በልማቱ የተሣሠሩ ፈርጦች

በአዲስ አበባ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከፍ ያለ ፋይዳ ያላቸው ትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶች በስፋት እየተከናወኑ ነው፡፡ ለአብነት ዘመኑ የደረሰበትን የኪነ ህንፃ ጥበብ በመጠቀም የዓድዋ ድል መታሰቢያ፣ እንጦጦ ፓርክ፣ አንድነት ፓርክ፣ ወዳጅነት አደባባይ፣ አብርሆት ቤተ መጻሕፍት፣ ሳይንስ ሙዚየም፣ የመንገድ እና የተለያዩ መሰረተ ልማቶች በተለያዩ የከተማዋ አካባቢ ተገንብተው ለነዋሪው አገልግሎት እየሰጡ ነው፡፡

ልማት መከናወኑ በራሱ በጎ ሆኖ እርስ በእርስ እንዲተሳሰር ማድረግ ደግሞ ፋይዳውን የላቀ ያደርገዋል፡፡ አዲስ አበባ ከዚህ አንጻር ምን የቤት ስራ አለባት? ከዚህ አንጻር እየሄደችበት ያለው ርቀት እና የኮሪደር ልማቱ ያለውን አበርክቶ መዳሰስ ያስፈልጋል፡፡ 

በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የአርክቴክቸር ትምህርት ክፍል መምህርና የከተማ ፕላን ባለሙያ መስፍን አለሙ ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡት ማብራሪያ እንደገለጹት፤ የኮሪደር ልማት ስራው ለአዲስ አበባ በርካታ ጥቅሞች አሉት፡፡ ዋናው በየአካባቢው ያሉትን መሰረተ ልማቶችን ማሻሻል ነው። ይህም የመንገድ፣ የውሃ፣ የመብራት፣ የፍሳሽ ማስወገጃ መስመሮችና ሌሎችም ደረጃቸውን በጠበቀ ሁኔታ የማሻሻል ስራ ተከናውኖበታል። የመንገድ መሰረተ ልማቶች ለተሽከርካሪዎች፣ ለእግረኞች፣ ሁለት እግር ተሸከርካሪ ለሚጠቀሙ ምቹ የማድረግ ስራም እንዲሁ፡፡

የዓድዋ ድል መታሰቢያ

የመሰረተ ልማት ዝርጋታው ምቹ ሲሆን ሰላማዊ፣ ከቆሻሻ የፀዳ ጤናማ አካባቢ እንዲፈጠር፣ የሰዎች እንቅስቃሴን የማይገድብ፣ ሰዎች ንፁህና ግልፅ የሆነ ቦታ ላይ እንዲንቀሳቀሱ ያስችላል፡፡ በኮሪደር ስራው በየመንገዱ የሚገጠሙ የደህንነት ካሜራዎች፣ የመንገድ ላይ መብራቶች መኖር አካባቢው ግልፅ እንዲሆን ያደርጋል፡፡ ወንጀል ለመስራት ምቹ ሁኔታ ስለማይፈጥር የከተማዋን ደህንነት ለማስጠበቅ ትልቅ አስተዋፆ እንዳለው መምህር መስፍን ያስረዳሉ፡፡

የኮሪደር ልማቱ በተለያየ አካባቢ የሚገኙ ልማቶችን በቀላሉ ለማገናኘትም ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ነው ባለሙያው የሚገልፁት። በተለያየ ቦታ ያሉ ልማቶች ባሉበት አካባቢ ብቻ አይታጠሩም፡፡ የኮሪደር ስራው ከሌሎች ልማቶች ጋር የሚያገናኛቸው በመሆኑ አንድ አካባቢ የሚሄድ ሰው አንዱን አይቶ በቀላሉ ወደ ሌላ ለመሄድ ያስችለዋል፡፡

 የኮሪደር ልማት ስራው የትራንስፖርት አገልግሎቱንም ምቹና ቀላል ያደርገዋል፡፡ ሁሉም ቦታ አንድ አይነት እና ጥራት ባለው ሁኔታ የማግኘት እድል ይፈጥራል። የመሰረተ ልማት ሀብት ክፍፍሉን በየአካባቢው እኩል ያደርገዋል።

