AMN – ታኅሣሥ 09/2017 ዓ.ም
ለሀገር ጥቅም ሲባል ልዩነቶችን ወደጎን በመተው በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ መቆምን መልመድ አለብን ሲሉ የኢዜማ ሥራ አስፈፃሚ አባል አቶ ግርማ ሰይፉ ተናገሩ።
አቶ ግርማ ሰይፉ በቅርቡ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል የተደረገውን የአንካራ የትብብር ስምምነትን በተመለከተ ከኤ ኤም ኤን ጋር ቆይታ አድርገዋል።
በቆይታቸውም ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት የነበረችበትን ታሪክ በማስታወስ ከ1983 ጀምሮ የኢትዮጵያ ሕዝብ የባህር በር ይፈልግ ነበር ብለዋል።
በወቅቱ የነበረው ገዢው ፓርቲ ጉዳዩን ማንሣት እንደ ነውር ይቆጥረው እንደነበር የገለጹት አቶ ግርማ፣ በዚህም ጉዳዩ የመንግሥት ድጋፍ የሌለው፣ የተቃዋሚዎች አጀንዳ ብቻ ሆኖ መቆየቱን ተናግረዋል።
ይህንን የረጅም ጊዜ ጥያቄ ለመመለስ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ደረጃ ኢትዮጵያ የባህር በር እንደሚያስፈልጋት የውይይት አጀንዳ ሆኖ መነሣቱ ትልቅ የምሥራች እንደነበር አስታውሰዋል።
ውሳኔው ብልጽግና ፓርቲ በታሪክ ውስጥ በወርቅ ቀለም ከሚጻፉለት ታሪክ አንዱ ነው ሲሉም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በማንኛውም ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊም ሆነ ዲፕሎማሲያዊ መንገድ የባህር በር እንደሚያስፈልጋት ፖለቲከኛው ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ከፍተኛ የሠለጠነ የባህር በር የነበራት ሀገር እንደነበረች አስታውሰው አሁን ላይ ሙሉ በሙሉ የምትቆጣጠረው ቢያንስ አንድ የባህር በር እንደሚያስፈልጋትም ገልጸዋል።
በመሆኑም ትልቅ ሀገር ለሆነችው እና ለዓለም ሰላም ብዙ አስተዋጽኦ ለምታበረክተው ኢትዮጵያ የዓለም ሀገራት ድጋፍ መስጠት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል አቶ ግርማ።
በቅርቡ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል የተፈረመው የአንካራው ስምምነት ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የፈረመችው የመግባቢያ ስምምነት ያመጣው ውጤት መሆኑን ጠቁመው ይህም፣ ኢትዮጵያ ብዙ የወደብ አገልግሎት ሊሸጡላት የሚችሉ ኃይሎች እየተፈጠሩ መሆናቸውን ያመላክታል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የባህር በር ያስፈልጋታል በሚለው ጥያቄ ምንም ልዩነት ሊኖረን አይገባም ያሉት አቶ ግርማ፣ ስምምነቱ እንዲተገበር ሁሉም ዜጋ ከመንግሥት ጎን እንዲቆም እና ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል።
በሰፊና ሁሴን