AMN- መስከረም 9/2017 ዓ.ም
ለመስቀል ደመራና የኢሬቻ በዓላት አከባበር 16 ሺህ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ለማስተባበር መዘጋጀታቸውን የአዲስ አበባ ወጣቶች ማኅበር አስታወቀ።
በመስከረም ወር በደማቅ ስነስርአት ከሚከበሩት የአደባባይ በዓላት መካከል የመስቀል ደመራና የኢሬቻ በዓላት ይጠቀሳሉ።
በእነዚህ በዓላት በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ አገራት ቱሪስቶች፣ የበዓሉ አክባሪዎችና ታዳሚዎች ይሳተፉበታል።
የመስቀል ደመራና የኢሬቻ በዓላት አዲስ አበባ እንግዶቿን ተቀብላ ለማስተናገድ ከወዲሁ ሁለንተናዊ ዝግጅት በማድረግ ላይ ትገኛለች።
ለበዓላቱ ስኬታማ የአከባበር ሂደት ፣ለአቀባበልና መስተንግዶ በርካታ የመዲናዋ ወጣቶች ዝግጁ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ወጣቶች ማኅበር አስታውቋል።
የማኅበሩ ዋና ጸሐፊ ይሁነኝ መሀመድ፤ የኢትዮጵያ መገለጫና የዓለም ሃብት የሆኑትን የመስቀል ደመራና የኢሬቻ በዓላት እሴታቸው ተጠብቆ በደማቅ ስነስርአት እንዲከበሩ የበኩላችንን ለመወጣት ተዘጋጅተናል ብሏል።
በሁነቱ ላይ እንግዶችን ለመቀበል፣ ለማስተባበርና ለማስተናገድ 16 ሺህ የማህበሩ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ዝግጁ መሆናቸውንም ተናግሯል።
ከማህበሩ አባላት መካከል ወጣት ዮሴፍ አደል እና ብርቱካን በቀለ፤ ለበዓላቱ ስኬታማ አከባበርና ሰላማዊ ሂደት የበኩላችንን አስተዋጽኦ ለማበርከት ተዘጋጅተናል ሲሉ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።