AMN – መስከረም 28/2017 ዓ.ም
በሊባኖስ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ደኅንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን የቴክኒክ ኮሚቴ ተቋቁሞ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
በሊባኖስ የሚኖሩ ዜጎችን ደህንነት በተመለከተ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተሰጠ መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሊባኖስ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ደኅንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን የቴክኒክ ኮሚቴ አቋቁሞ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል።
ከአሁን በፊት በተለያዩ አገራት ለችግር የተዳረጉ ኢትዮጵያውያንን ወደ አገራቸው ለመመለስ የተቋቋመው ብሔራዊ ኮሚቴ ቀዳሚ ትኩረቱን በሊባኖስ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን በማድረግ እየሰራ ነው። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር ቤይሩት የሚገኘው ቆንስላ ጀኔራል ጽ/ቤት የዜጎችን ምዝገባ እና ክትትል በተሻለ ፍጥነት ለማካሄድ የሚያስተባብር አመራር ወደ ሊባኖስ ተልኮ ሥራውን ጀምሯል። ቆንስላ ጀኔራል ጽ/ቤቱ ካለበት አገር የአገሪቱን ቋንቋ የሚችሉ ተጨማሪ ሰራተኞችን በመቅጠር እየሠራ ነው።
በአሁኑ ወቅትም ቆንስላ ጀኔራል ጽ/ቤቱ በሊባኖስ የሚገኙ ዜጎቻችንን በአካል እና ዲጂታል ምዝገባ ስርዓት ዘርግቶ እያከናወነ ይገኛል። በዚህ አጋጣሚ በሊባኖስ የምትገኙ ኢትዮጵያውያን በቆንስላ ጀኔራል ጽ/ቤቱ በተጠቀሰው አድራሻ እና በዲጂታል መመዝገቢያ እንድትመዘገቡ ጥሪ እናቀርባለን።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዜጎች አንጻራዊ ደኀንነት ወደ አለበት የሊባኖስ አካባቢ እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ እና ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ህጻናት እና ሴቶችን ወደ አገራቸው ለመመለስም ሁሉንም አማራጮች ለመጠቀም ከተለያዩ አካላት ጋር ጥረት እየተደረገ ነው።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አሁን ላይ በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲው ቅድሚያ በሊባኖስ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን በመስጠት ደኀንነታቸው ችግር ላይ እንዳይወድቅ ከፍተኛ ርብርብ እያደርገ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ለመግለጽ ይወዳል።
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
መስከረም 28 ቀን 2017 ዓ.ም