ቅን ልቦች በተቃኑ መንገዶች

 “የትራፊክ አደጋ ወንድሜን አካል ጉዳተኛ አድርጎብኛል” ይላል የትራፊክ እንቅስቃሴን ለማሳለጥ በመዲናዋ ጎዳናዎች ላይ ተሠማርቶ የሚገኘው በጎ ፈቃደኛ ወጣት ከድር ሰይድ፡፡ ከድር ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶችን ሰጥቷል፡፡ በተለይም ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራው የትራፊክ ፍሰትን ማስተናበር ላይ ነው፡፡ ለዚህ በምክንያትነት የሚያነሳው ደግሞ ወንድሙን ጨምሮ ቁጥሩ ቀላል የማይባል የህብረተሰብ ክፍል ለሞት፣ ለአካል ጉዳት እና ለንብረት ውድመት እየዳረገ መቀጠሉ ነው፡፡ ጉዳት አልባ ሆኖ የተወለደው ወንድሙ በደረሰበት የመኪና አደጋ አካል ጉዳተኛ እንዲሆንና በክራንች እንዲሄድ አድርጎታል፡፡ ይህ በቅርብ ቤተሰቡ ላይ የደረሰው አደጋ በሌሎች እንዳይከሰት “የድርሻዬን መወጣት አለብኝ” በሚል ተነሳስቶ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ነው ያብራራልን፡፡

በጎ ፈቃደኛው ባለፉት ዓመታት ያዳበረውን ልምድ በመጠቀም አሁን ላይ የአራዳ ክፍለ ከተማ የትራፊክ በጎ ፈቃድ አስተባባሪ በመሆን እና መሰል አገልግሎት ላይ የተሰማሩ ወጣቶችን እየደገፈ ይገኛል፡፡ በያዝነው የክረምት ወቅት የትራፊክ  ፍሰቱን የማሳለጡ አገልግሎት እንዴት እየተመራ እንደሆነ ጠይቀነው በሰጠው ምላሽ፤ በክፍለ ከተማው ከመሰል ጓደኞቹ ጋር በጋራ ጥረት በማድረጉ ማህበረሰቡ ራሱን ከትራፊክ አደጋ ለመጠበቅ ያለው ግንዛቤ እያደገ መምጣቱን እንደታዘበ አጫውቶናል፡፡ እግረኛውም ሆነ አሽከርካሪው በተፈቀደላቸው መንገድ የመንቀሳቀስ፣ የትራፊክ መብራቶችን የመጠቀም እንዲሁም በጎ ፈቃደኛ የትራፊክ አስተናባሪዎችን የማክበር ሁኔታዎች መሻሻል አሳይቷል፡፡ ለውጥ በመምጣቱም ለዓመታት እሱና ጓደኞቹ  የተሰማሩበት ተግባር ዋጋ እያገኘ እንደሆነ እንዲያስብና የተሰማራበትን የስራ መስክ የበለጠ እየወደደው እንዲመጣ እንዳደረገው ተናግሯል፡፡

የኮሪደር ልማቱ አካል በሆነው ፒያሳ ትራፊክ የማስከበር ስራ ላይ በጎ ፈቃደኞች ተሰማርተው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ

የአብዛኛው ማህበረሰብ ግንዛቤ እያደገ የመጣ ቢሆንም፤ ጥቂት በሚባሉ ግለሰቦች ላይ የሚስተዋሉ የግንዛቤ ማነስ ችግሮች እንዳሉ በጎ ፈቃደኛው አልሸሸገም፡፡ ስህተታቸውን ለመጠቆም እና ለማስገንዘብ በሚደረግ ጥረት መካከል አዎንታዊ ምላሽ የሚሰጡ የመኖራቸውን  ያክል፤ በተቃራኒው አስነዋሪ ንግግር የሚናገሩ ግለሰቦች ያጋጥማሉ፡፡ ግንዛቤውና ዕውቀቱ ያላቸውም ቢሆኑ አንዳንድ ጊዜ በሀሳብ ተውጠው በማይፈቀድበት ስፍራና ሰዓት ሊንቀሳቀሱ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ፡- አሽከርካሪዎች ትራፊክ መብራት መጣስና ለእግረኞች ቅድሚያ ያለመስጠት፣ እግረኞች ደግሞ መኪና ሳይቆም ለመሻገር መሞከርና በዜብራ ያለመሻገር ሊሆን ይችላል፡፡ እንዲህ አይነት አጋጣሚዎች ሲከሰቱ ከገቡበት ሀሳብ እንዲባንኑና ትክክለኛውን የመንገድ አጠቃቀም እንዲጠቀሙ የማድረግ ስራ እንደሚሠሩም አስረድቷል፡፡

