነበር ሃሳቡን ያነሳችው። በወቅቱ ከ17 ሀገራት የተውጣጡ 100 ሴቶች ተሳትፈውበት የነበረ ሲሆን በሃሳቧም ሙሉ በሙሉ ነው የተስማሙት። ለመጀመሪያ ጊዜም በኦስትሪያ፣ ዴንማርክ፣ ጀርመንና ስዊዘርላንድ በአውሮፓውያኑ 1911 የሴቶች ቀን መከበር ጀመረ፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ ይፋዊ ሆኖ መከበር የጀመረው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ክብረ በዓሉን ማክበር በጀመረበት በአውሮፓውያኑ 1975 ነው። ለመጀመሪያ ጊዜ ™የኋላውን ማክበር፤ የወደፊቱን ማቀድ∫ በሚል በተባበሩት መንግሥታት ባወጣው መሪ ቃል በ1996 ነበረ በዓለም አቀፍ ደረጃ በደመቀ ሁኔታ እለቱ የተከበረው፡፡
ዓለም አቀፉ የሴቶች ቀን የሚዘከረው ሴቶች በማህረበሰቡ የደረሰባቸውን ጭቆናን ተቋቁመው በፖለቲካውና በምጣኔ ሀብቱ ያገኙትን ትሩፋት ለመዘከር በማሰብ ነው፡፡ በዓሉ ዘንድሮም ™ተግባራችን ይፍጠን∫ በሚል መሪ ሀሳብ በልዩ ልዩ መርሃ ግብሮች ተከብሮ ይውላል፡፡

ሴቶችና ኪነ ጥበብ
የሰው ልጅ የበለጸገ፣ ሃሳብን፣ ስሜትንና ማንነትን የሚገልጽ የጥበብ ባህል እና ታሪክ አለው፡፡ ሥዕል፣ ግጥም፣ ሙዚቃ፣ ቅርፃ ቅርፅ፣ የብረታ ብረት ስራ ጥበብ፣ ፎቶ ግራፍ እንዲሁም የህትመት ሥራዎች ትናንትም የነበሩና ዛሬም እየዘመኑ የመጡ የጥበብ ውጤቶች ናቸው፡፡ ለእነዚህ ኪነ ጥበባዊ ውጤቶች ደግሞ የሴቶች ሚና ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል። ሴቶች ራሳቸው እነዚህን ጥበባዊ ክዋኔዎች አሳምረው ከመስራታቸውም ባለፈ ሴትነታቸው በራሱ ለኪነ ጥበብ እድገት አስተዋጽኦ አበርክቷል ማለት ይቻላል፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ስለሴት ልጅ መብት መከበር ግንዛቤ ለመፍጠር የተሰሩ ናቸው፡፡ በሀገራችንም ማርች 8 ሲመጣ ተደጋግመው ይሰሙ ከነበሩ ዘፈኖች ውስጥ አንዱ ™ሴት ናት ትከበር∫ የሚለው ህብረ ዝማሬ ነው፡፡
ሰው ነን
ሰው ነን ስንል ሰው ነን
ሰው ማለት ምንድን ነው
እንደ እንስሳ እንዳይሆን አርጎት በተፈጥሮ
እንዲያስብ የሰጠው የሚያስብ አእምሮ
ሰውነት
በአምሳል ፈጥሮ ባበጀው ፈጣሪ
መሆን የሚገባው ለሰው ተቆርቋሪ
እንዲንከባከባት ነው እንጅ እንዲጠብቃት
ማን አዘዘው ወንዱን ሴቷን እንዲያጠቃት… በማለት በዘመኑ በስፋት ይስተዋል የነበረውንና ዛሬም ድረስ ሙሉ በሙሉ ያልተቀረፈውን የሴቶች ጥቃት እንዲቀር በህብረ ዝማሬው ግንዛቤ ለመፍጠር ተሞክሯል፡፡በተጨማሪም፡-
