AMN – ታኅሣሥ 24/2017 ዓ.ም
ስምንት ተጨማሪ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግን በይፋ ተቀላቅለዋል።
ድርጅቶቹም የኢትዮ ፖስታ፣ ኢትዮ ኢንጅነሪንግ ግሩፕ፣ የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት፣ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና ብሔራዊ የእንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት ናቸው።
በዛሬው እለት በተካሄደው ይፋዊ የመቀላቀያና የትውውቅ መርሐ ግብር ላይ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ብሩክ ታዬ(ዶ/ር)፣ የሆልዲንጉ የቦርድ አባልና የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ እንዲሁም የልማት ድርጅቶች ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ዋና ስራ አስፈጻሚ ብሩክ ታዬ(ዶ/ር)፤ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ማሻሻያ አካል ሆኖ የተመሰረተው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ በስሩ 40 የልማት ድርጅቶችን በባለቤትነት እያስተዳደረ መሆኑን ገልጸዋል።
የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን የኮርፖሬት አስተዳደርና ትርፋማነት በማሻሻል የተሳካ ስራ እያከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።
ሆልዲንጉ የሀገር ሀብት ከሀገር ዕዳ ይበልጣል የሚል መርህ እንዳለው ጠቅሰው፥ ለዚህም የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ያላቸውን ሀብት አውቆ፣ በአግባቡ ማስተዳደርና ለሀገር ጥቅም ለማዋል በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲን የቦርድ አባል እና የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ፤ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ገቢ በማመንጨት፣ የመሰረተ ልማት በመገንባትና በስራ ዕድል ፈጠራ ትልቅ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል።
የልማት ድርጅቶች ወሳኝ መሰረተ ልማቶችን በመገንባት፣ የህዝብ አገልግሎትን በማሳለጥ እና ገቢና ወጪ ንግዱ ላይ ወሳኝ ሚና በመጫወት የሀገርን ልማትና ዕድገት በማፋጠን እና የዜጎችን ህይወት በማሻሻል ወሳኝ ሚና እያበረከቱ ነው ብለዋል።
በሀገር እና በዓለም አቀፍ አውድ ውስጥ ተወዳዳሪ፣ ትርፋማና ቀጣይነት ያለው የቢዝነስ ስራን ለማሳለጥ የልማት ድርጅቶቹ በአሰራር፣ በተቋማዊ አደረጃጀትና በፖሊሲ ጠንካራ መሆን እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ ሀብታሙ ኃይለሚካኤል፤ ሆልዲንጉ የልማት ድርጅቶችን በንግድ እሳቤ ውጤታማ ማድረግ፣ በሀገሪቱ የሚገኙ የመንግስት ሀብቶችን የማስተዳደር፣ የመምራትና የማልማት ኃላፊነት እንደተሰጠው ገልጸዋል።
በዚሁ መሰረት ከዚህ ቀደም በመንግሥት ይዞታና የልማት ድርጅቶች አስተዳደር ስር የነበሩ ስምንት የልማት ድርጅቶችን መቀላቀሉን ገልጸዋል።
የመንግሥት የልማት ድርጅቶቹ በዘርፍ፣ በምርት መጠን፣ በጂኦግራፊያዊ ተደራሽነት ብዝኃነት ያለው ኢንቨስትመንትን እንዲያስፋፉ ትኩረት መሰጠቱን አንስተዋል።
የመንግሥት የልማት ድርጅቶቹ በቀጣይ ገቢ ማመንጨት፣ ትርፋማነትን ማሳደግ እና ጠንካራ ቁመና እንዲኖራቸው አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።
አዲስ ከተቀላቀሉ የልማት ድርጅቶች መካከል የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍስሐ ይታገሱ(ዶ/ር፤ ኮርፖሬሽኑ የኢንቨስትመንት ሆልዲንግን መቀላቀሉ ትልቅ ዕድል መሆኑን ገልጸዋል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ፈሰስ በተደረገላቸው ኢንቨስትመንት ልክ ኢንዱስትሪዎች ወደ ምርት እንዲገቡ በማድረግ ውጤታማ እንዲሆኑ ትልቅ አቅም ይፈጥራልም ነው ያሉት።
በተለይም የተቀናጀ መሰረተ ልማት ለኢንቨስተሮች በማቅረብ ተጨማሪ ኢንቨስትመንት ለመሳብ አዲስ ምዕራፍ እንደሚከፍት አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ፖስታ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዳግማዊ ኃይልዬ፤ የልማት ድርጅቶች በአንድ ጥላ ስር መተዳደራቸው ኩባንያዎች ውጤታማ እንዲሆኑ እና ለሀገርና ህዝብ እንዲጠቅሙ ያስችላል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የኢትዮጵያ ፖስታ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ስር መጠቃለሉ ትርፋማነቱን እንዲያስቀጥል እና ከሌሎች ኩባንያዎች ጋር በቅርበት እንዲሰራ ዕድል እንደሚፈጥርለትም ገልጸዋል።