በኮሪደር ልማት ፕሮጀክት አማካኝነት በለሙ የመንገድ መሰረተ ልማቶች ላይ የትራፊክ የማስተናበር ስራው ከድሮው ጋር ሲነጻጸር ስላለው ልዩነት አስመልከቶ በጎ ፈቃደኛው እንደገለፀው፤ “ልዩነቱ የሰፋ ነው” በማለት ነበር ምላሽ መስጠት የጀመረው፤ “ቀደም ሲል መንገዶቹ ጠባብ ስለነበሩ በጎ ፍቃደኞች ራሳቸውን አደጋ ውስጥ አስገብተው ነበር የማሳለጥ ስራውን ይሰሩ የነበረው፡፡ አጠቃላይ መንገዶቹ ጠባብ ከመሆናቸውም በላይ ዳርና ዳራቸው እንደ አሸዋና ድንጋይ የተቀመጠባቸውና የተቆፋፈሩ ስለነበሩ ለማስተናበር ስራው እንቅፋት ሆነው ቆይተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን መንገዱ ሰፊ በመሆኑ ስራውን በቀላሉ ማሳለጥ ችለናል፡፡” ሲል አብራርቶልናል፡፡

ወጣት መሰረት ቱማ ሌላዋ የትራፊክ በጎ ፍቃድ አገልግሎት ስትሰጥ ያገኘናት ወጣት ናት፡፡ ወጣቷ በትራፊክ እንቅስቃሴ ሥርዓት ማስያዝ ተግባር ላይ በበጎ ፈቃደኝነት ለአራት ተከታታይ ዓመታት አገልግላለች፡፡ እንደ ወጣቷ ገለጻ፣ ህጻናትን፣ አቅመ ደካማ የሆኑ ትልልቅ ሰዎችንና አካል ጉዳተኞችን ማገልገል መቻሏ ደስታ የሚፈጥር ተግባር ነው፡፡ አስፋልት መንገድ ሲሻገሩ አደጋ እንዳይደርስባቸውና ግራ ቀኝ አይተው በጥንቃቄ እንዲሻገሩ እገዛ ያደርጋሉ፡፡

በአንዳንድ እግረኞችና አሽከርካሪዎች ስድብ እንደሚያጋጥማትና ይህንንም በጸጋ ተቀብላ ስራዋን እንደምትሰራ የገለጸችው ወጣቷ፣ “ማህበራዊ ሃላፊነትን መወጣት የሚቻለው የሚያጋጥሙ አስቸጋሪ ጉዳዮችን መሻገር ሲቻል ነው” በማለት ራሷን ለበጎ ፈቃድ አገልግሎት መስጠቷን አጽንኦት ሰጥታ ተናግራለች፡፡

በኮሪደር ልማት አማካኝነት የተሽከርካሪዎችም ሆነ የእግረኛ መንገዶች ለእንቅስቃሴ አመቺ ሆነዋል፡፡ ይህም የትራፊክ ፍሰቱን ለማሳለጥ ምቾት ፈጥሯል፡፡ በኮሪደር ልማቱ በለሙ መንገዶች ላይ የትራፊክ መጨናነቅ አይታይም፡፡ የሚዞር መኪና በነጻነት ይዞራል። እግረኛ ሳይሳቀቅ የሚሻገርበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮለታል፡፡ ቀደም ሲል ግን መንገዶቹ የተጨናነቁ ስለነበሩ የከፋ ችግር ያጋጥም ነበር። መንገድ በመሳት የትራፊክ አደጋ ሲከሰት ቆይቷል የምትለው በጎ ፈቃደኛዋ፣ ለሁለት እግር ተሽከርካሪዎችም መንገዱ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ መሰራቱ የትራፊክ ፍሰቱን የተሻለ እንዳደረገው ገልጻለች፡፡

ወጣት መቅደላዊት ለገሰም በተመሳሳይ በትራፊክ ማስተናበር ላይ የተሰማራች በጎ ፈቃደኛ  ናት፡፡ አጠቃላይ የትራፊክ በጎ ፍቃድ አገልግሎት መስጠት ከጀመረች ሦስት ዓመታትን አስቆጥራለች፤ በኮሪደር ልማቱ በለሙ መንገዶች ላይ ማስተናበር ከጀመረች ደግሞ ሁለት ወራት ሆኖታል፡፡

የኮሪደር ልማቱ ለማስተናበር ስራው መሳለጥ ያለውን አበርክቶ፤ “ቀድም ሲል መንገዶቹ የተጨናነቁ ስለነበር የትራፊክ አገልግሎት ለመስጠት ይከብድ ነበር፡፡ የእግረኛ መንገዱ ጠባብ ስለነበረ እግረኞች በመኪና መንገድ ከመኪናዎች ጋር ተቀላቅለው ነበር የሚጓዙት፡፡ አሁን ላይ ግን መንገዱ ለመኪናም ለሰውም አመቺ በሆነ መንገድ ስለተሰራ የማስተናበር ስራውን ለመከወን ቀላል አድርጎታል” ስትል ገልጸዋለች፡፡