ከዚህ አልፎ በከተማ የለሙ አካባቢዎች በእኩል ደረጃ እንዲፈጠሩ ስለሚያደርጉ ተፈላጊ ያደርጋቸዋል፡፡ ባለሀብቶች (ኢንቨስተሮች) መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈስሱ ያበረታታል። ይህ ደግሞ ለአዲስ አበባ ከተማ ኢኮኖሚያዊ እድገት የራሱ አስተዋፅኦ አለው፡፡ በየቦታው የተሰሩ ልማቶች ከተገናኙ አዲስ አበባ ዘመናዊነቷ ከፍ እንዲልና የቱሪዝም ማዕከል እንድትሆን ያስችላል ይላሉ፤ የከተማ ፕላን ባለሙያው፡፡

አንድነት  ፓርክ

እንደ  መምህር  እና የከተማ ልማት  ባለሙያ መስፍን ገለፃ፤ በኮሪደር ልማት ከተሞችን ውብና ለነዋሪው ምቹ ማድረግ  በበርካታ የውጭ ሃገራት ተግባራዊ የተደረገ አሰራር ነው። ለምሳሌ፦ ኔዘርላንድ ውስጥ የምትገኘው አንትወርፕ የምትባል ከተማ በወንዞች ዳር የኮሪደር ልማት ውብ ሆና ተገንብታለች፡፡ ከተማዋ ባላት የውሃ ሀብት የምትታወቅ ሲሆን፤ በከተማዋ የኮሪደር ልማቱ ውሃን ተከትሎ የተሰራ ነው፡፡

የመሰረተ ልማት ኔትዎርክ፣ የውሃ ኔትዎርክ፣ የአረንጓዴ ልማት ኔትዎርክ፣ የህንፃ ዲዛይን በማካተት በኮሪደር ልማቱ በተሰራው ስራም ትልቅ ምሳሌ የምትሆን ከተማ ነች፡፡ የከተማዋ ልማቶች በሁሉም ቦታ ተገናኝተዋል፡፡ ይህች ከተማን ጨምሮ ሲንጋፖር፣ ዱባይ፣ ሆንግ ኮንግ፣ ሴኡል እና ኩሪቲባ (ከብራዚል) በኮሪደር ስራ የተሰሩ ልማቶች እርስ በእርስ እንዲገናኙ የተደረገባቸውና ምሳሌ የሚሆኑ ከተሞች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

የከተማ ፕላን ባለሙያው እንዳብራሩት፤ በአዲስ አበባ በኮሪደር ልማት በየአካባቢው ያሉ የተሰሩ ልማቶችን የማገናኘት ተግባሩ በጥሩ ሁኔታ የተከናወነ ነው፡፡ ፒያሳ፣ ሜክሲኮ፣ መገናኛ፣ ቦሌ እና ሌሎችም የኮሪደር ስራው የተጠናቀቁባቸው አካባቢዎች መገናኘታቸው የከተማዋን ገፅታ አስውበዋል፡፡ ሰዎች ከአንዱ አካባቢ ወደ ሌላው በቀላሉ እንዲንቀሳቀሱ አድርገዋል፡፡ ይህ ለከተማው ነዋሪ ብቻ ሳይሆን አዲስ አበባ የዲፕሎማቶችና የተለያየ ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ በመሆኗ ለውጭ ሀገር ሰዎችም የምትመች እንድትሆን ያደርጋታል፡፡

“ቃል በተግባር” በሚል ርዕስ በተዘጋጀው ዘጋቢ ፊልም ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዳብራሩት፤ “በከተማዋ የተከናወኑ የተለያዩ የልማት አካባቢዎች (ዶቶች) ለብዙ ሰው አይታዩም፡፡ ምክንያቱም አልተያያዙም፡፡ እንደ ነጥብ የተቀመጡ ናቸው፡፡ አንደኛው ነጥብ ከሌላው ጋር አልተያያዘም፡፡ ሰው አንደኛውን አይቶ ያደንቃል እንጂ ከሁለተኛው ጋር ያለውን ትስስር አያየውም፡፡ አሁን በአዲስ አበባ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ስራ እነዚህን የልማት አካባቢዎች የማገናኘት ነው፡፡ እንጦጦ አንድ የለማ አካባቢ ነው፡፡ አብርሆት፣ ወዳጅነት ፓርክ፣ ሳይንስ ሙዚየም የመሳሰሉ የለሙ ቦታዎች እየተገናኙ ሲሄዱ የአዲስ አበባን ውበት ለማየት ያስችላል” ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል፡፡

