AMN – ጥቅምት 15/2017 ዓ.ም
በሐረሪ ክልል በቀጣዮቹ 3 ወራት ብቻ በከተማ እና በገጠር ወረዳዎች 25 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ስራዎችን ለማከናወን እየተሰራ መሆኑን የክልሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር መዕረግ የከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙክታር ሳሊህ ገለፁ።
የኮሪደር ልማት ኢንሼቲቩ የሐረር ከተማን ገፅታ የቀየረ እና የክልሉን የወደፊት ዕድገት ታሳቢ ባደረገ መልኩ የተከናወነ ዘመን ተሻጋሪ የልማት ስራ መሆኑን አቶ ሙክታር ተናግረዋል።
በክልሉ በአንደኛው ዙር በተከናወነው የኮሪደር ልማት ስራ አበረታች ውጤቶች መመዝገቡን ጠቅሰው፤ በተለይ በዓለም አቀፉ የጁገል ቅርስ የተከናወነው የኮሪደር ልማት ስራ ቅርሱን ተጋርጦበት ከነበረው አደጋ የታደገ መሆኑን አንስተዋል።
በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር መሪነት ማህበረሰቡን በማስተባበር በተሰራው የኮሪደር ልማት ስራ ካለ ምንም የመንግስት ወጪ ቅርሱን መልሶ በማልማት ለነዋሪው ብሎም ጎብኚዎች ምቹ ማድረግ መቻሉንም ጠቁመዋል።
የኮሪደር ልማት ስራው በምሽት ጭምር እየተከናወነ የሚገኝ በመሆኑ የክልሉን የስራ ባህል የቀየረ እና ፕሮጀክቶችን በፍጥነት በመጨረስ የይቻላል መንፈስን የፈጠረ እንደሆነ አመላክተዋል።
ለሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማት የወሰን ማስከበር ስራዎች እየተከናወኑ ሲሆን ማህበረሰቡ ለልማቱ እያደረገው ያለው ትብብር ለስራው ምቹ ሁኔታን መፍጠሩንም ገልፀዋል።
የኮሪደር ልማቱ የኢንቨስትመንትና ቱሪዝም ዘርፉ እንዲነቃቃ ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ጠቁመው፤ የክልሉ መንግስት ግብረኃል በማቋቋም የተጠናከረ ድጋፍና ክትትል እያደረገ እንደሚገኝ የክልሉ ኮሙዩኒኬሽን መረጃ ያመለክታል።