በሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት እና መልሶ ማልማት በስምንት ኮሪደሮች ከ2 ሺ 817 በላይ ሄክታር ቦታ ለማልማት ታቅዷል- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

You are currently viewing በሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት እና መልሶ ማልማት በስምንት ኮሪደሮች ከ2 ሺ 817 በላይ ሄክታር ቦታ ለማልማት ታቅዷል- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

AMN – መስከረም 28/2017 ዓ.ም

በሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት እና መልሶ ማልማት በስምንት ኮሪደሮች 132 ኪሎሜትር ርዝመት እና ከ 2 ሺ 817 ሄክታር በላይ ቦታ ለማልማት መታቀዱን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት እና መልሶ ማልማት ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመጀመሪያው ዙር የኮሪደር ልማት ያለው አፈጻጸም ተገምግሞ ጠንካራ ጎን እና ክፍተቶች ተለይተው ቅድሚያ የጥናት ስራው ተጠናቆ ወደ ዝግጅት መገባቱን ከንቲባ አዳነች አቤቤ አንስተዋል።

ከጥናት ቀጥሎ የዲዛይን እና ህዝብን የማወያየት ስራዎች መሰራታቸውን እና እነዚህ ቅድመ ዝግጅቶችም ቀድመው በመጠናቀቅ ላይ መሆናቸውን ከንቲባዋ ተናግረዋል።

የልማት ተነሺዎችን እና የሚነሱ መሰረተ ልማቶችን የመለየት ስራ በቀጣይ ትኩረት የተሰጠው ሲሆን በመረጃ ላይ ክፍተት እንዳይፈጠር የከተማዋ ከፍተኛ አመራሮች እስከታች በመውረድ ህዝብን ማወያየታቸውን እና በተነሺዎች ልየታም ከነዋሪው ጋር የጋራ ኮሚቴን በማቋቋም በከፍተኛ ጥንቃቄ መሠራቱን ተናግረዋል።

ከቅድመ ዝግጅት ስራው በዋነኛነት ለሚነሱ ነዋሪዎች ቅድሚያ በመስጠት ነዋሪዎች ተነስተው ለሚሰፍሩበት ስፍራ ዝግጅት ትኩረት መሰጠቱን የተናገሩት ከንቲባ አዳነች በዚህም 4ሺ የሚደርሱ መኖሪያ ቤቶች ለተነሺዎች መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡

ለስራ እድል ፈጠራ በጥቃቅን እና አነስተኛ ለተደራጁ አካላት በቂ የማምረቻ፣ መሸጫ እና ምርት መያዣ ሼዶች በቀበሌ እና በንግድ በቤቶች ኮርፖሬሽን ሲሰሩ የነበሩ ነጋዴዎች ተደራጅተው የንግድ ቦታ እንዲገነቡ እንዲሁም በአነስተኛ ሱቆች ሲሰሩ ለነበሩ 500 የሚደርሱ የሱቅ ኮንቴነሮች መዘጋጀታቸውንም ከንቲባዋ ተናግረዋል።

በሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ከሚነሱ መካከል 80 በመቶው የቀበሌ ቤት ፣ 10 በመቶው የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ቤቶች ነዋሪዎች እና 10 በመቶው የግል ባለይዞታዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።

ለእነዚህ የግል ባለይዞታዎችም 5 ቢሊየን ብር የሚደርስ ካሳ እና 100 ሄክታር የሚጠጋ ምትክ መሬት የተዘጋጀ ሲሆን የሁለት አመት የቤት ኪራይ ክፍያም ተዘጋጅቶላቸዋል ብለዋል፡፡

እንዲሁም ለሁሉም የልማት ተነሺዎች የእቃ ማጓጓዣ እና የስነ ልቦና ካሳ ክፍያም ጭምር እንደተዘጋጀላቸውም ተገልጿል።

በሰብስቤ ባዩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review