የቤተሰብ ዋልታ የቤተሰብ ማገር
ባለሙሉ ድርሻ የወገን የሀገር
የጥንካሬ ምንጭ የወንድ ልጅ ብርታት
የትጋት መነሻ የስኬት ምክንያት
ሴት ናት…በማለት ሴቶች በቤተሰብ፣ በማህበረሰብ እና በሀገር እድገትና ለውጥ ያላቸው ደርሻ ትልቅ መሆኑን ይመሰክራል፡፡ ሴቶች በማንኛውም መልኩ እና ሁኔታ የጥቃት ሰለባ ሊሆኑ እንደማይገባም በሙዚቃ ስራው ውስጥ በአጽንኦት ተንጸባርቋል፡፡
ሌላኛው ሙዚቃ ™የሀገር ካስማ ሴት ነኝ∫ ይሰኛል፡፡ በዚህ የሙዚቃ ስራ በርካታ ተወዳጅ ድምጻዊያን ተሳትፈውበታል፡፡ ሙዚቃውን ኩኩ ሰብስቤ፣ፍቅራአዲስ ነቃጥበብ፣ ዘሪቱ ከበደ፣ ሳያት ደምሴ እና ራሄል ጌቱ ተጫውተውታል፡፡ በተጨማሪም ሚካኤል ታዬ(ልጅ ሚካኤል)፣ኤፍሬም አስራት እና አስገኘው አሽኮ በሙዚቃ ስራው ላይ አሻራቸውን አኑረዋል፡፡
የሀገር ካስማ ሴት ነኝ እኔ
ለሀቅ የኖርኩ በዘመኔ
የሀገር ካስማ ሴት ነኝ እኔ
የበረታው በወገኔ..በማለት ሴቶች ለአንድ ሀገር እድገት፣ ለውጥና ማህበራዊ መረጋጋት ያላቸውን ትልቅ ድርሻ እውቅና ሰጥተዋል፡፡ ሴቶች ጸብን በማብረድ፣ እርቅን በመፍጠር፣ አብሮነትን በመሸመን ያላቸውን ጥበብም አወድሰዋል፡፡
ጠብ ይለዩን በማስማማቱ
ቂም ማርከሻ አላት ብልሃቱ
አላት ብልሃቱ ጥብብ ብልሃቱ
አላት ትዕግስቱ ስለ አንድነቱ… እያሉ የሴትን ጥበብና ብልሃት ከፍ አድርገዋል። ሴቶች በሀገርና በማህበረሰቡ ውስጥ ያላቸውን ድርሻ አጉልተዋል፡፡
ውሳኔዬን አምነዋለው
ለኔ የታየኝ በቂ ነው
እወጣለሁ በአደባባይ
እሰማለሁ በሀገር ጉዳይ
ከዚህ ባለፈ ሴቶች በሀገር ጉዳይ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለባቸው ሙዚቃው ያበረታታል፡፡ሴትነት በብዙ መልኩ ይገለጻል፡፡ እህትነት፣ ሀገርነት፣ አክስትነት አለፍ ብሎም መውለድን ከታደሉ ጥልቅ የእናትነት ስሜት ነው። ይህ ሴትነትና እናትነትን በዘመን ተሻጋሪ የሙዚቃ ስራዋ ውስጥ ከገለጹ ሙዚቀኞች ውስጥ አንዷ ብዙነሽ በቀለ ነች፡፡
“የእናት ውለታዋ” የተሰኘው የብዙነሽ በቀለ ሙዚቃ ተወዳጅ፣ ዘመን አይሽሬ እና በብዙዎችም ዘንድ የሚታወስ ነው። ሙዚቃ የእናትነትን ዋጋ ያሳየ እና ያከበረም ከመሆኑም በላይ በበርካቶች ልብ እና አእምሮ ተቀርጾ የሚኖር ዘመን አይሽሬ ስራ ነው፡፡
የእናት ውለታዋን ባወሳ እወዳለሁ
ደግነቷ ብዙ መሆኑን አውቃለሁ
ወላጅ እናት እኮ ፍፁም በመንፈሷ
