AMN-ታህሣሥ 9/2017 ዓ.ም
በመንግስት በኩል ለሰላም፣ ለውይይትና ድርድር የምትጠልቅ ጀምበር እንደሌለች ደጋግመን ማረጋገጥ እንወዳለን ሲሉ አቶ አደም ፋራህ አስታወቁ።
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ ባስተላለፉት መልዕክት፣ “በዛሬው እለት በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች ህዝቡ በነቂስ በመውጣት በክልሉ ሰላም እንዲሰፍን፣የህግ የበላይነት እንዲከበር፣ በንፁሀን ላይ ግፍ እየፈፀሙ የሚገኙ ፅንፈኛ ኃይሎች ለህግ እንዲቀርቡ፣መንግስት በተደጋጋሚ እያቀረበ ለሚገኘው የሰላም ጥሪ ድጋፍ እንደሚቸር በይፋ ድምፁን አሰምቷል፣ እጅግ በጣም እናመሰግናለን” ብለዋል።
በቀጣይም ክልሉ በተሟላ ሁኔታ ዳግም ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲመለስ በብልፅግና ፓርቲ የሚመራው መንግሰት ህብረተሰቡን በማሳተፍ ያላሰለሰ ጥረት ማድረጉን እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡
በመንግሰት በኩል ለሰላም፣ ለውይይትና ድርድር የምትጠልቅ ጀምበር እንደሌለችም ደጋግመን ማረጋገጥ እንወዳለን ሲሉም በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባጋሩት መልዕክት አስፍረዋል።
ስለሆነም በአማራ ክልል ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አካላት በኃይል አማራጭ የሚገኝ መፍትሔ አለመኖሩን በመረዳት በዛሬው ሰልፍ ጨምሮ ሕዝቡ በተደጋጋሚ እያነሳቸው ያሉ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ፣ በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች እየታየ እንደሚገኘው በአስቸኳይ ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበዋል፡