AMN – ጥር 14/2017 ዓ.ም
በሀገራዊ ምክክሩ ለኢትዮጵያ መጻዒ ዕድል ሁሉም ዜጋ ድርሻ እንዲኖረው ጥረት እየተደረገ መሆኑን የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ገለጹ።
ፕሮፌሰር መስፍን ይህን ያሉት ሀገራዊ መግባባት ላይ ትኩረት ባደረገው ሁለተኛው የዜጎች የፓርላማ ፎረም ላይ ተገኝተው ነው።
እንደ ፕሮፌሰር መስፍን ገለጻ፣ ኢትዮጵያውያን ያለምንም ልዩነት የሚግባቡባቸው የጋራ አጀንዳዎች አሏቸው።
ለአብነት የአድዋ ድል እንዲሁም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በማንሳት።
ኢትዮጵያ ለዘመናት የተከማቹና ስር የሰደዱ ያለመግባባቶችን በምክክርና በውይይት ለመፍታት ያላሰለሰ ጥረት እያደረገች መሆኗንም አንስተዋል።
ሀገራዊ ምክክሩ ሁሉንም ዜጋ ባሳተፈና የተለያዩ አጀንዳዎችን ባካተተ መልኩ እንዲካሄድ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ነው ብለዋል።
ባለፉት ዓመታት የተወሰኑ ልሂቃንና ፖለቲከኞች ሀገሪቱን እንዲዘውሩ ዕድል በማግኘታቸው አሁን እያጋጠመ ላለው ችግር መነሻ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በሀገራዊ ምክክሩ ሁሉም ዜጋ ለሀገሩ መጻዒ ዕድል የተሻለ አበርክቶ እንዲኖረው ጥረት እየተደረገ መሆኑን አንስተው እስካሁን ባለው ሂደት በአብዛኞቹ የሀገሪቱ አካባቢዎች ህዝብን ማወያየትና አጀንዳ መለየት ተችሏል ብለዋል።
ሀገራዊ ምክክሩ ወገንተኝነቱ ለሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ መሆኑን ጠቅሰው፣ ሃይማኖትና የፖለቲካ ልዩነት ሳይገድበው የሁሉንም ሀሳብ እኩል የሚያስተናግድ ነው ሲሉም ገልጸዋል።
በምክክር ሂደቱ በአጭር በመካከለኛና በረጅም ጊዜ ሊፈቱ የሚችሉ አጀንዳዎች መኖራቸውንም መጥቀሳቸውን ኢዜአ ዘግቧል።