AMN ህዳር 23/2017 ዓ.ም
በለውጡ ዓመታት የተከናወኑ የልማት ሥራዎች የአካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚነት ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸውን የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን ገለጸ።
በኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት በሁሉም ዘርፎች አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ የልማት ሥራዎች በስፋት ተከናውነዋል።
የኮሪደር ልማትን ጨምሮ በተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ምቹ አካባቢን በመፍጠር፣ በትምህርት ተደራሽነትና በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ ተጨባጭ ሥራዎች ተከናውነዋል።
በለውጡ ዓመታት በመሠረተ-ልማት ግንባታዎች ጭምር መንግሥት ለአካል ጉዳተኞች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት መሥራቱን የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አባይነህ ጉጆ አንስተዋል።
የአካል ድጋፍ አግኝተው ወደ ቀደመ ሥራቸውና ኑሯቸው እንዲመለሱ የአካል ድጋፍ ማምረቻ ማዕከልን በማጠናከር ረገድ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሚና የላቀ እንደነበር አንስተዋል።
በተለይም ለአይነስውራን ምቹና ዘመናዊ አዳሪ ትምህርት ቤት እንዲገነባ በማድረግ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ዘመን ተሻጋሪ ሥራ መሥራታቸውን ያነሱት ፕሬዝዳንቱ ለሁሉም ምስጋና አቅርበዋል።
የአይነስውራን 2ኛ ደረጃ አዳሪ ትምህርት ቤትም ለአይነስውራን የመማር ተስፋቸውን ያለመለመ ትልቅ ሥራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በለውጡ ዓመታት ለአካል ጉዳተኞች የሚጠቅሙ የሕግና አሠራር ማሻሻያዎችን ለማድረግ የተጀመረው ጥረትም ወደ መጨረሻው ምዕራፍ እየተሸጋገረ በመሆኑ በቀጣይ ትልቅ ዕድል ይዞ የሚመጣ መሆኑን አንስተዋል።
በተደጋጋሚ ቅሬታ ሲቀርብበት የቆየውን የሕንፃ አዋጅ ለማሻሻልም አዲስ ረቂቅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቅረቡን ጠቅሰዋል።
እንደ አጠቃላይ በአዲስ አበባና ሌሎችም አካባቢዎች የተከናወኑ እና በመከናወን ላይ ያሉ መሠረተ-ልማቶች አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸው ለአካል ጉዳተኞች ትልቅ ተስፋ ሆኗል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።