ልጇን ትወዳለች አብልጣ ከራሷ… በማለት በተስረቅራቂ ድምጿ ለእናቶች ክብር አዚማለች፡፡ በ1960ዎቹና 1970ዎቹ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ላይ የነገሰችው ብዙነሽ በቀለ እናት ለልጇ ስትል የምትከፍለው ዋጋ ተዘርዝሮ አያልቅም ስትል በሙዚቃዋ እናት ስለመሆን ትልቅነትና ስለ ሴትነት ዋጋ አሻራዋን አኑራለች፡፡
ዘጠኝ ወር በሆዷ ከዚያም በጀርባዋ
ጡቷን እያጠባች እኔን ማሳደግዋ
ዘውትር ይሰማኛል የናቴ ድካሟ
ጥራ በማሳደግ በሴትነት አቅሟ… በማለት፡፡
ድምጻዊቷ የእናት ውለታ ተዘርዝሮ የማያልቅ፣ ስጋዊ፣ መንፈሳዊም ቁርኝት ያለው፣ ከራስ አስበልጦ ልጅን የመውደድ ጸጋ እና ይህም ደግሞ መወሳትና መዘከር ያለበት እንደሆነ በስንኞቿ ገልጻለች። በተለይ ደግሞ በተለያየ ምክንያት ልጃቸውን ለብቻቸው የሚያሳድጉ እናቶች ጠንካራ ተምሳሌቶች እና የማይበገሩ ጀግና እናት ሴቶች መሆናቸውን በዘመን ተሻጋሪ ስራዋ፣ ሳቢ በሆኑ ስንኞች ከሽና አቀንቅናለች፡፡
ከሙዚቃም በተጨማሪ በሀገራችን ስለሴቶች የተለያዩ መጽሐፍት ተጽፈው ለንባብ በቅተዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የኢትዮጵያ ስኬታማ ሴቶችን ታሪክ “ተምሳሌት፣ እፁብ ድንቅ ኢትዮጵያውያን ሴቶች” የተሰኘው መፅሐፍ ቀዳሚው ተጠቃሽ ነው፡፡
መፅሐፉ፤ የኢትዮጵያ ሴቶች ከጥንት ጀምሮ እስካለንበት ዘመን ድረስ የተጫወቱትን ጉልህ ሚና የሚዘክር ሲሆን በተለያዩ ዘርፎች ተሰማርተው አንፀባራቂ ውጤት ያስመዘገቡ የ64 ኢትዮጵያዊያን ሴቶችን ታሪክ አካትቷል፡፡
በጋዜጠኝነት፣ በህግ፣ በንግድ፣ በህክምና፣ በግብርና፣ በኪነ ጥበብ፣ በማህበረሰብ አገልግሎት፣ በግንባታ ሙያ፣ በበጐ አድራጐት፣ በአመራር እና በሌሎች የሙያ ዘርፎች ለስኬት የበቁ ሴቶች ታሪክ በዚህ መጽሐፍ ተከትቧል፡፡
ከመጽሐፍ ሙዚቃ ግጥም እና ስዕል ባለፈም በማህበረሳበችን ዘንድ ሴትን የሚያወድሱ፣ የሚያበረቱና ችሎታዋን የሚገልጹ አባባሎች ይገኛሉ፡፡ በእርግጥ አሉታዊ አባባሎች መኖራቸው የማይካድ ቢሆንም እነዚህን መሰል አዎንታዊ አባባሎችም ይገኛሉ። የሴትን ብልሀት የውሀን ጉልበት ይስጥህ፣ ከሴት ብልሀትን ከጉንዳን ትዕግስትን ተማር፤ ከጠንካራ ወንድ ጀርባ ጠንካራ ሴት አለች፤ ሴት ለመላ፣ ጌሾ ለጠላ እንዲሁም የሴት ብልሀት፣ የጎራዴ ስለት አይረታም የሚሉትን በጥቂቱ መጥቀስ ይቻላል። በስዕል ደግሞ ሰዓሊ ታደሰ መስፍን የሀገራችንን ሴቶች አለባበስ፣ ወግ፣ ስርዓትና ማንነት አጉልቶ በማሳየት ተጠቃሽ ነው፡፡