ሳይንስ ሙዚየም

አክለውም በኮሪደር ልማቱ የልማት ነጠብጣቦች (ዶቶችን) የማገናኘት ስራ ከአንደኛው አካባቢ ወደ ሌላኛው ሲኬድ በልማቶቹ የተቀራረቡ፣ ደረጃውን የጠበቁ መሆን አለባቸው፡፡ ከቀለም፣ ከመንገድ ስራ፣ ከመብራት እና ከሌሎችም ጋር ተያይዞ ተመሳሳይነት ያላቸው መሆን አለባቸው፡፡ ይህም የከተማዋን ደረጃ ከፍ ያደርገዋል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡

ልማት አንዴ ተሰርቶ የሚቆም ሳይሆን ክትትልን ይጠይቃል፡፡ የኮሪደር ልማቱም በቴክኖሎጂ የተደገፈ ክትትል ያስፈልገዋል። በዚህ ዙሪያ ከሚሰሩ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር መስራትም ይገባል ሲሉ የከተማ ፕላን ባለሙያው ሃሳባቸውን አጋርተዋል፡፡

“በአዲስ አበባ እየተተገበረ ያለው የኮሪደር ልማት ስራ ጅምሩ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ ይህ ተግባር በሌሎች የሀገሪቱ ከተሞችም መስፋፋት አለበት፡፡ እንደ ሀገርና እንደ ከተማ ማስተር ፕላን ሊኖረንም ይገባል፡፡ ከዚህ አንፃር ከተማዋ ፕላን እንዲኖራት ልማቱ ጥሩ ጅምር ነው፡፡ ከመንግስት ባለፈ በየደረጃው ያሉ አመራሮች፣ ነዋሪው፣ የንግዱ ማህበረሰብ ሌሎች አካላት በኮሪደር ስራው በመሳተፍ አዲስ አበባ ከዚህም በላይ እንድትለወጥ ማድረግ ይገባል፡፡ የተሰራው የኮሪደር ልማት ‘የኔ ሀብት ነው’ በማለት ሁሉም ሊጠብቀውና ሊንከባከበው ይገባል” ሲሉ የከተማ ፕላን ባለሙያው ሀሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡

በኮሪደር ልማቱ አዲስ አበባን ለመለወጥ የገዘፈ ስራ እየተሰራ ነው፡፡ በከተማዋ እዚህም እዚያም የተከናወኑ ልማቶች ተገናኝተው ፈክተው እንዲታዩ እየተደረገ ነው፡፡ በዚህ ተግባርም ከተማዋን እንደ ስሟ አዲስ፣ ውብ፣ የፈካች አበባ፣ ፅዱ፣ ለነዋሪዎቿ  የምትመች እንዲሁም ተወዳዳሪና ተመራጭ የቱሪዝም መዳረሻ ከተማ እያደረጋትም ይገኛል፡፡

ይህ አይነቱ መልካም ተሞክሮ ወደ ሌሎች  የሀገሪቱ ከተሞች እንዲሰፋ በማድረግ ረገድ አዲስ አበባ ሚናዋን እየተወጣች ትገኛለች፡፡

በቅርቡ ከአዲስ አበባ በተጨማሪም በተለያዩ የክልል ከተሞች መሰል የኮሪደር ልማት ስራዎች እንደሚከናወኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራራታቸውና ይህንን ስራ የሚከታተሉ አመራሮችን በተለያዩ ከተሞች መመደባቸው የሚታወስ ነው፡፡ ይህንንም ተከትሎ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በአዲስ አበባ ከሚያከናውኑት ሰፋፊ የኮሪደር ልማት ስራዎች በተጨማሪ የጎንደርና ቢሾፍቱ ከተሞችን የኮሪደር ልማት ስራ በየከተሞቹ ካሉ ሀላፊዎች ጋር በመሆን እንዲያስተባብሩ አቅጣጫ መቀመጡ አይዘነጋም፡፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤም በቅርቡ በጎንደር እና በቢሾፍቱ ተገኝተው ስራዎቹ የደረሱበትን ደረጃና በቀጣይ ስለሚከናወኑ ተግባራት ከከተሞቹ የስራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡ በቢሾፍቱ ጉብኝት ወቅት ባደረጉት ንግግር፣ የኮሪደር ልማት ከተማ ከማሳመር በዘለለ ብዙ የአስተሳሰብ ለውጥ አምጥቷል፡፡ በተለይም ለመጪው ትውልድ የሚተላለፍ የልማት ስራን በአጭር ግዜ መስራት እንደሚቻል ያሳየ  ነው ብለዋል፡፡