ሁሉም ባይሆኑም አንዳንድ አሽከርካሪዎች የበጎ ፍቃደኞችን ትእዛዝ ያለመቀበልና ጥሶ የመሄድ፣ በተመሳሳይ እግረኞችም ‘ምን አገባሽ፤ እንደፈለግሁ እሄዳለሁ’ የሚል ቀና ያልሆነ ምላሽ የሚሰጡ ያጋጥማሉ፡፡ አልፎ አልፎም ዘለው መሀል አስፋልት የሚገቡ ቁጥራቸው ጥቂት የሚባሉ አይደሉም፡፡ በአንፃሩ ‘ለእኛ ብላችሁ ነው ጊዜያችሁንና ጉልበታችሁን መስዋእት እያደረጋችሁ ያላችሁት፤  እናመሰግናለን፤ ተባረኩ’ ብለው ቀና ምላሽ የሚሰጡ አሽከርካሪዎችና እግረኞች ብዙዎች ናቸው” በማለትም በዕለት ተዕለት የበጎ ፈቃድ ተግባሯ የታዘበችውን ተናግራለች፡፡

አቶ ሽመልስ አስራት በፒያሳ ደጎል አደባባይ አካባቢ አስፋልት ለመሻገር ቆመው አግኝተን የትራፊክ እንቅስቃሴውን በተመለከተ ከኮሪደር ልማቱ በፊት እና በኋላ የታዘቡትን ሁኔታ እንዲነግሩን ጠይቀናቸው በሰጡት ምላሽ፤ “ልዩነቱ የሰፋ ነው፡፡ ቀደም ሲል የእግረኛውም ሆነ የመኪና መንገዱ ጠባብ ከመሆኑም በላይ በአስፋልት ዙሪያ የተንሰራፋው ህገ ወጥ የጎዳና ላይ ንግድ ከመኪና ጋር እየተገፋፋን ለመጓዝ አስገድዶን ነበር፡፡ አሁን ላይ የመንገድ መሰረተ ልማቱ ላይ አመርቂ ለውጥ ያመጣው የኮሪደር ልማት መኪናውም ሆነ እግረኛው የራሱን መንገድ ይዞ ለመንቀሳቀስ እድል የሰጠ ነው” ብለዋል፡፡

በጎ ፍቃደኛ አስተናባሪዎች እየሰጡት ያለው አገልግሎት የሚመሰገን ነው፡፡ መንገድ ተመቸኝ ብሎ በፍጥነት የሚያልፍ መኪና አቀዝቀዞ እግረኛ እንዲያልፍ ያደርጋሉ፡፡ አሽከርካሪውንም እግረኛውንም በመጥቀም ላይ ናቸው፡፡ ምክንያቱም የቸኮለ እግረኛ ሮጬ ልሻገር ቢል ጉዳቱ ለሁለቱም ነው፡፡ አገልግሎት አሰጣጣቸውም አክብሮት በተሞላበት መሆኑንም አክለዋል፡፡ 

በፒያሳ ዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም አካባቢ ሲያሽከረክሩ ያገኘናቸው ወይዘሮ ሰላም አያሌውንም በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየታቸውን እንዲያጋሩን ጠይቀናቸዋል፡፡ በምላሻቸውም፣ “በኮሪደር ልማቱ በለሙት አስፋልት መንገዶች ላይ ከመንገዱ አመችነት ጋር ተያይዞ አሽከርካሪዎች ፍጥነት  በተሞላበት  መልኩ  ስለሚያሽከረክሩ ትራፊክ አስተናባሪዎች መኖራቸው ጠቀሜታቸው ከፍ ያለ ነው፡፡ አሽከርካሪዎች በከተማ ማሽከርከር ያለባቸውን የፍጥነት ወሰን ጠብቀው እንዲያሽከረክሩ የማንቂያ ደወል ሆነው ያገለግላሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አቅመ ደካሞች፣ ህጻናት፣ አካል ጉዳተኞች የመሳሰሉ ድጋፍ የሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎች ደህንነታቸው በተጠበቀ ሁኔታ እንዲሻገሩ ድርሻቸው ከፍተኛ ነው፡፡ የትራፊክ ፖሊሶችን በደንብ እያገዙ ነው። ስራቸውንም ያለመሰልቸት ሲሰሩ አያቸዋለው ሲሉ አድናቆታቸውን ለግሰዋል፡፡

