AMN – የካቲት 2/2017 ዓ.ም
በአዲስ አበባ ከተማ በህገ-ወጥ መንገድ በአይሱዚ ተሸከርካሪ ሲዘዋወር የነበረ 7 ሺህ 831 ሊትር ቤንዚን በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡
ቤንዚኑ በቁጥጥር ስር የዋለው በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ልዩ ቦታው ከአንፎ አደባባይ ወደ ጦር ኃይሎች በሚወስደው መንገድ በህገ-ወጥ መንገድ ሲዘዋወር መሆኑ ተገልጿል፡፡
የክፍለ ከተማው ህገ-ወጥ ንግድ ቁጥጥር ግብረ-ኃይል ምክትል ሰብሳቢ አቶ አሸናፊ ፍቅሬ፤ በክ/ከተማው ከአንፎ አደባባይ ወደ ጦር ኃይሎች በሚወስደው መንገድ ላይ በአይሱዚ ተሸከርካሪ ተጭኖ ሲዘዋወር የነበረ 7 ሺህ 831 ሊትር ቤንዚን ነዳጅ በቀራኒዮ አካባቢ ፖሊስ ኦፊሰሮች መያዙን ተናግረዋል፡፡
በህገወጥ መንገድ ሲዘዋወር የተገኘው ቤንዚን በህገ-ወጥ ንግድ ቁጥጥር ግብረ ኃይል አማካኝነት በአቅራቢያ በሚገኝ ማደያ እንዲሸጥ በማድረግ 794 ሺህ 611 ብር በገንዘብ በፋይናንስ ዝግ አካውንት ለመንግስት ገቢ እንዲሆን መደረጉንም አቶ አሸናፊ ጠቁመዋል።
ህብረተሰቡ እንዲህ አይነት መሰል ህገወጥ ድርጊቶችን ሲመለከት ጥቆማ በመስጠት እንዲተባበር ጥሪ ማቅረባቸውን ከክፍለ ከተማው ኮሙዩኒኬሽን ፅ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።