የሀገራችን ከተሞች ለኑሮ ምቹ እና ሳቢ እንዲሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባመነጩት ሀሳብ መሰረት የአዲስ አበባ ከተማ የኮሪደር ልማት ስራው የመጀመሪያው ምዕራፍ በስኬት ተጠናቅቋል፡፡ በዚህ የተገኘውን ልምድም በሌሎች ከተሞች ለማስፋት እየተሰራ  መሆኑን ተናግረዋል።

አብርሆት ቤተ መጽሐፍት

በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የከተማ ዲዛይንና ፕላን ተባባሪ ፕሮፌሰር ዳንኤል ሊሬቦ (ዶ/ር) ለጋዜጣው ዝግጅት ክፍል በሰጡት መረጃ እንደገለፁት፤ በአዲስ አበባ ከተማ የተሰራው የኮሪደር ልማት በየአካባቢው ያሉ የልማት ፕሮጀክቶችን፣ ዋና ዋና መንገዶችን፣ ወደ ግራና ቀኝ የሚገቡ መለስተኛ መንገዶችን በአጠቃላይ በከተማዋ መዋቅራዊ ፕላን ያሉ ልማቶችን የሚያስተሳስሩና የሚያገናኙ ሆነው መሰራት አለባቸው፡፡ ለአብነት ከ ሲ ኤም ሲ – መገናኛ፣ ከቦሌ – መገናኛ ያለው የኮሪደር ልማት ስራ ተጠናቋል፡፡ አሁን ከመስቀል አደባባይ መገናኛ የሚሰራው ኮሪደር ሲጠናቀቅ ሶስቱም የልማት አካባቢዎች (ዶቶች) ተገናኙ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የኮሪደር ስራው በከተማዋ ሁሉም አካባቢ ሲጠናቀቅ አንደኛው የልማት አካባቢ ከሌላው የልማት አካባቢ ጋር ስለሚገናኝ የትራፊክ እንቅስቃሴው፣ የእግረኛው፣ የሳይክል መንገዱና ሌሎችም ማህበራዊ እና የንግድ እንቅስቃሴዎች የተሳለጡ እንዲሆኑ ያስችላል ብለዋል፡፡

ዳንኤል (ዶ/ር) እንደሚገልፁት፤ የሁለተኛው ዙር የኮሪደር ስራ ከመጀመሪያው ኮሪደር ጋር ተገናኝቶ ሲጠናቀቅ ደግሞ በከተማዋ ያሉ የልማት አካባቢዎች ለአብነት እንደ ዓድዋ ድል መታሰቢያ፣ ወዳጅነት ፓርክ፣ አንድነት ፓርክ ያሉ አካባቢዎች ከሌሎች የመዝናኛ፣ የቱሪዝም፣ የንግድ ማዕከላት፣ ዋና ዋና መንገዶች በአዲስ አበባ ሁሉም አካባቢዎች ይተሳሰራሉ። በዚህም ከተማዋ ውብ፣ ለነዋሪዎች የተመቸች እና የተቀናጀና ወጥ የሆነ ገፅታ እንዲኖራት ያስችላል፡፡

ከዚህ ባለፈ የትራፊክ መጨናነቅን ያስቀራል፣ የከተማዋ ውበት ይጨምራል፣ የብዙሃን ትራንስፖርት እንዲስፋፋ ያደርጋል፤ በኮሪደር አካባቢ የሥራ እድል ይፈጠራል፤ የስማርት መፀዳጀ ቤት ይስፋፋል፣ የልጆች መጫወጫ፣ የህዝብ ማረፊያ፣ መዝናኛ ስፍራዎች፣ አረንጓዴ ቦታዎች ስለሚበዙ ለህዝቡ ኑሮ ምች የሆነች አዲ አበባ አንድትፈጠር ያደርጋል። በመሆኑም ኮሪደር ልማቱ በየቦታው የሚገኙ የልማት አካባቢዎችን እንዲያገናኝ ተደርጎ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ምሁሩ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

እኛም የልማት ስራዎች እርስ በእርስ የማስተሳሰሩ ስራ ይበልጥ ተጠናክሮ ይቀጥል፤ የተገኙ መልካም ተሞክሮዎችም ወደ ሌሎች ከተሞች እንዲሰፉ የማድረጉ ጉዳይም የበለጠ ይጎልብት እንላለን፡፡

በሰገነት አስማማው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review