በአራዳ ክፍለ ከተማ የትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን የመንገድ ደህንነት ግንዛቤና አቅም ግንባታ ቡድን መሪ አቶ ድሪብሳ ጉደታ በክፍለ ከተማው የክረምት የትራፊክ በጎ ፍቃድ ስራው አተገባበር ምን እንደሚመስል ማብራሪያ ሰጥተውናል፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ፤ የክረምት የትራፊክ በጎ ፈቃድ አተገባበር የሚበረታታ ነው። የኮሪደር ልማቱም በጎ ፈቃደኞቹ ስራቸውን ሳይቸገሩ እንዲወጡ መልካም አጋጣሚ ፈጥሮላቸዋል፡፡ ለእግረኛ፣ ለመኪና እንዲሁም ለባለሁለት እግር ተሸከርካሪ ምቹና በተለየ ሁኔታ በመሰራቱ በበጎ ፍቃድ ትራፊክ ለሚያስተናብሩት መልካም አጋጣሚ ፈጥሮላቸዋል፡፡

በጎ ፈቃደኞቹ ማህበረሰቡ ተገቢ የመንገድ አጠቃቀም እንዲከተል እንዲሁም የትራፊክ መጨናነቅ በሚበዛባቸው አካባቢዎችና ሰዓታት የማስተናበር ስራ መስራታቸው ከሰውና ከንብረት አልፎ ተርፎም በተለይም በኮሪደር ልማቱ የለማውን የመንገድ መሰረተ ልማት እንዲጠበቅ በማድረግ የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው። እንደ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን በጎ ፈቃደኛ የትራፊክ አስተናባሪዎችን ከመደገፍ ባለፈ የክረምት የመንገድ ደህንነት አጠቃቀም በክፍለ ከተማው ለሚገኘው ማህበረሰብ በተለያዩ መንገዶች ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እየተሰራ ነው። ትልቁ የትራፊክ አደጋን መቀነስ የሚቻለው የማህበረሰቡ የመንገድ ደህንነት አጠቃቀሙ እየዳበረ ሲሄድ ነው፡፡ አሽከርካሪውም ሆነ መንገደኛው ለህግና ደንብ ተገዢ ሆኖ በተፈቀደለት መንገድ መጓዝ ሲችል በመሆኑ ለተግባራዊነቱ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ሲሉም አክለዋል፡፡

በበጎ ፈቃድና ህብረተሰብ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ኮሚሽን የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ሶፎኒያስ ፍስሀ በበኩላቸው የዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የተጀመረው ግንቦት 1 ቀን 2016 ዓ.ም ሲሆን፤ እስከ መስከረም 30 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ ይቆያል። በመንገድ ትራፊክ አጠቃቀም ላይ እየተሰተፉ ያሉ በጎ ፈቃደኞች ቁጥርም ከ6 ሺህ በላይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በመዲናዋ አዲስ አበባ ከተማ የትራፊክ መጨናነቅ በሚበዛባቸው መንገዶችና አደባባዮች እንዲሁም የዜብራ መሻገሪያ ላይ በመሆን የትራፊክ ፍሰቱን የሚያሳልጡ ናቸው። ክረምት እንደመሆኑ መጠን አብዛኞቹ በጎ ፍቃደኞች ትምህርት ላይ ያሉ ወጣቶች ናቸው።ዓላማቸውም የእረፍት ጊዜያቸውን በመጠቀም ማህበረሰባቸውን በበጎ ፈቃድ ማገልግል ነው፡፡

በኮሪደር ልማቱ የለሙት መንገዶች ደህንነት መጠበቅ አለባቸው። ለዚህ ደግሞ እንደ ዜጋ ሁሉም የድርሻውን የመወጣት ግዴታ አለበት፡፡ ለዚህ በጎ ፈቃደኞቹ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ኮሚሽኑ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ ሰርቷል፡፡ በኮሪደር ልማቱ የተሰሩ የተለያዩ የልማት ስራዎች በንጽህናና በደህንነት እንዲያዙ፣ አሽከርካሪዎች ፍጥነታቸውን ጠብቀው በመጓዝ አደጋ እንዳይፈጥሩ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እየተሰራም ይገኛል፡፡

እግረኞችና አሽከርካሪዎች በጎ ፍቃደኞቹ የሚሰጡትን መልእክት መስማትና ማክበር እንዲሁም ተቀብለው መተግበር ይኖርባቸዋል። በጎ ፈቃደኞቹ ማህበረሰባቸውን ለማገልግል እንጂ ምንም አይነት የሚያገኙት ጥቅም የሌለ በመሆኑም ለሚሰጡት አገልግሎት ክብርና ምስጋና መስጠት ከሁሉም ይጠበቃል፡፡ የበጎ ፈቃደኞቹ ክፍያ የማህበረሰቡ ምስጋና ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከእያንዳንዱ የማህበረሰብ ክፍል ይጠበቃል ሲሉ አቶ ሶፎኒያስ ተናግረዋል፡፡

በለይላ መሃመድ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review